Telegram Web
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ውይይይይይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥቁር መልበስ የአባቶች ጭንቀት እና አሜን እያሉ በእምባ የታጀበ ምላሽ የሚሰጡት ምስኪን ምዕመን ድምፅ መስማት እና ማየት እንደምን ያውካል ??

" እስከ ፍጻሜአችን ድረስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አንድነት ይጠብቀን ዘንድ ስለ አንድነታችን እንማልዳለን " በእንተ ቅድሳት ፍሬ ቅዳሴ ❤️
የዮሐንስ ወንጌል 19:3
"እየቀረቡም፦ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን፡ ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር"

የማቴዎስ ወንጌል 11:29
"ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤

አባቶቻችን ዛሬ ክርስቶስ የደረሰበት እየደረሰባቸው ነው ያለው ! እርሱም ከእኔ ተማሩ ነውና ያለው ከእርሱ በተማሩት መሰረት መከራን በጸጋ እየተቀበሉ ጠላቶቻችንን እየመረቁ ነው ያሉት ! በዚህች አስጨናቂ ሰዓት መከራን እና ሰማዕትነትን እየተቀበሉ ያሉትን ሰማዕታቱን እንምሰላቸው ! የካቲት 5 ሰልፍ እንዳትወጡ ተብሏል ነገር ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን የሚያስተላልፈው መምርያ ውጡ ከሆነ እንወጣለን !
የቀረ ምንም አይነት ሰልፍ የለም ምዕመናን !
እንጠንክር
እንድፈር
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እናስከብር
ዖዝያን....
በክብር ቢቀባ ፥በአስራ ሶስት አመቱ፤
በዙፋን ቢቀመጥ፥ ፀንቶለት ሹመቱ።
እግዚአብሔር ነገሩን፥ እየከወነለት፣
እልፍ እየማረከ፥ እልፍ ቢያስገዛለት።

በበረታ ጊዜ፥ ለጥፋት ታበየ፤
በመቅደሱ ሊያጥን፥ ጽና ይዞ ታየ።
ካህኑ የአሮን ልጅ፥ ዓዛርያስ ሳለ፤
ንግስናውን ትቶ፥ ንጉስ ልጠን አለ።

የእግዚአብሄር ፍርድ፥አይለወጥምና ፤
ተመለስ ንጉስ ሆይ፥ በዙፋንህ ጽና፤
ጽና ይዞ ማጠን፥ ያንተ አይደለምና፤
ቢለው አልሰማ አለ፥ ካህኑን ናቀና።

የትዕቢቱ መጠን፥ ዙፋኑን ነቀነቆ፤
ለየው ከንግስና፥ ካባውን አውልቆ።
ያደረገለትን ሀይል፥ ክብሩን ዘንግቶ፤
ንጉስ ልጠን አለ፥ ቤተመቅደስ ገብቶ።

እግዚአብሄር ቀሰፈው፣ ለምጽን አተመበት፤
በቤተ መንግስቱ፥ ልጁ ነገሰበት።
የማይነካ ነክቶ፥ንግስናው ተሻረ፤
ከአባቶቹ ርቆ፥ በእርሻ ተቀበረ።

ዛሬም ዖዝያን ሆይ!
በበረታህ ጊዜ፥ ጌታህን አትርሳ፤
እርሱ ነው የሚሰጥ፥ እርሱ ነው ሚነሳ።
ካህኑን አትንካ፥ የጌታን አገልጋይ፤
ቁልፍ አለና በእጁ፥ የመንግስተ ሰማይ።
++++
አንድ ቤተክርስቲያን
አንድ ሲኖዶስ
አንድ ፓትሪያርክ
አንድ መንበር
+++++
ሰማይ ስማ፥ ምድር አድምጪ፤
ቀን ወጣልኝ ብለሽ፥ ከሕጉ እንዳትወጪ።
በበደል ላይ በደል፥ እየጨመራችሁ፤
ዖዝያኖች ዛሬም፥ ትቀሰፋላችሁ።
++++++
©ታዜና
      #መንፈሳዊ_ግጥሞች
      www.tgoop.com/Menfesawigetmoch
!
ጠብቅ...!
!
ተዋህዶ እምነትህን፣
ቤተክርስቲያንህን፣
የአርባ ቀን ቤትህን፣
አንዲት ስስትህን፣
የደም ስርህን፣
እናት አለምህን፣
ስም የሰጠችህን፣
ልጅ ያረገችህን።
!
ጠብቅ...!
!
አባት ካህንህን፣
የሚባርክህን፣
የሚናዝዝህን፣
ይፍታህ የሚልህን፣
ግርማ ሞገስህን፣
የሲኖዶስህን፣
የፓትሪያርክህን፣
ዶግማ ቀኖናህን፣
እምነት ማተብህን።
!
ጠብቅ...!
! አታስነጥቅ።
++++
አንድ ቤተክርስቲያን
አንድ ሲኖዶስ
አንድ ፓትሪያርክ
አንድ መንበር
++++++
©ታዜና
      #መንፈሳዊ_ግጥሞች
      www.tgoop.com/Menfesawigetmoch
በቀድሞ ስማቸው አባ ንዋየ ሥላሴ አካሉ የይቅርታ ደብዳቤ በአስገቡ ሰዓት "የተሾሙበትን" አስኬማና አልባሳትም አስረክበዋል።

"እውነትን ተረድተው ስለመጡ ቤተ ክርስቲያን ደስተኛ ናት። ሌሎች በማወቅም ባለማወቅም የሄዳችሁ አሁንም ለመምጣት የተቸገራችሁ ቤተ ክርስቲያን በሯ ክፍት ነው::" ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
"መከራውን ቤቴ ሁኜ ልቀበል ብለው ስለመጡ ቤተ ክርስቲያን ደስ ይላታል፤ ሌሎችም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከእኛ ጋ ናቸው ተብላችሁ ተታላችሁ የሄዳችሁ፤ ፀፀት ውስጥ እንዳላችሁ እናውቃለን። ሌሎች ለመምጣት እየፈለጉ ቁልፍ ተይዞባቸው እንደተቸገሩም ሰምተናል:: " ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ይህንን የተናገሩት በሕገ ወጥ መንገድ ከተሾሙት "ኤጲስ ቆጶሳት" መካከል በቀድሞ ስማቸው አባ ንዋየ ሥላሴ አካሉ የይቅርታ ደብዳቤ በአስገቡ ሰዓት ነው፡፡
ፍምን እፍ ብት​ላት ትነ​ድ​ዳ​ለች፤ ትፍ ብት​ል​ባ​ትም ትጠ​ፋ​ለች፤ ሁለ​ቱም ከአ​ንድ አፍ ይወጣሉ።

ሐሜ​ተ​ኛ​ንና ሁለት አን​ደ​በት ያለ​ውን ሰው ይረ​ግ​ሙ​ታል፤ ብዙ ወዳ​ጆ​ችን አጋ​ድ​ሎ​አ​ልና። ነገረ ሠሪ አን​ደ​በት ብዙ ሰዎ​ችን አወ​ካ​ቸው፤ ከሕ​ዝ​ብም ወደ ሕዝብ አሳ​ደ​ዳ​ቸው። የጸኑ ከተ​ሞ​ች​ንም አፈ​ረሰ፤ የመ​ኳ​ን​ን​ቱ​ንም ቤት ጣለ። .…

ንብ​ረ​ት​ህን በእ​ሾህ ብታ​ጥር፥ ወር​ቅ​ህ​ንና ብር​ህ​ንም ብት​ቈ​ልፍ፥ ነገ​ር​ህን በሚ​ዛን ብት​መ​ዝን፥ ለአ​ፍ​ህም መዝ​ጊ​ያና ቍልፍ ብታ​ደ​ርግ፥ ዳግ​መ​ኛም በአ​ን​ደ​በ​ትህ እን​ዳ​ት​ሰ​ነ​ካ​ከል፥ በሚ​ያ​ድ​ን​ህም ፊት እን​ዳ​ት​ጥ​ልህ ተጠ​በቅ።
መጽ​ሐፈ ሲራክ 28:12 - 14 ,  24-26
አሁን:- "ፅኑዕ ነገር ከአፋችሁ አይውጣ፤ እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና።" 1 ሳሙ. 2:3። እናመስግን!!!

ገንቢና ወደፊት ተመልካች አስተያየቶችን ለማቅረብ አምላክ ይርዳን። ክርስትና ያለፈውን ትቶ የወደፊቱን መያዝ ነው። ላለፈው ሥርየት: ለሚመጣው ዕቅበት።

ያለፉና የተጎሳቆሉ ወንድሞቻችንን አንረሳም። ደማችሁን አፍርቷል። ሞታችሁ ተገፍኦአችሁ ቅዱስ ነው።

ቅር የተሰኘንባቸው አበው በሄዱበት መንገድ እንጅ እውነታቸውን አልካድንም። ክፍተት አለ። አንድነታችን ኅብረታችን ይሞላዋል። አሁንም ተመስገን።

የሰላም ልዑካን - peace agents እንሁን።

ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ማትያስ ይዕቀቦ እመዐተ ወልዳ። አባታችን፥ ስንት ጊዜ ወለዱን?!
✍️ በአማን ነጸረ
ጠላት ሲዋጋን የጦር መሳርያ ብቻ ሳይሆን ወቅትም ጭምር ነው መርጦ የተዋጋን ! ጠላት በደንብ አጥንቶ ያወቀን ይመስለኛል! ከወቅቶች ሁሉ መርጦ በጾም ወቅት ያውም በታላቁ በዓብይ ጾም ጦርነቱን አካሄደው ! ይህም ሃገሬውም ወታደሩም በሙሉ ጿሚ ስለሆነ በጾም የደከመ ወታደር ችሎ ቆሞ መዋጋት አይችልም ብለው አስበው ነው :: ሃገሬው ግን እንዲህ ነው :- 2ኛ ቆሮ 12:10 " ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና "

ዛሬም ጸላኤ ሠናይ ዲያብሎስ ከወቅቶች ሁሉ መርጦ እንደሚዋጋን ስንቶቻችን እናውቃለን ? ያውም ጦሩን በጾም ያበረታዋል !

ለኢጣልያ ስጋዊ ጦር አባቶችን እየጾሙ ታቦት ይዘው ከተዋጉ ከነፍስ ጠላት ዲያብሎስማ እንደምን ያለ ውግያ ይጠብቀን ይሆን ? ሊቁ እንደዚ ይላል :-

ወደ ኤፌሶን 6:12
"መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ"

ኦ ፍጡነ ረድኤት እምሩፀተ ነፋስ ወአውሎ ለዘይጼውአከ በተወክሎ
🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺
ጊዮርጊስ ቅረብ ለምህረት ወለተሣህሎ
ተወከፍ ወትረ ጸሎትየ ወቃለ ጽራሕየ ኩሎ
እስመ ልበ አምላክ ርኅሩኅ በኃቤከ ሃሎ!
🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺🌺

«ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ አንተን በመተማመን ለጠራህ ሁሉ ፈጥነህ ስትደርስለት ከአውሎ ነፋስ ይልቅ በተፋጠነ ሩጫ ነው እኮን፤ ጊዮርጊስ ሆይ የዘወትር ጸሎቴን የቃሌን የልመና ጩኽት ትቀበል ዘንድ ለይቅርታና ለምሕረትህ ፈጥነህ ወደ እኔ ቅረብ፤”

✍️ JohnD
በቅርቡ በተቋቋመው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮቿ እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዛሬ መጋቢት 17 2015 ዓ.ም የተሰጠ መግለጫ፦

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በተለያየ ዘመን በተነሱ ቅዱሳን ክርስትና እንዲሰበክ በማድረግ ለሺህ ዓመታት የሀገሪቱ የሃይማኖት፣ የታሪክ እና የሞራል ምንጭ ሆና ኖራለች፡፡

ቤተ ክርስቲያን ራሷ የሆነው ክርስቶስን በመስበክ ያላመኑትን ከማሳመን፣ ያመኑትን ከማፅናት እና የፀኑትን ከመቀደስ ውጪ ሌላ ምድራዊ ዓላማ ሳይኖራት ነገስታቱንም ሆነ ምዕመኑን እኩል ንስሀ አባት መድባ አና ንስሀ አቀብላ፣ ቀድሳ አቁርባ እና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ለሁሉም እኩል ፍትሃት አድርጋ የምትሸኝ ሰውን በፆታው፣ በቋንቋው፣ በነገዱ እና በማንነቱ አድሎ ሳታደርግ የኖረች ናት።

ሆኖም ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ውስጥ ያለአንዳች ማስረጃ የተፈጠሩ የሀሰት ትርክቶች እና እነዚህን ትርክቶች መሠረት ተደርገው በሰፊው ሲነዙ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ቤተ ክርስቲያንን ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡

አሁን አሁን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምእመናን በሃይማኖታቸው ብቻ ተለይተው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አካላት ካህናት አባቶቻችን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደሙን ቀድሰውና አክብረው ለሰዎች ድህነት ይሆኑ ዘንድ በተሰጣቸው ስልጣነ ክህነት ምእመናን ለርስት መንግሥተ ሰማያት የሚያበቁ ሁነው ሳለ በተለያዩ ጊዜ ለሞት እና ለእንግልት እንዲሁም ለስደት እና ለእስራት ሲዳረጉ ማዬት የእለት ተእለት ተግባር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡

በአዲሱ መንግስታዊ መዋቅራዊ አደረጃጀት በአዲስ አበባ ዙርያ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሸገር ከተማ በሜጢ ሆርሲሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን የነበሩት ቄስ አባይ መለሰ በመጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ከቅዳሴ ወጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲሄዱ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተፈጸመባቸው ድብደባ ሕይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን ተረድተናል፡፡

መንግሥት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ደህንነት የማስጠበቅ እና ዋስትና የመስጠት እንዲሁም ጭካኔ እና አረመኔያዊ ከሆኑ ጥቃቶች የመጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነት ሊኖርበት ይህንን ባለመወጣቱ ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ዜጎች በሕይወት የመኖር መብት በየእለቱ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ሀገረ ስብከታችን በቀሲስ አብይ መለስ ሞት የተሰማንን መሪር ኃዘን እየገለጽን የሚመለከተው የፌዴራል፤ የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና የፍትህ አካል ጉዳዩን ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን ምርምራ በማድረግ ይህንን አስነዋሪ እና ጭካኔ የተሞላበትን የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስር የሚተዳደሩ ቁጥራቸው ከዐሥራ ሦስት በላይ የሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በአዲሱ የከተማ ድንበር ማካለል ወደ ኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ክልል ውስጥ የተካለሉ ቢሆኑም ለዓመታት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገንብተው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ

፩ የኤርቱ ሞጀ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማፍረስ ተሞክሮ ከእነዚህ ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በመሉ በአፍራሽ ግብረ ሀይል እንዲፈርስ ከመደረጉም በላይ የፈረሰውን ቤተ ክርስቲያን በውስጡ ከሚገኙ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በሙሉ እንዲቃጠሉ እና እንዲወድሙ ተደርጓል፡፡

፪. በኤርቱ ሞጆ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አጥሩን ማፍረስ ተጀምሮ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ባደረጉት ርብርብ የማፍረስ : ሒደቱ ለጊዜው ቢቆምም አሁንም ይህን ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሸገር ከተማ ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ስለሆነም ለሀገር ባለውለታ የሆነችን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማሳደድ እና በማውደም ታሪካዊ መሠረቷን ለመናድ እና ከሌሎች ቤተ እምነቶች በመነጠል በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈጸመ ያለው አድሏዊ እና ኢ-ሕገ መንግስታዊ የሆነው ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ እያሳሰብን የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥትም የድርጊቱን ፈጻሚ አካላት ላይ ተገቢውን እርምት እንዲወስድ ስንል እንጠይቃለን፤

በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሚመለከተው ባለስልጣን አካል በየካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በገነተ ጽጌ ቅዱስጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን እና ሕገ ወጥ ተግባርን በተመለከተ የድርጊቱን ፈጻሚ አካላትን በ፭ ቀናት ጊዜ ውስጥ ተለይተው በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ለሕዝብ እንዲያሳጡት ጥሪ ያስተላለፈች ቢሆንም ይህ መግለጫ  አስከሚሰጥ ድረስ ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ተለይተው ተጠያቂ አለመሆናቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ነው፡፡

በመሆኑም መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ያቀረበችውን ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ ያልቻለ በመሆኑ የድርጊቱን መነሻ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ የተገባ መሆኑን እያሳወቅን ኮሚቴው የደረሰበትን ጥቅል መረጃ በአጭር ቀናት ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ሪፖርቱን የሚያቀርብ እና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ቤተ ክርስቲያንን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እና አጥፊዎችም ለድርጊታቸው ተገቢውን ሕጋዊ ቅጣት እንዲያገኙ እየሠራን መሆኑን እናሳውቃለን።

በመሆኑም፡

፩. መንግሥት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በመሆናቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ በመንገድ ላይ ተደብድበው ሕይወታቸው እንዲያልፍ የተደረጉት የቄስ ዐብይ መለሰ ገዳዮችን ተከታትሎ ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ችግሩን ከሥር ከመሠረቱ በመፍታት የአገልጋዮችንና የምእመናን መብት እንዲያስከብር

፪. በሸገር ከተማ አስተዳደር እየተፈፀመ ያለው አብያተ ክርስቲያናትን የማፍረስ ድርጊት በአስቸኴይ እንዲቆም እንዲደረግ፣

፫. የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ቦታ ተመላሽ እንዲያደርግ እና የፈረሰውን ቤተ ክርስቲያንም በራሱ ወጪ እንዲያሠራ እንዲደረግ እንጠይቃለን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን እና ምእመናት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባቶች ዘመነ ቤተ ክርስቲያንን በጉልበታችን፤ በዕውቀታችን እና በገንዘባችን የምናገለግልበት ብቻ ሳይሆን በአካላችን፣ በጤናችን እና በሕይወታችንም መስዋዕትነትን የምንከፍልበት የሰማዕትነት ዘመን ነው፡፡

ይህ የሰማዕትነት መከራም በሀገራችንና በየቤታችን እየመጣ ያለ የመከራ ዘመን በመሆኑ አብዝቶ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ፤ ሥጋችንን በጾም እና በስግደት በመግራት ከአባቶቻችሁ አባታዊ መመሪያ በመቀበል በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይባርክ ።
መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም                     
@sigewe
፩) ሴት ልጅ ወንዶች ባሉበት በዓውደ ምሕረት መዘመር አትችልም። ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በግልጽ ነግሮናል።  1ኛ ቆሮ. ፲፬፣ ፴፬ "ሴቶችም በቤተክርስቲያን ዝም ይበሉ። ሊታዘዙ እንጂ ሊናገሩ አልተፈቀደምና። ኦሪትም እንዲህ ብሏልና። ለሴት በቤተክርስቲያን መናገር ክልክል ነው" እንዲል። በተጨማሪም 1ኛ ጢሞ. 2፣11 "ሴት ግን በጸጥታ ትኑር እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ እንድትሰለጥን አንፈቅድም" እንዲል። የሙሴ እኅት ማርያም እንኳ በሴቶች መካከል ዘመረች ይላል እንጂ በወንዶች መካከል አልዘመረችም። ዘጸ. ፲፭፣፳ "የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጇ ወሰደች። ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዝማሬ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች" እንዲል። ሴት ሴቶችን ማስተማር ትችላለች። ቲቶ ፪፣፫ "ባልቴቶችም___በጎ የሆነውንም ትምህርት ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ለሴቶች ያስተምሩ" እንዲል። ሴቶች ዘማርያት ሆነው በዓውደ ምሕረት ሲዘምሩ ጳጳሱ ዝም ስላለ ልክ ነው አይባልም። ይህ በቸልተኝነት የመጣ ክፉ ልማድ ነው።
                            ።
ወደፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከፍትሐ ነገሥት፣ ከሥርዓት የተጣላ ትውልድ እንዳይፈጠር እሰጋለሁ። ምክንያቱም አሁን አሁን በተለይ ከ1900 ዓ. ም ወዲህ ብዙ ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያፈነገጡ ናቸው። ልምድ ሆነው ሰውም ዝም ብሏል። ክፉ ልማድ ሥር ሳይሰድ ካልነቀልነው የወደፊት ምእመናን ሃይማኖታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ያፈነገጠ እየመሰላቸው ይቸገራሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከፍትሐ ነገሥት የተጣሉ የልማድ ሰዎች ይሆኑብናል። በእርግጥ አንዳንድ ታላላቅ አድባራት ላይ አሁንም ቢሆን ሴቶች በዓውደ ምሕረት አይዘምሩም። ይህ በሁሉም ሊሆን ይገባል።
                                ።
፪) የጾም ሰዓት ከዐቢይ ጾም ውጭ ያሉት እስከ ፱ ሰዓት ይጾማሉ። ሰው ግን ጾሞ ግን 7 ሰዓት ላይ ይበላል። ከየት የመጣ ሥርዓት ነው ይሄ??? ጾሙን ሳይጨርሰው ገደፈኮ?። ይህ ሊስተካከል ይገባል።
                                ።
አንድ ቀን ቆማ ፋሲለደስ አቡነ እንድርያስ ዐቢይ ጾም ሊገባ ሲል ዘወረደ እስከ ፲፪ ሰዓት ይጾማል፣ ሰሙነ ሕማማት እስከ ምሽቱ ፩ ሰዓት ይጾማል። ከቅድስት እስከ ኒቆዲሞስ ዓርብ እስከ ፲፩ ሰዓት ይጾማል ብለው አስተማሩና እንኳን እውነቱን ነገርኳችሁ እንጂ ከዚህ በኋላ የራሳችሁ ውሳኔ ነው አሉ።
                                ።
እና ብዙ እውነታዎች አሉ። ያው መረር ቢላችሁም እውነታዋን መናገር ይሻላል። አንዳንዱ ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም ይልሀል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ካለመጠበቅ በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ አለ ?
#መጋቢት_27

#መድኃኔዓለም (#ጥንተ_ስቅለት)

መጋቢት ሃያ ሰባት በዚችም ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት በሥጋ ተሰቀለ። ፈጣሪዋ በዕንጨት መስቀል ላይ ተዘርግቶ ተሰቅሎ በአየችው ጊዜ ፀሐይ ጨለመች እርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣትን ለባዊት ነባቢት የሆነች ነፍሱን ከሥጋው ለያት ሐዋርያ ጴጥሮስ በሥጋ ምውት ሲሆን በመለኮት ሕያው ነው እንዳለ ነፍሱ ከመለኮት ሳትለይ ከሥጋ ተለየች በዚያ ጊዜ ሥጋ ከመለኮት ሳትለይ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር። እንዲሁም ነፍስ ከመለኮት ጋራ አንድ ሁና እሥረኞች ነፍሳትን ትፈታቸው ዘንድ ወደሲኦል ወረደች።

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለ ዓለም ሁሉ ድኅነት በሥጋ ተሰቅሏልና ሞቱን በአንክሮ እናዘክር ዘንድ የልቡናችን ዐይን ወደ ቀራንዮ እናንሳ! እነሆ ክፉዎች አይሁድ ሰይጣን ልባቸውን አስቶታልና እንደ ወረንጦና እንደ ወስፌ እንደመርፌም ያለ 300 እሾህ ያለው ስረወጽ አድርገው አክሊል ሠርተው ከፍላት አግብተው በጉጠት አንስተው ‹ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሥ ነህ ዘውድ ይገባሃል› ብለው በራሱ ላይ ደፉበት፡፡ ለአክሊለ ሦኩም 73 ስቁረት ነበረው፡፡ እራሳቸው እንደ መሮ፣ ወርዳቸው እንደ ሞረድ 4 ማዕዘን አሠርተው ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር፣ ስለታቸውን እንደ ወስፌ አድርገው 73 ችንካር ሠርተው በ73ቱ ስቁረት አግብተው በጌታችን በራሱ ላይ ቢመቱበት ሥጋ ለሥጋ ገብቶ መሐል ልቡን ወጋው፡፡ አክሊለ ሦኩን በራሱ ላይ አድርገው ሲያበቁ ከቤት ወደ አደባባይ እያመላለሱ ‹‹ንጉሥ ሆይ!...›› እያሉ ምራቃቸውን እየተፉበት ተዘባበቱበት፡፡ መስቀል አሸክመው ከሊቶስጥራ እስከ ቀራኒዮ ድረስ እያዳፉ ሲወስዱት 136 ጊዜ በምድር ላይ ጣሉት፡፡ ከኋላ ያሉት ‹‹ፍጠን›› እያሉ ገፍትረው ይጥሉታል፣ ከፊት ያሉት ደግሞ ‹‹ምን ያስቸኩልሃል?›› እያሉ መልሰው ገፍትረው ይጥሉታል፡፡ ከዚህ በኋላ ክፉዎች አይሁድ ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር ስለታቸው ደግሞ እንደ ወስፌ የሆኑ 5 ችንካሮችን ሠርተው ሳዶር በሚባለው ችንካር ቀኝ እጁን፣ በአላዶር ግራ እጁን፣ በዳናት ሁለት እግሮቹን፣ በአዴራ መሐል ልቡንና በሮዳስ ደረቱን ቸንክረው የአዳም ራስ ቅል ባለበት ቀራኒዮ አደባባይ ላይ ሰቅለውታል፡፡

ክፉዎች አይሁድ መድኃኔዓለም ክርስቶስን እንደያዙት የኋሊት አስረው አፍንጫውን 25 ጊዜ ቢመቱት ደሙ በመሬት ላይ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከጌቴሴማኒ እስከ ሐና ቤት ድረስ አስረው የፊተኞቹ ሲጎትቱት የኋለኞቹ እየለቀቁት የኋለኞቹም በተራቸው ሲጎትቱት የፊተኞቹ ይለቁታል፡፤ እንዲህ እያደረጉ 65 ጊዜ ከመሬት ጋር አጋጭተውታል፡፡ ሳውል በእግሩ ሲረግጠው ጌታችን ‹‹መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?›› ቢለው ስለዚህ ንግግርህ ብሎ ሳውል 440 ጊዜ አስገረፈው፡፡

ክፉዎች አይሁድ መድኃኒታችንን በሁለት ግንዶች መካከል አድርገው 65 ጊዜ ከግንዱ ጋር አጋጩት፡፡ ቀያፋ በሚመረምረው ጊዜ ጌታችን ‹‹አምላነቴን አንተው ራስህ ተናገርኽ›› ቢለው አይሁድ በእጃቸው ሲመቱት እጃቸውን ቢያማቸው ድንጋይ ጨብጠው 120 ጊዜ ፊቱን ጸፉት፡፡ አይሁድ ወደ ጲላጦስ ዘንድ ሲወስዱት ‹‹ምናልባት ጲላጦስ ባይፈርድበት እንኳ እንዳይቆጨን›› ብለው 305 ጊዜ በሽመል ደብድበውታል፡፡ በአምላክነቱ ቻለው እንጂ የአንዱ ምት ብቻ በገደለው ነበር፡፡ በርባን የይሁዳ የሚስቱ ወንድም (አማቹ) ስለነበር እርሱ እንደፊታለትም ከዋጋው ከ30ው ብር ጋር አብሮ ተደራድሮበት ነበር፡፡
ሰይጣን ልባቸውን ለክፋት ያስጨከናቸው ክፉዎች አይሁድ በጲላጦስ አደባባይ የጌታችንን ፂሙን 80 ጊዜ ነጭተውታል፡፡ ጲላጦስ እንደ ሕጋቸው 41 ብቻ ገርፈው እንዲለቁት ቢያዝም ክፉዎች አይሁድ ግን ጌታችንን ሲገርፉት ‹‹አሠቃቂ ግርፋቱን አይተን ልባችን እንዳይራራ›› ብለው ሰንጠረዥ ገበጣ ሰርተው ሲጫወቱ አንዱ ተነስቶ እስከ 60 እና 70 ድረስ ይገርፍና ሲደክመው ‹‹ቆጠራችሁን?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹አልቆጠርንም›› ሲሉት ከድካሙ የተነሣ ‹‹እኔው ልግረፍ እንደገና እኔው ልቁጠር›› ብሎ ትቶት ሲቀመጥ ሌላኛው ይነሣና እንደዛኛው ሁሉ በተራው 60 እና 70 ይገርፈዋል፡፡ ሁሉም እንዲህ እያሳሳቱ የራሳቸውን ሕግ እየተላለፉ አይሁድ ጌታችንን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እንደበረዶ ነጭ ሆኖ እስኪታይ ድረስ 6666 ጊዜ ጽኑ ግርፋትን ገረፉት፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግርፋቱ ወቅት 366 ጊዜ ሥጋው ተቆርሶ መሬት ላይ ወድቋል፡፡

የመድኃኔዓለም ወገኖች ሆይ! የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ መሆኑንና የትዕግሥቱን ብዛት አይተን እናደንቅ ዘንድ ከመጻሕፍት ጠቅሰን እንነግራችኋለን፡፡ አይሁድ ጌታችን አብርሃም ሳይወለድ በፊት እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን አምላክ መሆኑን ቢነግራቸው ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፡፡ እሱ ግን ጊዜው ገና ነበርና ተሰውሮአቸው በመካከላቸው አልፎ ሲሄድ በፍጹም አላዩትም ነበር፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም:- ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም:- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡›› ዮሐ 8፡56-59፡፡

ዳግመኛም በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው አይሁድ መድኃኔዓለምን ሊይዙት የጦር መሣሪያቸውን ሰብስበው ወደ ጌቴሴማኒ በመጡ ጊዜ ‹‹ማንን ትፈለጋላችሁ?›› ቢላቸው ‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ›› ቢላቸው ከአንደበቱ የወጣውን መለኮታዊ ቃል ብቻ መቋቋም አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀው ተዘርረዋል፡፡ ይህም ክስተት በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል ላይ ምዕራፍ 18 ከቁጥር አንድ ጀምሮ ይመለከቷል፡፡) እናም የጌታችን ሞቱ በፍጹም ፈቃዱ ባይሆን ኖሮ በጌቴሴማኒ ሊይዙት የመጡት ክፉዎች አይሁድን እንደመጀመሪያው ሁሉ በተሠወራቸው ነበር አሊያም ከአንደበቱ በሚወጣው አምላካዊ ቃሉ ብቻ ባጠፋቸው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችን ወደዚህች ምድር የመጣበትን ዓላማ ይፈጽም ዘንድ እንዲገድሉት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ቢሰጣቸው ያን ሁሉ እጅግ አሠቃቂ መከራ አደረሱበትና ለመስቀል ሞት አበቁት፡፡

ወዮ ለዚህ ለመድኃኒዓለም ፍጹም ትዕግስት አንክሮ ይገባል! ዓለምን በመዳፉ የያዘ አምላክ በአይሁድ እጅ እንደሌባ ተያዘ፡፡ ሠራዊተ መላእክት ለምሥጋና በፊቱ የሚቆሙለት መድኃኔዓለም እርሱ ሊፈረድበት በፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡ በእስራት ያሉትን የሚፈታ እርሱ በብረት ችንካር ተቸነከረ፡፡ ሰማይን በከዋክብት ምድርም በአበባ ያስጌጠ እርሱ ግን የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፡፡ ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብ እርሱ ተጠማሁ አለ፡፡ ወዮ የመድኃኔዓለም የማዳኑ ምሥጢር ምንኛ ድንቅ ነው!!! ለዚህ ባሕርይው አንክሮ ይገባል፡፡

በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞት በአንድነት እናለቅስ ዘንድ ቅዱሳን ሁላችሁ ኑ! መድኃኒታችን ሙቷልና ፍጥረታት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ መያዝንና መታሠርን የተቀበለ መድኃኒታችን ሙቷልና፡፡ ጥፊንና ግርፋትን የተቀበለ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ መደብደብንና መመታትን የታገሰ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ ሄኖክ እግዚአብሔር ‹‹በሴም ቤት ይደር›› ብሎ አብ ስለራሱ የተናገረለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አብርሃም ቃልኪዳን የገባልህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ይስሐቅ ከሰይፍ ቤዛ የሆነህን
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ያዕቆብ በበረሃ የታገለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮብ በደመና የታየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሙሴ ስለ እርሱ ‹እንደእኔ ያለ ነቢይ ይነሣል› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳዊት ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ በበረሃ ዛፍም አገኘነው›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤርሚያስ ‹‹የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበሉ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ኢሳይያስ ‹‹ወልድ ሰው ለመሆን ተገለጠልን፣ ሕፃን ተወለደልን፣ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ›› ብለህ የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅኤል ‹‹አምላክ ወደ ተዘጋች ደጃፍ ገባ፣ ከተዘጋች በርም ወጣ›› ብለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳንኤል ነጭ ሐር ለብሶ ያየኸውን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤልያስ ከሞት በፊት የሰወረህ በእሳት ፈረሶች ያሳረገህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅያስ የፀሐይ መግባቱን ያሳየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ምናሴ ችንካሮችህን ከእግር ብረት የፈታ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኢዮስያስ ፋሲካውን ያደረግህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ከእሳት ምድጃ ያዳናች የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አብያና ሲላ ፌንቶስ ከመወለዱ አስቀድሞ ያመናችሁበት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ የቀድሞ አባቶች ነቢያት ሁላችሁ ከፋራን ተራራና ከቴማን ይመጣል ያላችሁት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አሞፅ በአድማስ ቅጥር ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዘካርያስ በተራራዎች መካከል ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዕዝራ በአርፋድ በረሃ ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ስምዖን በክንድህ የታቀፍከውን ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዮሴፍ እንደ አንተ የተሸጠ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ጠራቢ ዮሴፍ በትከሻህ ያዘልከው በክንድህ የተሸከምከው ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከሕፃንነትህ ጀምሮ በበረሃ ያለ እናት ያለ አባት ያሳደገህ መንገዱንም እንድትጠርግለት ያዘጋጀህና መለኮትን እንድታጠምቅ የመረጠህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡

ኢያቄምና ሐና ሆይ የልጃችሁን ልቅሶዋን የልቧንም መዘንጋት ታዩ ዘንድ ኑ፡፡ ከሔዋን እስከ ፋኑኤል ልጅ እስከ ሐና ያላችሁ ሁላችሁ ቅዱሳት ሴቶች የድንግልን ልቅሶዋን ታዩ ዘንድ ኑ፣ አንድ ልጇ ሙቷልና፡፡ የለመለመ የሥጋ ሞት ሕንፃ የተጀመረበት የአቤል ተከታዩ፣ ከጎኑ የፈሰሰው ደም ሔዋንን ከጥፋት ያዳናት የተገደለ መድኃኒታችን ነው፡፡ የናቡቴ ጓደኛው የተገፋው መድኃኒታችን ነው፡፡ አቤል ስለሚስቱ ሞተ፡፡ ናቡቴም ስለ ወይኑ ቦታ ሞተ፡፡ መድኃኒታችን ግን በቀኙ ያነጻት ዘንድ ስለቤተክርስቲያን ሞተ፡፡ ነፍሳችሁን ይወስዷታልና መውረዱንም አላወቁምና ስለ ወገኖቹ ኃጢአት እስከ ሞት ደረሰ ብሎ ስለ እርሱ የተናገረ አባቱን እንስማው፡፡ ሙሴም እርሱን ያውቁት ዘንድ አላሰቡትም፣ በሚመጣበት ቀንም አላወቁትም አለ፡፡ ዕዝራ በባሕር ጥልቅ ያለውን ማወቅ እንዳይችሉ ወልድንም ማወቅ እንዲሁ ሆነባቸው አለ፡፡ ጳውሎስም ብታውቁትስ ኖሮ የክብርን ጌታ እግዚአብሔርን ባልሰቀላችሁት ነበር አለ፡፡

በመሰደድ፣ ያለምንም በደልም በፍርድ አደባባይ በመቆም መከራ መስቀልን በመሸከም አብነት የሆናችሁ ሰማዕታት ሁላችሁ ኑ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት አስባችሁ በጋራ አልቅሱለት፡፡ ሁሉ የእርሱ ከእርሱ ለእርሱ ተፈጥሮ ሳለ በምድር ላይ ምንም ሳይኖረው ራሱን እንኳን የሚያስጠጋበት ቤት ሳይኖረው አብነት የሆናችሁ ባሕታውያንና መነኮሳት ሁላችሁ ኑ በዛሬዋ ዕለት ስለሞተው አምላካችሁ መሪር ዕንባን አልቅሱለት፡፡ ሕግ ጠብቆ፣ ሥርዓት አክብሮ፣ ነዳያንን በመመገብና ያዘኑትን በማጽናናት 33 ዓመት በምድር ላይ ኖሮ አብነት የሆናችሁ እናንት በዓለም ሆናችሁ ሕግ ጠብቃችሁ፣ አሥራት በኩራቱን አውጥታችሁ፣ ድሆችን በመርዳት የምትኖሩ ክርስቲያኖች ሁላችሁ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት ታስቡ ኑ፡፡

‹‹የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና›› ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደጻፈልን (1ኛ ጴጥ 2፡21) እርሱ ንጹሕ ባሕርይ ሲሆን ወደ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ ለተጠመቅን ለእኛ ለተነሣሕያን ለሁላችን አብነት የሆነን መድኃኒታችን ስለእኛ ሞቷልና ሞቱን እናስብ ዘንድ ኑ በቤቱ ተሰብስበን እናልቅስለት፡፡ መታሰያውንም እናድርግለት፡፡ ጌታችን ሞቶ ተቀብሮ ካረገ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳን አባቶቻችን ለእነ አቡነ መባዓ ጽዮን፣ ለእነ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደነገራቸው የሞቱን መታሰቢያ የሚያደርግ ኃጠአተኛ እንኳ ቢሆን ሲኦልን አያያትም፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ ቢኖር ሲኦል ራሷ አፍ አውጥታ ‹‹ይህችን ነፍስ ወደኔ አታምጡብኝ›› ብላ ትጮሃለች እንጂ ችላ አትቀበለውም፡፡

የጌታችን ወዳጆቹ ዮሴፍ ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታና በመቶ ወቄት ሽቱ ገንዘው በሐዲስ መቃብር ሊቀብሩት ቢሉ ጌታችን ያን ጊዜ ዐይኑን ክፍቶ ‹‹በሰውነቴ መዋቲ ብሆን በመለኮቴ ሕያው ነኝ እንጂ ምነው እንደ እሩቅ ብእሲ ዝም ብላችሁ ትገንዙኛላችሁን?›› አላቸው፡፡ ይህን ጊዜም ዮሴፍ ኒቆዲሞስ በታላቅ ድንዳጤ ሆነው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ! እንግዲያስ ምን እያልን እንገንዝህ?›› አሉት፡፡ መድኃኒታችንም እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ አላቸው፡- ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦ› እያላችሁ ገንዛችሁ ቅበሩኝ አላቸው፡፡›› ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለወዳጆቹ ለ12ቱ ሐዋርያት፣ ለ72ቱ አርድእት፣ ለ36ቱ ቅዱሳት አንስት ‹‹እስከ ሦስት ቀን እነሣላችኋለሁ እዘኑ አልቅሱ፣ እህል ውኃ አትቅመሱ በሏቸው›› ብሎ ለዮሴፍና ለኒቆዲሞስ አክፍሎት አስተማራቸው፡፡

ዳግመኛም መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከዕርገቱ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሞቱን መታሰቢያ እንዲያደርጉ ነግሯቸዋልና፡፡ ሕማሙንና ሞቱንም እንዲዘክሩ አዟቸዋልና አሁንም ያንን ሁሉ የመድኃኔዓለምን ሞቱን ያላሰበና የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያላከበረና እርሱንም የማይወደው ቢኖር ዕድል ፈንታው ጽዋ ተርታው ከአይሁድ ጋር ነው፡፡

የአምላካችንን የመድኃኔዓለምን ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባብረን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ ለመተባበር ያብቃን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት እና #ከገድላት_አንደበት)
2025/07/01 11:29:14
Back to Top
HTML Embed Code: