Telegram Web
ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
አድዋ፦ ሶስተኛው ፍልስፍናዊ  አብዮት !!!!! ** #Repost <<አድዋ ሶስተኛውን ፍልስፍናዊ አብዮት ትወክላለች፡፡ በጥቂቱ ርእሰነገሩን ለማስረዳት ያህል፣ በአለም ላይ ሶስት ፍልስፍናዊ አብዮቶች አሉ፡፡ ስለመልካም ግብ ግህደት (እውንነት) የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ ያደረጉ፣ በእግሩ የቆመውን በሙሉ በጭንቅላቱ የተከሉ፣ የውስጡን ወደውጪ የገለበጡ፣ተደብቆ የነበረውን ሁለንተና ሀቅ ነጻ ያወጡ እሳቤያዊ…
እኛ ግን ለመላው ጥቁር ሕዝብ ትርክት ቀማሪነት የታጨን ሆነን ሳለን የራሳችን የቤት ሥራ እንኳን ሰርተን ያልጨረስን መሳቂያ የመሆናችን ነገር ያሳዝናል፡፡

ታሪካችንን አላወቅነውም፡፡ መናናቂያ አድርግነዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን በሰው ዘርን ሁሉ ፊት በግርማ ሊያስጠራን የሚችል ዕድል እንደዘበት አምልጦናል፡፡ እናስ ያቆሙን መሰረቶች ምን ያህል ጽኑዓን ነበሩ? እንደ ኅብረተሰብ የአቋራጭ ልክፍተኞች ሆነን ለመገኘታችን ምክንያቱ ምንድን ነው? የምንዋቀሰው፣ የምንናናቀው በድንቁርናችን ልክ አይደለምን? ለፍጥረት ሁሉ ከሚተርፍ በረከት፣ ኅሊና እና ርህራሄ ጋር ተፈጥረን ሳለን ዘመኑን ስላለመዋጀታችን ምክንያቱ ምንድነው?

በሰንደቅ ዓላማ ለሚያስለምን ችጋር ራሳችንን አላጨንምን?
በአለም ላይ ከየትኛው ሀገር ህዝብ በላይ ረሀብ ፣ስድት፣ መፈናቀል፤ የእርስ በርስ ጦርነት አላስተናገድምን?

ደሞስ የሚያስተባብረን አንድ የሆነ ዓይነት ቁጭት ለማግኘት ከነበረን የጥቁር ሕዝብ አለኝታነት ማማ ከመፈጥፈጥ፣ በሰንደቅዓላማ ከመለመን በላይ ሌላ ምን ውርደት ያስፈልገናል?

ያዕቆብ ብርሀኑ

@zephilosophy
"የማህበረሰብ ኮንትራት"
ሆብስ

ራስህን በዋሻ የሚኖር የጥንት ስው አድርገህ አስበው፡፡ በየለቱ ሚዳቋ በማደንህም ፊትህ በደስታ ተሞልቶ ወደ ልጆችህ እና ወደ ሚስትህ ትመለሳለህ፡፡ ሕይወትህን በእንዲህ አይነት ሁኔታ እየመራህ ሳለ፤ አንድ ቀን በመንገድህ ላይ ካንተ የገዘፈ ሰው ያጋጥምሃል፡፡

"ርቦኛል ካደንካት ሚዳቋ ጥቂት አምጣ" ይልሃል... ትደነግጣለህ፤ ፍዳህን አይተህ ነው ይህቺን ሚዳቋ ያደንካት።
"ለምን?" አልከው፡፡

"አንተን እና ቤተሰቦችህን ከሌላ ጉልበተኞች እጠብቃለሁ አንተም ምግብ ትሰጠኛለህ"

ሆብስ ይህን "#የማህበረሰብ_ኮንትራት" ሲል ይጠራዋል፡፡ አሁን ላይም መንግስት ብለን የምንጠራው ተቋም የተወለደው በዚህ መንገድ ነው፡፡

መንግስታት ከመመስረቱ በፊት ያለው የሰው ልጆች ሕይወት እጅግ አስፈሪ እና አዳጋች ነበር፡፡ ሰውም ከመጥፎነት የሚጋርደው ኃይል ከሌለው እና ያሻውን እንዲያደርግ ከተለቀቀ፣ ለፍቶ ከመብላት መስረቅን ያስቀድማል፡፡

ደህንነቱ ባልተጠበቀ ቦታ ላይ መኖር አስቸጋሪ ነውና፣ ሰዎች እንደ ማህበር የሚጠብቃቸውን እና ከግለሰቦች በላይ ኃይል ያለውን አካል ከመሃላቸው ይሾማሉ፡፡ አዎን መንግስት ካለ፣ ልክ እንደ ሌሎች እንስሳዎች ሁሉ ደስ እንዳለን የመስረቅም ሆነ የመገዳደል ነጻነት አይኖረንም፤ ሆኖም ንብረታችን እና ደህንነታችን እንዲጠበቅ ያደርግልናል። ሆብስ ይህ ነጻነት እና ምቾትን ይሰጠናል ይለናል ለምሳሌ ስራ መስራት ስንፈልግ ቤታችንን ዘግተን መውጣት እንችላለን፤ ለሰራነው ስራም በእርግጠኝነት ደሞዝ እንደምንቀበል እናምናለን፡፡ ይህም እንድናድግ ይረዳናል፡፡

“የማህበረሰብ ኮንትራት” በማህበሩ አካል በሆኑ ሰዎች መሃል የሚፈረም ስምምነት ነው፡፡ በፊርማችንም ከነጻነታችን እንደምንሰጥ ቃል እንገባለን፤ በሰጠነውም ነጻነት ልክ ደህንነትን እና ምቾትን እናገኛለን፡፡ የብዙሃን ድምጽም ከግለሰቦች ድምጽ በላይ ይሰማል።

የመንግስት የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ከልማት፣ከዲሞክራሲ እና ከሁሉም ጥያቄዎች ቅድሚያ የሚሰጠው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

ሆብስ መንግስት ቢያስከፋንም ትዕዛዙን አልቀበልም ብለን ማመጽ አንችልም ይለናል፡፡ ምክንያቱም ለእኛ ባይመቸን እንኳ ለብዙዎች ልክ ነውና፤ ይህንን ኮንትራት መቅደድ የለብንም፡፡ በአንጻሩ ጆን ሎክ እና ዣን ዣክ ሩሶ ይህን የማህበረሰብ ኮንትራት ቀድሞውኑ መንግስት ካፈረሰው  ህዝቦች አመጻን ማስነሳት አለባቸው ይሉናል፡፡

አንተ እና መንግስትህ ስለምን ነገሮች ተፈራርማችኋል? መቼ ነው መንግስትህ ቃሉን የሚያፈርሰው? መቼስ ነው ማመጽ ያለብህ?

✍️ፍሉይ አለም

@zephilosophy
እግዚአብሔር ለማይወደው ህዝብ የምጨነቀው ለምንድነው?
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ዎልፍ ጋንግ ገፀባህርይ ነው። ደራሲ ቤተማሪያም ተሾመ 3ኛ ቤተ-መቅደስ በሚለው መፅሐፉ ላይ የፈጠረው ምናባዊ ገፀባህርይ

ዎልፍ ጋንግ በ77 ረሃብ ወቅት ሐገራችንን ለመርዳት ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ መጣ። የአንድ ግብረሰናይ ድርጅት አባል በመሆን በትጋራይ ያሉ ዜጎችን ሲረዳ ቆይቶ ከህብረተሰቡ ጋር ተላመደ። ትግረኛ ለመደ፥ ጠላ እና ዶሮ ወጥ ወደደ።
ትርሃስ የተባሉ እናት ደግሞ ጀርመናዊውን እንደ ቤተሰብ አቀረቡት።

ከእለታት በአንዱ፥ የደርግ አየር ሀይል ጥቃት ሲሰነዝር ብዙሃኑ ወደ ሞት ተነዱ። የእርስ በእርስ ጦርነት ወለድ ጥቃቱ በመደዳ ብዙዎችን ገደለ። እናት ትርሃስ ከሟቾች መካከል ነበረች።
ዎልፍ እየተሯሯጠ ቁስለኞችን ሲያግዝ የትርሃስን በድን አገኘ። የ እማማ ትርሃሰ በድን ከህፃን ልጃቸው አስክሬን ጋር ተቃቅፎ ተጋድሟል።

ድጋፍ ለማድረግ የመጣው ዎልፍ ጋንግ ሀዘን መታው። በሀዘን ውስጥ ሆኖ "እግዚአብሔር ያላዘነለትን ህዝብ እኔ ምን አባቴ ልፈጥርለት ነው?" አለ።

ይህ ታሪክ በቤተማሪያም የልብወለድ መፅሐፍ ውስጥ ያለ ነው። ታሪኩ ምናብ ወለድ ቢሆንም ወደ እውነት የሚንጠራራ ነው።

በታሪክ አጋጣሚ እንደ ህዝብ ብዙ መከራ ተፈራርቆብናል። ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር እንሸጋገራለን። የሰላም ፋታ ሳናገኝ ወደ ጦርነት እንገባለን።
አያቶቻችን ላይ የወረደው የመከራ ዝናብ በእኛም ላይ ወርዷል። አባቶቻችንን የነረተ የችጋር ቡጢ እኛንም ነርቶናል። ከሰቆቃ ወደ ሌላ ሰቆቃ ስንሸጋገር ኖረናል።

የሆነብን ሁሉ እግዘብሔርን ሊራራልን ስላልወደደ እስኪመስል ድረስ መራር ነው። ዛሬም የትላንቱን በሚመስል ጭንቅ ውስጥ ነን።

እስከአሁን ከመለኮት አለም መፍትሄ ስንፈልግ ኖረናል። ፖለቲካ ወለድ ችግራችንን እግዚአብሔር እንዲፈታልን ስንሻ ነበርን። ምናልባት መፍትሄ የምናገኘው የመፍትሔ ፍለጋ መንገዳችንን በመቀየር ቢሆንስ?

ያ እስኪሆን ድረስ ግን ዎልፍ ጋንግ እንዳለው 'እግዚአብሔር ያላዘነለት ህዝብ' እንመስላለን።


@Tfanos
ከከፍታ ምሳሌነት ወደ የኋላቀርነት ማሳያነት ለምን ተቀየርን?

ታሪክን ከእኛ ጋር አያይዤ ሳስብ ያለፉ ኹነቶቹን ምርኩዝ አድርገን ኢትዮጵያኖች "ትልቅ የነበረን ሕዝቦች ነን" የሚል ጥቅስ በየልባችን ሰንቀን፣ ጀርባችን ላይ በሚሰማን ሙቀት አማካኝነት ያለንበትን ኹኔታ እየለካን “ደህና ነን " እያልን የምንኖር መሆናችን አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለዛሬ ጉድለታችን፣ ለአሁን ክፍተቶቻችን፣ ለስንፍናችን ሰበብ ፍለጋ ከአጽም ጋር ትግል ላይ መክረማችንም ይደንቀኛል፡፡

ቀዳሚ እንጂ ተከታይ ተሸናፊ ሳይሆን አሸናፊ እንደነበረን የቀደምት ስልጣኔዎቻችንን ምስክር ናቸው፡፡ ታዲያ ከቀዳሚነት ወደ ተከታይነት ፤ከክብር ወደ ውርደት፤ ከከፍታ ምሳሌነት ወደ የኋላቀርነት ማሳያ መቼ?፣ ለምን? እና እንዴት? ተሻጋገርን የሚለውን ለማወቅ  ታሪካችንን መመርመር ያስፈልጋል። ሌላው ቢቀር ታሪክን በመፈተሸ ለውጥ በማስተናገድ ሂደት ላይ የሚፈጠሩ መሰናክሎችን መቀነስ ይችላል፡፡

ዛሬ ሙሉ ሰውነታችን በድህንነት፣ በአስተሳሰብ ልልነት፣ የሚበጀንን ስልጣኔ በማጣት ቆሻሻ ታወሯል። ይህን ቆሻሻ የአመክንዮ እንዶድ በመቀንጠስ፣ ከሳይንስና ከጥበብ ወንዝ መመራመርንና መጠየቅን በመጭለፍ እንደመጽዳት ፋንታ በተቃራኒው እኛ እያደረግን ያለነው በአንድ እጃችን የድህንነት እከካችንን እያከክን፣ በሌላኛው ደግሞ ላለንበት ኹኔታ ምክንያት ናቸው ወደ ምንላቸው እየጠቆምን ጊዜያችንን በመንቀፍ እና በመተቻቸት መፍጀት ነው።

አሁን ላይ ላለንበት ኹኔታ ሰበብ ፍለጋ ከቅርጫታችን ውጪ በሚገኙ አካላት ላይ ጣት የመቀሰር አባዜ ማብቃት አለበት፡፡ ማውገዝ አለብንም ከተባለና ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ገዢዎችን፣ ለሆዳቸው ያደሩትን የማኅበረሰብ ወኪሎቻችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ነው (ኹሉም ባይሆኑም ውሉ)፡፡ በየትውልዱ ብቅ ለማለት ድፍረት ያገኙትን እና ሊያነቁን የሞከሩቱን ሲያሳድዱ፣ ሲያስሩ እና ሲገድሉ እንደነበር ስለ ታሪካችን የሚናገሩትን መጽሐፍት ይነግሩናል። ኾኖም እነሱንም ቢሆኑ የሰሩት ስህተት ዳግም እንዳይከሰት ለመማሪያነት ካልተገለገልንበት በስተቀር ስማቸውን እየጠራን መቆዘሙና የጥፋተኝነት ካባ እያከናነቡ መሰንበቱ ምኑም አይጠቀመንም! መወጋገዝን ካመጣን አይቀር ራሳችንንም እናውግዝ፤ የማይጠቅሙ ባህሎችን መርምሮ ጥቅም ጉዳቱን ሊነግረን ላይ ታች የሚል አንቂዎቻችንን ያልሆነ ስም ሰጥተናልና፤ ልፋታቸውን መና ማድረግን የጀግንነት መስፍርት አድርገን አስቀመጠናልና!

ኢትዮጵያውያን አሁን ላለንበት ማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች ምን ይሆኑ ብዬ ብጠየቅ "ባይመችን እንኳን ተቀመጡ ባሉን ቦታ ላይ ቦታ ከመቀየር ይልቅ መቀመጫችንን እያታከክን ለመኖር በመመርጣችን ነው" ብዬ አስቀድሜ እመልሳለሁ፡፡ ዛሬም ድረስ የተቀመጥንበት ቦታ እንደቆረቆረን ብንገኝም ማን እንዳስቀመጠን እና ለምን እንደተቀመጥን አልጠየቅንም፡፡ ባይሆን መቀመጫችንን ከቦታው ጋር ለማለማመድ ጊዜና ጉልበታችንን እናባክናለን። ግና አሁንም ቢኾን አረፈደምና እንጠይቅ። ካልሆነ ግን ከድጡ ወደ ማጡ መንሸራተታችን አይቀርልንም(መንሸራተቱንማ ከጀመረን ቆይተናል፡፡)

ሌላኛው ምክንያት ብዬ የማስቀምጠው 'የሀገራችን ልክ ያልሆነና ወደ ኋላ ጎታች የሆነ ማኅበረሰባዊና ፓለቲካዊ ሥርዓት ጠልቆና ጠንክሮ በሀገራችን በመገንባቱ ነው' የሚል ነው፡፡ ይህ ሥርዓት  የሕዝብን ጊዜያዊ ስሜት በመኰርኰር የተካኑ ብልጣ-ብልጥ አላዋቂ ብሔርተኞችንና ጥቅመኞችን ንጉስ አድርጎ የሚያሾም ፤ በየዘመኑ ያሉብንን ችግሮች በመለየት ያሳዩንን፣ወደ ኋሊት እየተጓዝን መሆኑን በማስመልከት ሊያነቁን የሞከሩትን  አገርና ሕዝብ ወዳዶችን ደግሞ የበዪ ተመልካች የሚያደረግ ነው።

ትልቁ ችግራችን በርካታ ነገሮችን ሳንመረምር፣ ሳንፈትሽ እና ሳንጠይቅ እንደተነገረን የምንቀበል መሆናችን ነው።ብዙዎቻችን ስለ አንድ ነገር የሚኖረን ድምዳሜ አሊያም “እውነታው' ተብሎ የሚነገረንን ሐሳብ ለመፈተሽና ለመፈተን ጥረቱና ድፍረቱ የለንም።፡ በቸልተኝነት አውሎ ንፋስ የተወሰድን፣ ከፍርሃት ጥላ ገለል ማለት የተሳነን ሆነናል። አጎንብስ ስንባል እሺ፣ ተቀመጥ የሚል ቃል ስንሰማ ዝፍዝፍ፣ ሩጥ የሚል ድምጽ ስንሰማ ፈርጣጭ ሆነናል።

መፅሀፍ - ጥያቄዎቹ
ደራሲ- ፍሬው ማሩፍ

@zephilosophy
@zephilosophy
የጠየቁ ተሻግረው አሻገሩን

ስንቱ ይሁን የፖሟ ፍሬ ስትወድቅ እየተመለከተ “ለምን? እና እንዴት? ሳይል ያለፈ! አንድ ሰው ግን ጠየቀ፤ አይዛክ ኒውተን፡፡ ኒውተን አእምሮቸውን በተገቢው ተጠቅመው ማለትም ማወቅን ሽተው፣ ያወቁትንም ለወግ አብቅተውና ለማዕረግ አድርሰው ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ከተረፉት መካከል በምሳሌነት ሊነሳ የሚችል ግለሰብ ነው። ይህ ሳይንቲስት “በምን ምክንያት?፣ ከምን የተነሳ?' ብሎ፤ በመጠየቅ መንገድ ተጉዞ ምላሾችን ፈለገና ስለ መሬት ስበት እንዲገባን አደረገን። የፍጥነት እና የኃይል ምጥነት እንዲሁም የአድራጊ እና ተደራጊ እኩልነት ሕጎችን አጥንቶ ሚስጥራትን ገለጠልን። ይህን ማድረግ የቻለው አእምሮን በሚገባ ለመጠቀም ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል የብልህ ምርጫ የሆነውን መጠየቅን በመምረጡ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ይህን መንገድ በመምረጥ ብልህነታቸውን ካስመስከሩ መሃከል በምሳሌነት ኒውተንን ብጠቅስም በተመሳሳይ በመጠየቅ መንገድ ተራምደው መዳረሻቸውን ተሻጋሪ እና አሻጋሪ ያደረጉ ሌሎችም አሉ። ኾኖም አሳዛኙ ነገር ለተፈጠረባቸው ጥያቄ መልስ ለማግኝት ዳክረው እውቀትን ያገኙ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ፈላስፎች በርካታ አሊያም በቂ የሚባል አለመሆናቸው ነው። ግና ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኚህ በቁጥር ውስን የሆኑ ብልሆች ለምን እንዴት የት ብለው በመጠየቃቸው እና ጥቂት የማይባል ምላሾችን ፈልገው በማግኝታቸው ዓለመ ሰማያትን፣ ምድራችንን እና ማንነታችንን እንድናውቅ ረድተውናል፤ እየረዱንም ይገኛሉ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተን እንዴት ዘላቂ መሆን እንደምንችል በምርምር ውጤታቸው አስተምረውናል። ታመን እንድንድን እና እድሜያችንን እንዲዘልቅ መንገድ ጠርገውልናል። ኑሯችን በኋላቀርነት ገመድ ተተብትቦ እንዳይቀር፣ አኗኗራችን ምቹ እንዲሆን፣ እመርታችን እንዲጎለብት እና ዕይታችን እንዲሰፋ አድርገዋል።

አሁንም ቢኾን የመጠየቅ ጉዞን መከተል እንዳለበት ተረድቶ የወሰነ እንዲሁም ወስኖ መራመድ የጀመረ ሰው መዳረሻው ከላይ በምሳሌነት ካየነው የኒውተን ታሪክ የተለየ አይሆንም። እንግዲህ ይህን ያወቀ ተጓዥ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማግኝት እንደሚችል ያምናል፤ ያውቃልም። ይህ መንገደኛ ማምለጫ የለሽ በሚመስል ወጥመድ ውስጥ ቢገኝ እንኳን መውጫ እና ማምለጫ ዘዴን ያበጃል እንጂ በፍጹም ተስፋ አይቆርጥም፡፡ እንዲህ ዓይነት ተራማጅ ሰው መሬት ላይ የማያወርደው ህልም እንደሌለው ከእውነቶቹ አንዱ ነው፡፡ ወደ ኋላ ሊጎቱት የሚችሉ እልፍ አእላፍ ነገሮች እንደሚገጥሙት ቀድሞዎንም ያውቃል። ነገር ግን መሮጥ ቢያቅተው ተራምዶ፣ መራመድ ቢሳነው ተንፏቆ፣ መንፏቀቅ ቢያቅተው ወደ ፊት ወድቆ ካለመበት ይደርሳል፤ አሸናፊም ይሆናል። አሸናፊም ሲሆን ከራሱ አልፎ ለብዙዎች በነገሮቹ ኹሉ ይተርፋል።

✍️ፍሬው ማሩፍ
📚ጥያቄዎቹ

@zephilosophy
የነቃ ሲመክር

ውዶቼ!
ተነሱ! ተነሱ! ተነሱ!
በጠያቂ አቅም ነው የሚሰራው መልሱ፡፡

ከኮከቦች ርቀት፣
ከባህሮች ስፋት፣
ከአውሎ ንፋስ ጉልበት
የተጠነሰሰ፤
የመገለጥ ወይን ከልቤ ፈሰሰ።
ከከፍታዎቼ፣ ከአደባባዮቼ ወስዶ ላይመልሰኝ፤
ከነፍሴ ተማክሮ ክንፌ ቀሰቀሰኝ።

ሰረገላው አይቆም፣ ነጂውም አይተኛ፤
ጥያቄም፣ ይቅርታም፣
ፀፀትም፣ ትዝብትም - ይልካል ወደእኛ፤
“ተጓዦቼን ሁሉ ምንድን አስተኛቸው?
እኔ መቆም አላውቅ -
             ወይኔ ረበሽኳቸው!” ይላል።

ዕረፍት የማያውቀው - ፈጣን ሰረገላ፣
መንቃት በማያውቁ- ተጓዦች ሲሞላ፤
የመገለጥ ወይን በአፍጢሙ ተደፋ፤
“ወራጅ አለ!” የሚል ተሳፋሪ ጠፋ።


ውዶቼ!
ተነሱ! ተነሱ! ተነሱ!
ግለጡ፣ ኀስሱ፣
ከጥያቄ ጅረት በጥራት ፍሰሱ፤
ሰፊ ጊዜ ስጡ ክንፍ ከነፍስያ እንዲወሳወሱ።
ጎዳናው፣ ሸለቆው፣
ጋራው፣ ሸንተረሩ - አዲስ ፊት እንዲያዩ፤
“ወራጅ አለ!” በሉ በየአደባባዩ።

መፅሀፍ -የመንፈስ ከፍታ
ደራሲ-ሩሚ
በረከት በላይነህ እንደተረጎመው!!

@Zephilosophy
@Zephilosophy
"I reject any religious doctrine that does not appeal to reason and is in conflict with morality." 
— Mahatma Gandhi

@zephilosophy
ሐይማኖተኛ እንጂ መንፈሳዊያን አይደለንም

~
አምልኮታችን ውስጥ ስሜት እንጂ ስክነት የለም... ቶሎ ነው ቱግ የምንለው... አንዳንዴ ለእግዜሩ/ አላህ 'ጠበቃ' የሆንን ሁሉ ይመስለናል... ስሜት ደግሞ የተቀባበለ ጠብመንጃ ማለት ነው... በየትኛውም ሰዓት ቃታው ሊሳብ ይችላል... አያድርስ ነው ያኔ...
------
ይህ ለምን ሆነ?…
----
ስሜት ሐይማኖተኛ ብቻ ከመሆን ሲወለድ ስክነት መንፈሳዊነትን ከመደረብ ይመዘዛል… እኛ ደግሞ ሐይማኖተኛ እንጂ መንፈሳዊያን አይደለንም… ስለምን ቢሉ “መምህራኑ” የሐይማኖት እውቀትን ከስሜት ጋር ሰጡን እንጂ መንፈሳዊነትን ከስክነት ጋር አላሳዩንም…
-----
ሌላም አለ… ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’… እንዲሉ…

•  ባለፉት አስርት ዓመታት ከዘመን ጋር የነወሩ፣ በንዋይ መገዛት እንጂ ራስን መግዛት የማያውቁ ተኩላዎች ከስማቸው ፊት በሚያስቀምጡት ‘የስያሜ’ ለምድ በግ መስለው ተቋማቱን አጨናንቀዋል…

•  ከደዌ ያልተላቀቀው ፖለቲካችን በሃሳብ ልዕልና ከመቆም ይልቅ በማናቆር ብልጠት ስለሚጓዝ እነዚህን ተቋማት እጀታ አድርጎ ግቡን ያስፈጽማል…

•  መጠየቅ፣ መመርመር፣ ለምን እንዴት ማለት የተነጠቀው ትውልድ ደግሞ በምንም ጉዳይ የእውር ድንብር ግርርርር ማለት መደበኛ ግብሩ ሆኗል… ግርግር  ለማን ይመቻል? - ለሌባ!!
___
እንደ ሙስሊምነትህ አክብሮት የምትሰጠውን ነገር ፕሮቴስታንቱ 'አልባሌ' ሲያደርገው መቆጨትህ ባይገርምም ነገሩን በመግባባት ማሳለፍህ ነው አማኝ የሚያስብልህ... ኦርቶዶክስ ሆነህ ሙስሊሙ ውድህን 'ሲያንቋሽሸው' የሚፈጠርብህ ጉዳት ይሁን ቢባል እንኳ እልሁን በፍቅር ለማብረድ ያለህ ብርታት ብቻ ነው ክርስቲያን 'ሚያደርግህ...
___
<<ቅዱስ ቁርዓንን>> በማዋረድ 'የከበረ' ክርስቲያን ሊኖር አይችልም... የተዋረደ ካልሆነ በቀር... <<ንዋየ ቅድሳቱ>> ላይ በመሳለቅ የጸደቀ ፕሮቴስታንትም ፈልገን አናገኝም... በሞራል የዘቀጠ እንደሆን እንጂ… በእኔ እምነት ቅድስና የራስን ከመጠበቅ ጥንቃቄ በላይ የሌላውን ከማክበር ልዕልና ለመወለድ ቅርብ ነው... ያም ሆኖ ችግሩ ሲፈጠርስ?... ሰይፍ እንምዘዝ?... ደም እንቃባ?... ቤተ አምልኮ እናፍርስ?... በጭራሽ... ሰው በክፋቱ ልክ ቢከፉበት እጥፉን ይከፋል... በፍቅር ካረቁት ግን ለሁልጊዜ ይድናል...
___
አፍጋኖች እንዲህ ይላሉ...

"Don't use your teeth when you can untie the knot with your fingers"
___
ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግደው መስተጋብራችን በብዙ እንከኖች የተሞላ ነው... ከትናንት ብዙ ብንርቅም አዘጋገማችን ግን መዳረሻን የሚያርቅ ይመስላል... እንደ ቤተ-አምልኳችን አስተምሮ እኛ መታረቅ እየተገባን በፖለቲከኞች እንታረቃለን… በመንፈሳዊ ስክነት በርደን እንድንታይ ሲጠበቅ በአፈሙዝ እንቀዘቅዛለን… ታዲያ ምኑ ላይ ነው የሐይማኖት ፋይዳው?... ሐይማኖተኛን እምነቱ ከመግደል ካላስቆመው ሌላውማ ስለምን ይፈረድበታል?... ሐይማኖተኝነት ሐይማኖቱን ሳይኖሩት ይሆኑታል እንዴ?...
----
“True religion is real living; living with all one's soul, with all one's goodness and righteousness.” - Albert Einstein
___
ለማንኛውም...
• ሁኔታዎችን በእኛ ላይ የመጣ፣ ሆን ተብሎ የተደረገ፣ ከጥላቻ የመነጨ ከሚል ፍረጃ ማላቀቅ ውብ ነገር ነው...

• አንዳንድ ሁኔታዎችን በመንጋ ቁርቁስ ከማጦዝ ይልቅ ተቋማዊ አልያም ጓዳዊ በሆኑ መንገዶች ለመፍታት መሞከር የማይሻገር ቁስል እንዳይፈጠር ያደርጋል...

• አንድና ሁለት ግለሰቦች የፈጸሙትን ጥፋት ግለሰቦቹ የተገኙበት ሐይማኖት /ተቋም/ ጉዳይ አድርጎ አለማሰብም በጎ ነገር ነው...
___

“When I meet a new person, I don't see race or religion. I look deeper. We must learn to satisfy our conflicts peacefully and to respect one another.” - Muhammad Ali
-----
መልካም ጊዜ

ደምስ ሰይፉ

@bridgethoughts
ኤግዚስቴንሻሊዝም እና ኒሂሊዝም

ኤግዚስቴንሻሊዝም በፍልስፍና ውስጥ ብዙ ከተሠራባቻው ፍልስፍናዊ ንድፈ-ሐሳቦች አንዱ ነው፤ በአንዳንድ ምልከታዎቹ ከኒሂሊዝም ጋር የሚጋራቸው ነጥቦች ስለሚኖሩ ሁለቱን ንድፈ-ሐሳቦች ቁልጭ አድርጎ ማሳየት ባይቻል እንኳ ተዛምዶና ተባዕዷቸውን ለማሳየት መሞከር ተገቢ ነው። ኤግዚስቴንሻሊዝም “አሁን” እና “እዚህ” በሚሉ ነጥቦች ያምናል። “ኒሂሊዝም” ግን በምንም አያምንም፤ ካመነም በምንም ነው።

ኒሂሊዝም የትኛውንም ዓይነት ዓለማዊ ሀቅ አይቀበልም፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሩስያ ሥነ-ጽሑፎች ውስጥ እንዳበበ ወይም እንደተመሠረተ ይታሰባል። በዚያም በሩስያ በነበሩ ተቋማዋዊ መዋቅሮች አመጽ ከመነሳት አልፎ የትኛውም መንግስታዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ መዋቅርንም መቃወም ችሏል።

“ኤግዚስቴንሻሊዝም” በየትኛውም የሕይወት ትርጓሜ የማይስማማ ነገር ግን እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዓለም መሥራት እንደሚችል የሚያስረዳ ወይም በእዚህ እውነት የሚያምን ነው። በጠቅላላው ሁለቱም እሳቤዎች ናቸው። መነጽራቸው የሚለያየው ግባቸው ላይ ነው።

ኒሂሊዝም በምንም ከማመን ይልቅ ምንምን የሚያመልክ ነው። በምንምነት ማመን በክብ ውስጥ ላለ ነገር ሁሉ ዕውቅና መስጠት ነው። “ኤፕሲቲሞሎጅካል” ፍልስፍናቸውም “ራሽናሊዝም” እና “ማቴሪያሊዝም” ነው፡ የግለሰብ ነጻነት ደግሞ የመጨረሻ ግባቸው። አይዲያሊዝም ወይም እምነታዊነት ለእነርሱ ዋጋ የለውም።

ኒሂሊስት ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” ብለው የሚያምኑ ሰዎች አይደሉም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርን መኖር ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ በእግዚአብሔር መኖር እርግጠኞች አይደሉም። በሌላ ምሳሌ ደግሞ ለማየት አንዲት ሚስት በባሏ ላይ ብትቀላውጥ “ባል ግድ የለም አይጎዳኝም” ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ጉዳዩ የሚሆነው ሚስት በሕይወት ውስጥ ትቀላውጥ እንደሆነ ማስረጃዎች በመኖራቸውና ባለመኖራቸው ላይ ነው። ይህም ሆኖ ሚስት መቀላወጧ በማስረጃ የተረጋገጠም ቢሆን ባል የሆነ ጊዜ በእርሷ ላይ ስላለመቀላጡ ማስረጃው ምንድን ነው? ስለዚህም እርግጠኛ የምንሆንበት ሕይወት የለንምና ሚስት ቀላውጣ ብትገኝ የሚደንቅ ሊሆን አይችልም ይላሉ።

ይሄንን ነገራቸውን ሊገለጥ የሚችል ሁለት ገላጭ ምሳሌዎቻቸውን ማየት እንችላለን። “What he wished to believe, that is what each man believes” “ሊያምን የሚመኘው ማንም የሚያምነውን ነው” እና “The life of mortals is so mean a thing as to be virtually un-life” “የሟች መኖር ማለት አለመኖር ነው” ወይም “ሟች ሕይወቱ አለመኖር ነው”። (ሁለቱም አባባሎች በሃይዲገር የተጠቀሱ ናቸው)

ኒሂሊስቶች ለእዚህ እሳቤአቸው አስረጂ የሚያደርጉት የሰው ልጅ ምኞትን እና ቅዠትን ከሕይወቱ ካስወጣ ምንም መሆኑን ይገነዘባል” የሚል ነው። ለመሆኑ የኒሂሊስቶች መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል? እነርሱስ በምን ሊገለጡ ይችላሉ? ሕይወት ትርጉም የላትም፣ ይች ዓለምም ምንም ናት ብለው ያመኑ ኒሂሊስቶች ከእነዚህ በአንደኛው ጥላ ላይ ያርፋሉ።

ፍልስፍናዊ ሞት ፡

እጅ ይሰጣሉ፤ “ሕይወት ትርጉም አልባ ናት ስለዚህም መፈላሰፌ ዋጋ የለውም” ከሚል መነሻ ራሳቸውን በሃይማኖት ጥላ ሥር ይደብቃሉ፤ ወይም በአንድም በሌላ መንፈሳዊ ዋሻ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ።

አካላዊ ሞት :

ትርጉም አልባ በሆነ ዓለም ውስጥ በሕይወት መኖር አሰልቺና የስቃይ ምንጭ ስለሚሆንባቸው ራሳቸውን ያጠፋሉ።

መቀበል :

ሕይወት እውነተኛ እና የመጨረሻ ትርጉም እንደሌላት እያወቁ መኖር።

ለመደምደም ሦስት ተመሳሳይ የሚመስሉ ነገር ግን የተለያዩ ፅንሰ ሐሳቦችን እንይ

ኤግዚስቴንሻሊዝም

"በግለሰባዊ ግንዛቤ፣ ግለሰባዊ መልካም ፈቃድና ግለሰባዊ ኃላፊነት ውህድ ኑረት አንድ ሰው በዓለም ውስጥ የራሱን የሕይወት ትርጓሜ መስጠት ይችላል ወይም ይገባዋል” ብሎ የሚያምን ነው።

ኒሂሊዝም

“ዓለም ትርጉም አልባ ነው ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን ለዚህ ዓለም እና ሕይወት ትርጉም ለመስጠት መሞከር በራሱ ምንምነት ነው” ብሎ የሚያምን ነው።

አብዘርዲዝም :

ደግሞ ለሕይወት ትርጉም ለማግኘት የሚደረገው ትግል ሁሉ ከተፈጥሮ የተነሣ ሁሌም ከትርጉም አልባነት ጋር የሚደረግ ግብ ግብ ነው፣ ነገር ግን ሕይወት ማለት ሁሌም ቢሆን ይህንን ተቀብሎ ሕይወት ልትሰጥ የምትችለውን አዎንታዊነት ሁሉ ለማግኘት መፍጨርጨር ነው።

በስተመጨረሻ ሥራ ላይ ያለውን የፍልስፍና ትርጓሜ ማየቱ መልካም ይሆናል። እስካሁን ያየናቸው የፍልስፍና ትርጓሜዎች በቅን ልቦና ያየ ሰው ፍልስፍናን እንዲህ ሊበይነው ይችላል። ወይም ይገባል።

“ፍልስፍና ማለት ጥብቅ በሆነ ምክንያታዊነት ላይ በመመሥረት በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ መሞከር ማለት ነው”

በዚህ ብያኔ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ጭብጥ “ጥብቅ እና ምክንያታዊ" የሚለው ነው። ነገር ግን “ስለምን?” –እዚህ ጋ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በማውጠንጠን፣ በመተንተን ወይም በኀልዮአዊነት መንገዶችም ቢሆን እያንዳንዳቸው በሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች ላይ በቂ አስረጂ ያለውን ጥብቅ ምክንያታዊነት ማቅረብ ነው። እንዳየነውም በተለያየ መደብ ያሉት ፈላስፎች በራሳቸው ጠቃሚ ያሏቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሠራሉ። እነዚያም ጥያቄዎች ለእነርሱ መሠረታዊ ናቸው።

ደሳለኝ ስዩም
📚የፍልስፍና መግቢያ
@Zephilosophy
@Zephilosophy
‹‹ትንንሽ ደስታዎች››
(በገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹የሚያፅናኑ›› ላይ ተመስርቶ የተጻፈ)
-------



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ- ለአፍታም ቢሆን 'ሚከልሉ

በፈተና 'ሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ፣
ከኑሮ ውክቢያ- ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር 'ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች





የፍቅር ውጥን
የሚያጓጓ፣  ልብ 'ሚያግል

ቀጭን ደሞዝ…
ለአምስት ቀናት- እንደንጉስ 'ሚያንቀባርር

ሚጢጢ ቤት
እንደልብህ 'ምትሆንባት
ኡፎይ ብለህ 'ምታርፍባት


አዲስ ልብስ
ፕ-ስ-ስ-ስ!


አዲስ ጫማ
ላረማመድ የሚስማማ…


ቆንጆ ጭልፋ፣ ማንቆርቆሪያ
ብርጭቆ፣ ድስት፣ አዲስ ቂጣ መጋገሪያ


የተቆላ ቡና፣ ፈልቶ ሲወርድ፣ ሲጨስ እጣን
ትኩስ ቄጠማ ተጎዝጉዞ ያለው ጠረን



ሻይ በስኳር ከአምባሻ ጋር
ምሳ ሽሮ- እራት ምስር


ኮልታፋ ህጻን ነፍስ የማያውቅ
ያለ ሰበብ ስቆ 'ሚያስቅ


ሳያስቡት በድንገት
የሚደውል ወዳጅ ዘመድ
እንዴት ነህ ብቻ ለማለት…



ውብ የራስጌ መብራት

መጽሐፍት!  መጽሐፍት! መጽሐፍት!


ዘፈን! ዘፈን! ዘፈን!
የጂጂ፣ የቴዎድሮስ፣ የአስቴር፣ የመሐሙድ፣
የፍቅርአዲስ እና የጥላሁንዘፈን!


መታቀፍ መታቀፍ…!
በሚያፈቅሩት እቅፍ እንደሞቁ እንቅልፍ

እንቅልፍ! እንቅልፍ! እንቅልፍ!



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ ለአፍታም ቢሆን  'ሚከልሉ

በፈተና የሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ
ከኑሮ ውክቢያ ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች

✍️ሕይወት እምሻው

@Zephilosophy
ወንፊት ነፊ አትሁኑ

የእግዜር ቃል ሁሉን አቃፊ ነው። አጥርና መገደቢያ በዚያ የሉም። እና ለምን ይሆን የእናንተው በአጥር  መከበቡ?

የእግዜር ቃል ማቅለጫ ነው። የቱንም አክብሮ የቱንም ሳያቀል፣ የፈጠረውን ሁሉ አቅልጦ አንድ ያደርጋል። የመረዳት መንፈስ አለውና፣ እርሱና ፈጠራው አንድ መሆናቸውን ሙሉ ለሙሉ ይረዳል-አንዱን ለይቶ አለመቀበል ሙሉውን አለመቀበል፣ ሙሉውን አለመቀበል ደግሞ ራሱን አለመቀበል መሆኑን ጭምር! ስለዚህም ዓላማና ትርጉሙ ለዘለዓለሙ አንድ ነው።

የሰው ልጅ ቃል ግን ወንፊት ነው። ከፈጠረው ውስጥ ገሚሱን አቅፎ ገሚሱን ይገፋል። ዘለዓለሙን፣ ይሄን ወዳጅ ብሎ እንዳቀረበ ያንን ጠላት ብሎ እንዳራቀ ነው - ነገር ግን ዘወትር የትናንት ወዳጁ የዛሬ ጠላት፣ የዛሬ ጠላቱ የነገ ወዳጅ እየሆነው

እናም፣ የሰው ልጅ ከራሱ ጋር በገጠመው ጨካኝ እና ፍሬ አልባ ጦርነት ሳቢያ ውስጡ በንዴት ፍሟል።

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ የሰው ልጅ፣ እሱና ፈጠራው ሌላም ሳይሆን አንድ መሆናቸውን፣ ጠላትን ማባረር ወዳጅን ማባረር፣ ጠላት ላይ በር መዝጋት ወዳጅ ላይ በር መዝጋት መሆኑን እንዲረዳ የሚያደርገውን ቅዱስ መንፈስ ስላጣ ነው። “ጠላት” እና “ወዳጅ" የሚሰኙት ሁለቱ ቃላትም የእርሱ ቃል፣ የእርሱ "እኔ" ፈጠራዎች ናቸው::

የጠላኸው እና መጥፎ ነው ብለህ የወረወርከውን ያለምንም ጥርጥር ሌላው ወድዶ እና ጥሩ ነው ብሎ ያነሳዋል። እውን አንድ ነገር በአንዴ ሁለት ተፃራሪ ነገሮችን መሆን ይችላልን? እውነታው ግን፣ ይሄኛውንም ያኛውንም አይደለም - ያንተው “እኔ” መጥፎ ሲያደርገው ሌላው “እኔ” ጥሩ እድርጎት እንጂ!

መፍጠር የሚችል፣ የፈጠረውን መልሶ እንዳልተፈጠረ ማድረግ እንደማይሳነው አልነገርኳችሁምን? ጠላታችሁን ራሳችሁ እንደፈጠራችሁት ሁሉ ራሳችሁ ጠላትነቱን ልታጠፉ ወይም ዳግም ወዳጅ አድርጋችሁ ልትፈጥሩትም ትችላላችሁ። ለዚያ ደግሞ የእናንተ “እኔ” ማቅለጫ ሊሆን ግድ ይለዋል። ለዚያ የመረዳት መንፈስ ያስፈልጋችኋል።

ስለዚህም ... እንዲህ እላችኋለሁ - ከጸለያችሁ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም መረዳትን በመሻት ጸልዩ። ባልደረቦቼ ሆይ ... ወንፊት ነፊ አትሁኑ።

የእግዜር ቃል ሕይወት ነውና፤ ሕይወትም ሁሉም አንድ እና የማይከፋፈል ሆኖ የሚሰራበት ማቅለጫ ነች - ሁሉም በፍጽም ሚዛን፣ ሁሉም በደራሲው ቅድስት ሥላሴ ፊት ክብር የተቸረው ሆኖ! ባንተስ ፊት ምን ያህል የገነነ ክብር ይኖረው ይሆን?

መቼም ቢሆን በወንፊት አንገዋላዮች አትሁኑ ወዳጆቼ፤ ያኔ ሁሉን አቅፋችሁ፣ ሁሉን አልፋችሁ በገዘፈ ቁመና ትቆማላችሁ - ሊይዛችሁ የሚችል ወንፊትም አይኖርም።

አዎን ... ፈጽሞ በወንፊት አንገዋላዮች አትሁኑ ወዳጆቼ፡፡ የራሳችሁን ቃል ታውቁ ዘንድ፣ መጀመሪያ ነገር የቃሉን ዕውቀት እሹ። ቃላችሁን ስታውቁ ደግሞ፣ ወንፊታችሁን ለእሳት ትዳርጉታላችሁ። የእናንተ ቃል ገና መሸፈኛውን ያልገለጠ ቢሆን እንጂ የእያንዳንዳችሁ እና የእግዜር ቃል እንደሁ እንድ ነው!

ሚርዳድ መሸፈኛዎቹን ትጥሉ ዘንድ ይሻል...

የእግዜር ቃል፣ መቁጠር ያልጀመረ ጊዜ እና ያልተስፋፋ ቦታ ነው። እውን ከእግዜር ጋር ያልነበራችሁበት ጊዜ ነበረን? እግዜር ውስጥ ያልሆናችሁበት ቦታስ አለ? እና ታዲያ ዘላለምን በሰዓታት እና ወቅቶች የጠፈራችሁት ለምን ይሆን? ለምንስ ይሆን ቦታን በጋት እና ክንድ ለክታችሁ የገደባችሁት?

የእግዜር ቃል የማይወለድ ሕይወት ነው፤ ስለዚህም አይሞትም። እና ለምን ይሆን በልደት እና ሞት መከበባችሁ? በእግዜር ሕይወት ብቻስ አይደል የምትኖሩ? ሞት አልባውስ የሞት ሰበብ መሆን ይችላልን?

የእግዜር ቃል ሁሉን አቃፊ ነው። አጥርና መገደቢያ በዚያ የሉም። እና ለምን ይሆን የእናንተው በአጥርና መገደቢያ መከበቡ?

እኔም እላችኋለሁ፣ ሥጋ እና አጥንታችሁ እንኳ የእናንተ ብቻ ሥጋ እና አጥንት አይደለም። ሥጋ እና አጥንታችሁን እወሰዳችሁበት፣ መልሳችሁም የምትመልሱበት፣ ከዚያው ከምድር እና ሰማይ ገንቦ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው እጆች አብረዋችሁ ጠልቀዋል።

በዓይኖቻችሁ ውስጥ ያለው ብርሃንም የእናንተ ብርሃን ብቻ አይደለም። ፀሐይን አብረዋችሁ የሚጋሩት ሁሉ ጭምር እንጂ። ውስጤ ያለው ብርሃን ቢሆን እንጂ፣ ዓይናችሁ ከእኔ ምን ያይ ነበር? በዓይናችሁ ውስጥ ሆኖ የሚያየኝ የእኔው ብርሃን ነው። በዓይኔ ውስጥ ሆኖ የሚያያችሁ የእናንተው ብርሃን ነው፡፡ እኔ ድቅድቅ ጨለማ ብሆን፣ ዓይናችሁ፣ እኔን ሲያይ፣ ድቅድቅ ጨለማ ያይ!!!

በደረቶቻችሁ ውስጥ ያለው ትንፋሽም የእናንት ብቻ አይደለም። ዓየር የሚተነፍሱና፣ ተንፍሰው የሚያውቁ ሁሉ በደረቶቻችሁ ውስጥ እየተነፈሱ ነው። አሁን ድረስ ሳንባዎቻችሁን የሚሞላው የአዳም ትንፍሽ አይደለምን? አሁን ድረስ ልቦቻችሁ ውስጥ የሚመታው የአዳም ልብስ አይደል?

ሐሳቦቻችሁም የእናንተ ብቻ ሐሳቦች አይደሉም። የጋራ ሐሳብ ባሕር የእኔ ትላቸዋለች፤ እናም ደግሞ ያንን ባሕር ከእናንተ ጋር የሚጋሩ አሳቢ ፍጡራን ሁሉ..

ሕልሞቻችሁም ቢሆኑ የእናንተ ሕልሞች ብቻ አይደሉም። መላው ሁለንተና በሕልሞቻችሁ ውስጥ ያልማል...

ቤቶቻችሁስ ቢሆኑ - የእናንተ ብቻ አይደሉም። የእንግዶቻችሁ ማረፊያ፣ ቤቱን የሚጋሯቸሁ ፍጡራን ሁሉ የዝንቦች፣ የአይጥ የድመቱ ሁሉ ማደሪያ ናቸው።

ስለዚህም፣ አጥሮችን ተጠንቀቁ። ስታጥሩ በማጭበርበር ነው፣ እውነትንም ከአጥሩ ውጪ ታገልሏታላችሁ። አጥሩ ውስጥ ፊታችሁን ለማየት ስትዞሩ ደግሞ፣ ሌላው ስሙ ማጭበርበር ከሆነው ሞት ጋር ፊት ለፊት ግጥም!

መነኩሴዎች ሆይ፣ ሰውን ከእግዜር መለየት አይቻል ነገር! ሰውን፣ ከእግዜር ቃል ከወጡት ከብጤዎቹ የሰው ዘርና ከመላው ፍጡራን መለየትም እንዲሁ...

ቃሉ ውቅያኖስ ነው፤ እናንተ፣ ደመናዎችን! እና .... እውን ውቅያኖስን በውስጡ ባይይዝ ደመና ደመና ይሆን ነበር? ቢሆንም ግን፣ ቅርፅና ማንነቱን በሕዋው ላይ ቀርፆ ለዘለአለም ለማኖር ደፋ ቀና ሲል ሕይወቱን የሚያባከን ደመና ጅል ነው። ከተንኮታኮተ ተስፋ እና ከመሪር ከንቱነት በቀር ከዚህ የጅል ልፋቱስ ምን ያጭድ ይሆን?

ራሱን ካላጣ በቀር ራሱን አያገኝም። እንደ ደመና ሞቶ ካልጠፋ በቀር፣ ብቸኛ እኔነቱ የሆንውን፣ ውስጡ ያለውን ውቅያኖስ ሊያገኝ አይችልም።

ሰው፥ እግዜርን ያረገዘ ደመና ነወ። ከራሱ ባዶ ካልሆነ ራሱን የማያገኝ! አህ .... ባዶ የመሆን ደስታ- አህ፣ ባዶ የመሆን ሐሴት!

በቃሉ ውስጥ ለዘለዓለሙ ካልጠፋህ፣ አንተን ... እንዲያውም አንተነትህን የሆነውን ቃል መቼም አትረዳው! አህ ... የመጥፋት ደስታ፣ አህ ... የመጥፋት ሐሴት!

ደግሜ እላችኋለሁ ... መረዳትን በመሻት ጸልዩ። ቅዱሱ መረዳት ልቦቻችሁን ሲያገኘው፣ “እኔ” ባላችሁ ቁጥር በፈጣሪ ታላቅነት ውስጥ የደስታ ምላሽ የማይደውልላቸው አንዳችም ነገር የለም።

ምንጭ ፦ መጽሀፈ ሚርዳድ
ፀሀፊ፦  ሚካኤል ኔይሚ
ተርጓሚ፦ ግሩም ተበጀ

@Zephilosophy
@Zephilosophy
"Dictators and their retinue are four times removed from truth and reality. The first time they lie to themselves as individuals, the second time they lie to each other as partners, the third time they lie to the people as a group, and the fourth time they expect the people to lie to them by acquiescing their lies."

Mindaryalew Zewde
@zephilosophy
“Now, there is one thing you might have noticed I don’t complain about: politicians. Everybody complains about politicians. Everybody says they are terrible. Well, where do people think these politicians come from? They don’t fall out of the sky. They don’t pass through a membrane from another reality… it’s what our system produces: Garbage in Garbage out. If you have selfish, ignorant citizens you’re going to get selfish & ignorant leaders…”

George Carlin
@zephilosophy
መፅሀፍ-ሽፍቶችና መሪዎች
ደራሲ-ስብሐት ገብረእግዚአብሔር
የገፅ ብዛት - 384

"በዚህ ስብስብ ውስጥ ታሪክ ነክ ፣ አፈ ታሪክ፤ የልብ ወለድ ገፀባህሪይ ላይ የተመሰረተ ወግ ፣ ተረት ፣ ሀይማኖት ነክና ፍልስፍና ቀመስ ወግ፤ ሳይንስ፣ የጉዞ ትውስታዎች፤ መረጃዎች ማህበራዊ ትዝብትና አስተውሎቱን የሚያጋረበት መጣጥፍና ግለሰባዊ ታሪክ ፤ ከህይወት ልምዱ ፣ ትዝብቱና በንባብ ከካበተ ዕውቀቱ እየጨለፈ በማይጠገብ ለዛና የአጻጻፍ ክህሎቱ የቸረን በረከቶች ይገኙበታል።"

አርታኢ -ማንይንገረው ሸንቁጥ

ገዝታችሁ እንድታነቡት ጋብዘናል
@zephilosophy
መኖር ፣ መኖር ፣አሁንም መኖር (ጓድ ሌኒን)

መፅሀፍ -ሽፍቶችና መሪዎች
ደራሲ-ስብሐት ገብረእግዚአብሔር

እቺን ከባድ ኑሮ ስንኖራት እንግዲህ አንዳንድ ጊዜ እንደ መፈላሰፍ... አንዳንድ ጊዜ እንደ ወፈፍ ወፈፍ!... አንዳንድ ጊዜ እንደ መመጻደቅ... አንዳንድ ጊዜ እንደ መዘባረቅ... አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደ ሌላ ሌላ ያረገናል - ሰው በመሆናችን

አሁን ደግሞ ምስጋና ይግባው፣ እንደ መፈላሰፍ አሰኝቶናል፣ እነሆ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ሲከታተል

ፍልስፍና የማንንም ሀሳብ (የዝጌርን እንኳ ቢሆን) ሳይመረምር አይቀበልምም እምቢ አይልምም። እንድያውም የኛ ፍልስፍና አሪፍ አሪፍ ጥያቄ እንጂ መልስ የለውም።

አንተ ተፈላሳፊው “ማን ነህ? ከየት መጣህ? ወዴትስ እየሄድህ ነው?” ማን እንደሆንክ ከማንም ሰው ይበልጥ የምታውቀው አንተ ራስህ ነህ። ያውም ብዙ አታውቅም፣ ከምታውቀው የማታውቀው በስንትና ስንት እጥፍ ይበዛል። እንድያም ሆኖ አንተን የሚያውቅ ሰው አንተ ብቻ ነህ። ሌላው ሰው (እናትህን ጨምሮ) ሊወድህ፣ ሊያደንቅህ፣ “ሊያመልክህ” ይችላል እንጂ ሊያውቅህ አይችልም።

እኛ ሌሎቻችን ስላንተ ልናውቅ የምንችለው፣ እንደሁላችን (እንደ ህያው ፍጡር ሁሉ - ሳር ቅጠሉን ጨምሮ) ከተባዕትና ከእንስት መዋሀድ የመነጨህ የህይወት እመርታ መሆንህን ነው....ተራህን ከሌላው ፆታ ተዋህደህ የህይወት ምንጭ፣ የእመርታ መዝለያ ሆነህ እስክታልፍ ድረስ...

...በባዮሎጂ መነጽር _ እንመልከትና፣ አንድ ጤነኛ ጐልማሳ የወሲብ ግንኙነት ሲያደርግ፣ ሴቷ ውስጥ ሁለት መቶ ሚሊዮን ፍሬ ይዘራል። ሁሉም ወደ ማህፀን ዋኝተው ደርሰው ከእንቁላሏ ጋር ለመዋሃድ እየተሽቀዳደሙ ነው።

እንግዲህ አባትህ ከዚያች አንተ ከተረገዝክባት ግንኙነት በፊት ስንትና ስንት ጊዜ ሁለት መቶ ሚሊዮን ተሽቀዳዳሚ እንደተኰሱ አዕምሯዋችንን ያታክታል አስብ  ያ ሁሉ ቢሊዮናት ዘር የትም ላይደርስ መበተኑ! ከንቱ ኪሳራ!!

ተፈጥሮ (ሌላ ስምዋ እዝጌር) ግን እኛ የምናውቀውን ቁጥር፣ ክብደት ቁጠባ ምናምን የምታውቀው አትመስልም። ካወቀችም ግድ ያላት አትመስልም (እኛ ደሞ ሊመስለን ይችላል እንጂ ልናውቅ አንችልም እንዲያም ቢሆን መፈላሰፋችንን እንቀጥላለን...)

...በዚያች በፍሬያማ የወላጆችህ መተቃቀፍ እንግዲህ፤ያንን ሁለት መቶ ሚሊዮን ተሽቀዳዳሚ ቀድመህ አንደኛ ስለሆንክ ተረገዝክ  ካንተ ሻምፒዮንነት ጋር ፣የአበበ ቢቂላ፣ የነኃይሌ ገብረሥላሴ የማራቶን ድል ምንድናት? ኧረ ከቁጥርም አትገባ!!

ያቺ በናታችን ማህፀን ውስጥ የምንኖራት ዘጠኝ ወር ራሷን የቻለች ገነት ነበረች። ምንም ሥራ ሳይኖርብን፣ ሳንጐርስ ሳናኝክ እየተመገብን፣ ማንም የሚጋራን ወይም የሚሻማን ሳይኖር እየተንፈላሰስን፣ እንደ ልብስ በተሰካችልን ሐይቅ ውስጥ እየተንሳፈፍን እንዲያውም አንዳንድ የሳይንስ ዘርፍ (anthropology, psychiatry, sociology) አዳምና ሔዋን ከገነት ተባረሩ የሚባለው የሙሴ “ታሪክ” ከማህፀን ወጣን ...ወደዚች ኑሮ ጣጣ ተባረርን - ከማለት ሌላ ትርጉም የለውም ይላል።

“እኛ ወደ ማህፀን ስንሽቀዳደም'ኮ አንደኛና መጨረሻዎች ውራዎች ሳይሆን፣ አንደኛና ሁሉ ዜሮዎች ነበርን። አንደኛ የወጣችሁት ሻምፒዮኖች ከነኃይሌ ገብረሥላሴ ሚሊዮናት ዶላሮች የሚበልጠውን፣ የትና-የት ከአድማስ-እስከ-አድማስ
ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የሚበልጠውን፣ ህይወት የምንለውን ሽልማት
ተጐናጽፈናል! ትላላችሁ። ያላችሁት እንደተቀመጠ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ (ግፋ ቢል በመቶ አስር-ወይ-ሃያ ሀምሳ ዓመት ዕድሜያችሁ እናንተም፣ ልክ እነዚያ ስትረገዙ ወደሞት ወደ አልቦ የተራገፉትን ዘሮች ያህል ወደ ሞት የምትራገፉ ናችሁ።)

ከኋላችሁ ዘለዓለም- ከመሀል ከእናንተ እቺን ከባድ ህይወት ስትኖሩዋት የተወሰኑ ዓመታት - ከፊታችሁ ሌላ ዘለአለም።

የናንተ መኖር ሁለት ዘለአለማት እንደ ጣቢቂያ ድንጋይ ያማከሉት ኮብላይ-ጠፊ ባዶ ጊዜ ነው።

ያም ቢሆን እኛ (ፀሐፊም አንባቢም) አሁን ይኸው እየኖርንም እየተፈላሰፍንም እንገኛለን። እጅ መስጠት የለም። “ወይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ!” አለች የፋሲካ ዶሮ! ፈጣሪው ሰጥቶንም ወስደንበትም ይሁን፣ እቺ ህይወት እንደሆነች የገዛ ራሳችን ናት! ወይ ፍንክች!

@zephilosophy
ሰሞኑን Fana እና Etv የሚባሉ የመንግስት ሚዲያዎች  "ብርቱካን አልታገተችም። አልተደፈረችም። ሁሉም ነገር ድራማ (ውሸት) ነው የሚል ዶክመንተሪ ፊልም ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሰርተዋል። "

እሺ ማንም ያዘጋጀው ድራማ  ነው እንበል።ግን እናንተ የመንግስት ሚዲያዎች እስካሁን ሰው በየቦታው ሲታገትና ሲገደል ምንም እንዳልተፈጠረ ድምፃችሁን አጥፍታችሁ ድራማ(ውሸት) ሲሆን ብቻ ነው ዶክመንተሪ የምሰሩት።በሺዎች የሚቁጠሩ የእገታ ሰቆቃዎች  ተገቢ ደምፅ ሳያገኙ እንዴት የአንዲት ሴት ቀሽም ድራማ ሰፊ ሽፋን ይሰጠዋል? ከብዙ ሺዎች የእውነት ድምፅ እንዴት የአንድ ሴት የውሸት ድምፅ በለጠባችሁ ?

ሚዲያዎች ተገቢ ሽፋን ባይሰጡትም በኢትዮጲያ ሰማይ ስር በዚህ አራት አመት ውስጥ በመቶወች የሚቆጠሩ ሰዎች በእገታ ሞተዋል። በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ታገተው ከፍለው ተለቀዋል። በብዙ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተመንዝብረዋል።

አሽከርካሪዎች ተዘዋውረው ስራ መስራት ፈተና ሆኖባቸዋል።ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆኗል። በዚህ የተማረረው ዜጋ አካባቢውን ጥሎ ለመውጣት እየተገደደ ነው። ያውም ያለው። የሌለው አማራጭ ስላጣ እዛው በሰቀቀን ይኖራል።

አንድ ቦታ ላይ ተደጋግሞ እገታ ሲፈጸም ዘላቂ እርምጃ የማይወስደው ለምንድነው ? አንድ አካባቢ ላይ ለዓመታት ሰው እየታገተ ገንዘብ ሲጠየቅ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታ አለማድረግ ትልቅ ጥያቄ ነው የሚያስነሳው።

ብዙዎች በእገታና ግድያ ተግባራት መሯቸዋል።

ከዓመታት በፊት በዚህ ስፋት ልክ ያልተለመደ አሁን ግን ልክ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ እየሆነ የመጣን ተግባር ፍትህ ማስፍንና እርምጃ መውሰድ ለምን እንዳልተቻለ የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ይህ ጥያቄ የብሔር ወይም የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም የሰብዓዊነት ጥያቄ ነው።ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ሰው ብቻ መሆን በቂ ነው።

@zephilosophy
ሁላችንም የተፈጥሮ አካላቶች ነን - ስፒኖዛ

ምንጭ፦ ፍልስፍና ከዘርአያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ
ዝግጅት፦ ፍሉይ አለም

በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ብዙ ኃይላት አሉ፡፡ ምድር ወደ ላይ በረን እንዳንሄድ ስባ ታስቀረናለች፡፡ ጸሐይ ምድርን በክብ ምህዋር ላይ እንድትዞር ታስገድዳታለች... ብንዘረዝራቸው የማያልቁ ብዙ ኃይላትን በሁለንተና ውስጥ እናገኛለን፡፡ በእያንዳንዱ ቁስ አካል ውስጥም ይፈሳሉ፡፡ በዓለም ሁሉ ያለ ነገር በእነዚህ ሃይሎች ተይዟል፡፡ ሰዎች፣ በባህር ውስጥ ያለ አሳ፣ ከወፎች የሚወጣ ድምጽ... ሁሉም የዚህ ኃይል አካል ናቸው፡፡ ሁላችንም በእነዚህ ኃይላት ታስረናል፡፡

ይህ ሁለንተናን በሌላ መንገድ የመመልከቻ ሃሳብ የቀረበው ባሩክ ስፒኖዛ በተባለ ፈላስፋ ነው፡፡ የፍልስፍናውም ሃሳብ ሞኒዝም ተብሎ ይጠራል፡፡ ሞኒዝም ቃሉ “አንድ ብቻ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ይህም በሁለንተና ውስጥ ያለ ነገር ሁሉ እንደ “አንድ አካል” ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡ እኔም አንተም፣ ጨረቃም ጸሐይም - ሁላችንም በአንድ አካል ውስጥ እንዳሉ ህዋሳቶች ነን፡፡

ስፒኖዛ በአብርሆት ዘመን በፊት የነበረ አውሮፓዊ ፈላስፋ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር በአንድ ዘመን የነበረው ዴካርት በሁለንተና ውስጥ ያሉ ነገሮችን በሶስት ይከፍላቸዋል- አእምሯዊ፣ አካላዊ እና አምላክ (ያልተፈጠረ እና ሁለንተናን የፈጠረ)።

ነገር ግን ስፒኖዛ እንዲህ ይላል - ከሁላችንም በላይ የሆነ እና ሁላችንንም የሚያውቅ አምላክ ካለ፣ ይህ አምላክ በሆነ መንገድ ከሁላችንም ጋር ይገናኛል ማለት ነው፡፡

“አቤቱ፣ ፈትነኝ መርምረኝም፤ ኩላሊቴንና ልቤን ፈትን:: እንዳለው መዝሙረኛው ዳዊት፣ ልብ እና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ በልብም፣ በኩላሊትም ውስጥ መገኘት አለበት ይለናል ስፒኖዛ፡፡ የአካላቸው ክፍል የሆኑ ነገሮችን ብቻ ነው ልንመረምር የምንችለው... አምላክም እኛን ሊመረምር የሚችለው እኛ የእርሱ አካል እስከሆንን ድረስ ብቻ ነው፡፡ እግርህ ላይ ያለ ህመም የሚሰማህ እግርህ የአንተ አካል ስለሆነ ነው፡፡ አምላክም የእኛ ህመም የሚሰማው እኛ የእርሱ አካል ስለሆንን ነው፡፡

በተመሳሳይም በሁለንተና ውስጥ ያሉ ሁሉም ነገሮች እንደ አንድ አካል ናቸው፡፡ አእምሮም፣ አካላዊ ቁሶችም የአንድ ግዙፍ ስርዓት አካል ናቸው፡፡ እንደ አንድም ይንቀሳቀሳሉ። ሁሉም ነገር ስረ መሰረቱ አንድ ነው፡፡ ያንተ ህሊናም፣ የጉንዳኖች ጉዞም፣ የአንዲት የብርሃን ቅንጣት፣ አንዲት ጠብታ ውሃም መዳረሻቸው አንድ ነው ... ሞኒዝም፡፡

አንስታይን ስፒኖዛን ይወደው ነበር፡፡ የስፒኖዛ ፍልስፍና ለእርሱ ሒሳባዊ ቀመሮች የሚፈይድለት ነገር ኖሮ አይደለም፤ ነገር ግን ስፔኖዛ ተፈጥሮን እንደ አምላክ አድርጎ ስለሚገልጻት ነው። አንስታይንም ተፈጥሮን አምላክ ብሎ ይጠራት ነበር፡፡

ስፒኖዛ ከጥቃቅን ነገሮች ወይም ተፈጥሮን/አምላክን ለመረዳት መጓዝ አለብን ይለናል፡፡ በተፈጥሮ ሁነቶች ተነስተን ውስጥ ራሳችንን እያስመጥን ስንመጣና ከተፈጥሮ ጋር ፍጹም አንድ ስንሆን፣ መታበያችን ከእኛ ይርቃል። እኔ እንዲህ ነኝ ማለትንም እናቆማለን፡፡ ራሳችንንም ነጥለን የምንኮራበት አልያም የምንወቅስበት ምክንያት አይኖርም... ምክንያቱም “እኔ” የሚባል ማንነት
አይኖረንም...

ስፒኖዛ የሰው ልጆች ሕይወታቸውን አወሳስበው ይኖራሉ ይለናል። ልክ እንደ ህጻናትም በጸደይ አበባ መሃል ከመቦረቅ ይልቅ፣ በብዙ ጥቃቅን ጉዳዮች ራሳችንን አስረነዋል። ይህ የሚገባን ግን እድሜያችን ሲገፋ ብቻ ነው፡፡ በእርጅና ዘመናችን በወጣትነታችን የነበሩ አላስፈላጊ ጭንቀቶቻችን እና ፍርሃቶቻችን ይገለጡልናል። ሕይወታችን ውስጥ ያሉ ነገሮችንም መውደድ እና ማድነቅ እንጀምራለን፡፡

@zephilosophy
@zephilosophy
ብርሃናዊና ፅልመታዊ
ደራሲ-ስብሃት ገ/እግዚአብሔር

መኖር-ማንበብ - መፃፍ። እዚህ ላይ ገፀባህሪ የሚባለው ፍጡር ይመጣና ራሱን ያስተዋውቃል። ፔሲሚስት Pessimist ነው። በአማርኛ  ምን እንደሚባል ቃሉን እስክንፈልግ ድረስ ተቃራኒው ኦፕቲሚስት Optimist ማንሳት የማይቀር ነው። እንዲህ ይላል። ግማሽ ብርጭቆ ወይን ጠጅ ቢያሳዩዋቸው ኦኘቲሚስት ለመሙላት ግማሽ ጐደለው ሲል አቶ ፔስሚስት ግን ገና ግማሽ ብርጭቆ ይቀራል ይላል።

የዲክ ግሬጐሪ አባት ደግሞ አስቀድሞ ማን እየቀዳ እንደሆነ ማወቅ ያሻል ይላሉ።

ነብሳችን በፔሲሚስትና በኦፕቲሚስትነት መሀከል እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ብርሃናዊነትና ዕልመታዊነት ይፈራረቁብናል። እቺ ምድራዊት ህይወታችን ስንኖራት የሲኦልና የገነት ስብጥርጥር ትመስላለች። ራብ ክፉኛ ሲሞረሙረን ጊዜዋ አንገብጋቢት ሲኦል ብትሆንም፤ አግኝተን ስንበላ አግኝተን ስንበላ ደግሞ ምግቡ መጣፈጡ የገነት ያህል ነው። ውሀ ጥም ለረዥም ጊዜ ሲያቃጥለን ጊዜው የሲኦል በመሆኑ ቢከፋንም፤ ውሀ አግኝተን ስንጠጣበት ገነት ሲበዛ መጣፈጥዋን እናውቃለን። ከአቅም ውጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሽንታችን ቢወጥረንና ከዚያም እየባሰበት ሄዶ ፊኛችን ሊፈነዳ እየቃጣ ቆይቶ ቆይቶ በለስ ቢታረቀንና ሽንታችንን ብንሸና ያቺ እፎይታ
የገነት ሌላ ገፅታ ናት።

እንደ መፈላሰፍ ቢያሰኛቸው ፔሲሚስቱ ንጉስ
ሰሎሞንን ይጠቅሳሉ። “ከቆሙት የሞቱት ይሻላሉ፤ ከሞቱት ደግሞ ጭራሹኑ ያልተፈጠሩት ይሻላሉ። ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው።” ኖረን ኖረን ማብቂያችን ሞት እስከሆነ ድረስ እንዴትስ ብንኖር ምን ልዩነት ያመጣል?

“ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባህር ይሄዳሉ፣ ባህሩ ግን አይሞላም። ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ።ነገር ሁሉ ያደክማል፣ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፣ አይን ከማየት አይጠግብም፣ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፣ ለኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሱት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። ከፀሀይ በታች የተሰራውን ስራ ሁሉ አየሁ፣ እነሆ ሁሉ ከንቱ ነው። ነፋስንም እንደመከተል ነው። ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፤ ጐደሎም ይሞላ ዘንድ አይችልም።
...
ጥበብና እብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፤ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደመከተል እንደሆነ አስተዋልሁ። በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና እውቀትንም የሚጨምር ሀዘንን ይጨምራልና...

... ልጄ የሰራቻትን ስራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ተመለከትሁ፣ እነሆ ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሀይ በታችም ትርፍ አልነበረም...!!"

ብርሀናማው ኦፕትሚስት የበኩሉን ይቀጥላል። እየለመድነው መሄዳችን መውለድ ምንኛ የሚያስደንቅ ተአምር መሆኑ እየተረሳን ይሄዳል እንጂ ከወንዱና ከሴቷ መተቃቀፍ ህፃኑ መመንጨቱ ማደጉ በጣም የሚገርም ነው። በየእንስሳቱ በየእፅዋቱ ተአምራት መባዛቱ። የህይወትን ችቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፉ ማለፍ።

የአፍላነት እድሜያችን ወደነበረው ወደ ህፃንነታችን እንመለስና እናቴን ከየት መጣሁ ስላት ወልጄህ ነው ትለኛለች። አንቺስ ከየት መጣሽ? እናቴ ወለደችኝ። እሷስ ከየት መጣች?እናቷ ወለደቻት። ማለቂያ የለውም? ሄዋንን እግዚአብሄር ፈጠራት። እሱስ ከየት መጣ? እሱማ ፈጣሪ ነው። እሺ እሱንስ ማን ፈጠረው? እሱማ አልተፈጠረም ፈጣሪ ነው። እሺ ከየት መጣ ኧይ!? ተወኝ እንግዲህ አታድርቀኝ!
በአዛውንትነት እድሜያችንም ከጥያቄ ወደ ጥያቄ እየነጠርን እንሄድ እንሄድና በመጨረሻ ፍጥጥ! መልስ የለም።

በአዳም ሀረግ ብንሄድ ወይም በኢቮሉሽን (በዝግመታዊ ለውጥ) ብንጓዘው የመጨረሻው ጥያቄያችን “ይሄ ሁሉ መዋለድ መፈጣጠር እንዴት ተጀመረ? የጀማሪውስ ጀማሪ ማን ወይም ምንድነው? ምንም ይሁን። ብቻ ሂደቱ ተጀምሯል። በራሳችን ላይ እያየነው ነው። ከአለመኖር ወደ መኖር መጥተናል። ቀጥሎ እንግዲህ በጊዜ ውስጥ ነብሳችን የኖረባትን ስጋችንን እና ያኖረችን ምድራችንን ተሰናብታ ለዘለአለም ወደምንኖርበት ሰማይ ቤት ታርጋለች። ሂደቷን ለመቀጠል። እቺ የመጨረሻዋ ምኞት ናት የሚሉ ቢኖሩ የመፈጠር ወይም የመወለድን ተአምር በገዛ ራሳቸው ሂደት ያዩት መሆኑን የማይገነዘቡ ወይም የረሱ ናቸው። እንጂ ካለመኖር ወደ መኖር (ከአልቦ ወደ ቦ) የነጠረ ተአምር በመሞት ሌላ ተአምር ከመኖር ወደ ዘለአለማዊ ህይወት ሊነጥር ለምን አይችልም? ተስፋ አለ። እምነትም አለ። የዛፍ ፍሬ ያንን የማናውቀው መነሻና መድረሻችንን የሚያውቅ ሀይል በማመንዋ ትረግፋለች። በእምነት ስትጠብቅ ሰንብታ ዝናብ ይመጣላታል። በእምነት ቅጠልዋ ብቅ ትላለች ከፀሀይ ጋር የፈጠራ ስራዋን ትቀጥላለች...

እነዚህ ብርሃናዊና ዕልመታዊ ተቃራኒ ገፀባህሪያት ከውስጣችን ተወስደው በማህበራዊና በአለማዊ ገፅታ ሲታዩ ወደ ሩቅ ምስራቅ ወደ ህንድ ወደ ቻይና አስተሳሰብ ይወስዱናል። ቀንና ሌት፣ ላይና ታች፣ ወንድና ሴት፣ በጋና ክረምት፣ ራብና ጥጋብ፣ እጥረትና ርዝመት፣ርቀትና ቅርበት፣ ደስታና ሀዘን፣ ብርድና ሙቀት...ሁለት ሁለት መሬትና ሰማይ
እነዚህ ሁሉት ሁለቶች መሐልኮ የሚመሳሰል ሶስተኛ አለ። ሶስተኛውን ማወቅ ግን የፈጣሪውን ምስጢር ገልጦ ማየት ስለሚሆን ለኛ ለፍጡራን ክልክል ነው።

ምናልባት እነሱ ሁለት፣ ሁለት እየሆኑ ያሉት እኔ ሶስተኛቸው ወይ እነሱ የፈጠሩኝ ወይ እኔ የፈጠርኳቸው ወይ በየተራ ያኛውም ይኸኛውም። ክልክል ነው!!

@zephilosophy
አጀብ!
ሳንታጀብ
!

ይህ በግርግር ዘመን ላይ ቆሞ የሚደነቅ ዘመነኛ ድምጽ ነው። የብቻ መንገዱን እየተመናተለ የሚገፋ ሰው ህቅታ። በሚያየው አጉል ዳንኪራ የሚሳቀቅ ብክን ነፍስ ሲቃ ነው። ሰው የመሆንን ውል ላጣን፣ እንደ ሸርጣን እየተጓተትን ለምንደማ መናኛዎች የተወረወረ የመገረም ቃል ነው።

ኖሮ ከሚታዘብ፣ ትርምስምሱን በአርምሞ ከሚመለከት ነፍስያ የሚቀዳ መባከን ነው። ቡድናዊነት እንደ ብራቅ ከሚጮህበት፣ አጀቡ፣ ወጀቡ ከሚያናፈበት ቀዬ የተገኘ ዘመነኛ የሚያስተጋባው ቃል ነው። አጀብ! ያውም ለብቻ ቆሞ።

አንድ ቀን ሳይሞላ!?
ወደ ነበረ ሆድ፣ ወደ ዛሬ ጥላ
ከነፍን
ታለፍን
እኔና ዘመኔ
ሀሳብና ህይወት፣ ሆነውብን ቅኔ፤


እነሆ ዘመን እንደ ጥላ እያለፈ ነው። ቀን ቀንን እየተካ እየተሸበለለ እልም ይላል። የሰው ልጅ እግሮች ወደ ሞት ይሰግራሉ።

ይሄ ሁሉ የሚጥመለመል ትውልድ አንድ ቀን እንኳን ኖሮ አያልፍም። አንድ ቀን ማለት ባህርይው ብዙ ነውና። በተለይ ለገጣሚማ አንድ ቀን ውሉ ብዙ ነው።

እነሆ የፀሐይ መግባትና መውጣት በቀን የተተለመ አይደለምን። ፀሐይስ ምንድን ነው ቢሉ ብርሃን አይደለምን? በብርሃን ለመመላለስ የታደለ ትውልድማ ምንኛ የበቃ፣ የነቃ ነው?
ትናንት ላይ ለመድረስ ስንባክን፣ ነበርን ለመሻገር ስንዳክር ይሄው አንዲት እለት እንኳን አልሞላንም። መክነፋችን ፣ መትመማችን፣ ከነበር ላለመሻገር መሆኑ አያስቆዝምም ወይ?

እንደ ዋዛ ያለፍነው እልፍ ነው። ከነገ ለመድረስ ስንንጠራራ ከትናንት ጥላ አንዲት ጋት አልተሻገርንም። ዘመን እንደ ጥላ እያለፈ፣ ጊዜ እንደ አቡጀዲ እየተተረተረ እንዴት ሰው ነገን ማየት ያቅተዋል? እንዴት ሰው ብርሃን መመልከት ይከብደዋል?

አጀብ!
የግርንቢጥ
ሰርክ በተቃርኖ
ማን ልቡን ይሰጣል፣ በዋጋ ተምኖ?


አጀብ! ይገርማል እናንትዬ። የሰርክ መባከናችን አያሳዝንም፣ አያስገርምም ወይ? ነገራቸን ሁሉ የግርንቢጥ መሆኑ ምንኛ ያንግበግባል? ልብ ቦታዋ የት ነው? ቅንነት፣ ንጽህና አይደለምን? እሱን የንጹህ ነፍስ አድባርስ እንዴት በዘመን ዋጋ ይተምንታል? ዘመንስ ዋጋው ምን ያህል ነው? የትውልድ ቁዘማ ለልብ ይደርሳልን?

እነሆ መቃቃራችን ለከት የለውም። ጨለማው ያስፈራል። ጭካኔው ያስደነብራል። ልብ አልባ ሰው መሆን ይገማሸራል። ሰውነት ያለ ልብ ምንድን ነው? ልብ የአስተውሎት ሁሉ አድባር አይደለምን? ታዲያ ሰው መሆንን፣ አስተውሎትን የተነጠቀ ዘመን ምን ይባላል? ልብን በዲናር መዝኖ ለሚንከላወስ ድንጉጥ ዘመን ማርከሻው ምንድን ነው? በጨለማ የተሰነገ ልቡን አቅፎ ለየብቻው ለሚርበተበት ትውልድ ዘመንስ ዋጋው ምን ያህል ነው?

እንገዛ ነበር
እኛም ባገር ዋጋ፣ ልብን ከሥጋ እኩል
ቃል ያጠፋውን ስም፣ ላይስቅለን ነገር ከምንኮለኩል።
(አቡዬን)


መፅሀፍ -አያምንምና ቀድሞም ያልካደ
ደራሲ- ታዲዮስ አዲሱ

@zephilosophy
2025/05/13 03:18:12
Back to Top
HTML Embed Code: