tgoop.com/Zephilosophy/1054
Last Update:
የጠየቁ ተሻግረው አሻገሩን
ስንቱ ይሁን የፖሟ ፍሬ ስትወድቅ እየተመለከተ “ለምን? እና እንዴት? ሳይል ያለፈ! አንድ ሰው ግን ጠየቀ፤ አይዛክ ኒውተን፡፡ ኒውተን አእምሮቸውን በተገቢው ተጠቅመው ማለትም ማወቅን ሽተው፣ ያወቁትንም ለወግ አብቅተውና ለማዕረግ አድርሰው ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ከተረፉት መካከል በምሳሌነት ሊነሳ የሚችል ግለሰብ ነው። ይህ ሳይንቲስት “በምን ምክንያት?፣ ከምን የተነሳ?' ብሎ፤ በመጠየቅ መንገድ ተጉዞ ምላሾችን ፈለገና ስለ መሬት ስበት እንዲገባን አደረገን። የፍጥነት እና የኃይል ምጥነት እንዲሁም የአድራጊ እና ተደራጊ እኩልነት ሕጎችን አጥንቶ ሚስጥራትን ገለጠልን። ይህን ማድረግ የቻለው አእምሮን በሚገባ ለመጠቀም ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል የብልህ ምርጫ የሆነውን መጠየቅን በመምረጡ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ይህን መንገድ በመምረጥ ብልህነታቸውን ካስመስከሩ መሃከል በምሳሌነት ኒውተንን ብጠቅስም በተመሳሳይ በመጠየቅ መንገድ ተራምደው መዳረሻቸውን ተሻጋሪ እና አሻጋሪ ያደረጉ ሌሎችም አሉ። ኾኖም አሳዛኙ ነገር ለተፈጠረባቸው ጥያቄ መልስ ለማግኝት ዳክረው እውቀትን ያገኙ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ፈላስፎች በርካታ አሊያም በቂ የሚባል አለመሆናቸው ነው። ግና ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኚህ በቁጥር ውስን የሆኑ ብልሆች ለምን እንዴት የት ብለው በመጠየቃቸው እና ጥቂት የማይባል ምላሾችን ፈልገው በማግኝታቸው ዓለመ ሰማያትን፣ ምድራችንን እና ማንነታችንን እንድናውቅ ረድተውናል፤ እየረዱንም ይገኛሉ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተን እንዴት ዘላቂ መሆን እንደምንችል በምርምር ውጤታቸው አስተምረውናል። ታመን እንድንድን እና እድሜያችንን እንዲዘልቅ መንገድ ጠርገውልናል። ኑሯችን በኋላቀርነት ገመድ ተተብትቦ እንዳይቀር፣ አኗኗራችን ምቹ እንዲሆን፣ እመርታችን እንዲጎለብት እና ዕይታችን እንዲሰፋ አድርገዋል።
አሁንም ቢኾን የመጠየቅ ጉዞን መከተል እንዳለበት ተረድቶ የወሰነ እንዲሁም ወስኖ መራመድ የጀመረ ሰው መዳረሻው ከላይ በምሳሌነት ካየነው የኒውተን ታሪክ የተለየ አይሆንም። እንግዲህ ይህን ያወቀ ተጓዥ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማግኝት እንደሚችል ያምናል፤ ያውቃልም። ይህ መንገደኛ ማምለጫ የለሽ በሚመስል ወጥመድ ውስጥ ቢገኝ እንኳን መውጫ እና ማምለጫ ዘዴን ያበጃል እንጂ በፍጹም ተስፋ አይቆርጥም፡፡ እንዲህ ዓይነት ተራማጅ ሰው መሬት ላይ የማያወርደው ህልም እንደሌለው ከእውነቶቹ አንዱ ነው፡፡ ወደ ኋላ ሊጎቱት የሚችሉ እልፍ አእላፍ ነገሮች እንደሚገጥሙት ቀድሞዎንም ያውቃል። ነገር ግን መሮጥ ቢያቅተው ተራምዶ፣ መራመድ ቢሳነው ተንፏቆ፣ መንፏቀቅ ቢያቅተው ወደ ፊት ወድቆ ካለመበት ይደርሳል፤ አሸናፊም ይሆናል። አሸናፊም ሲሆን ከራሱ አልፎ ለብዙዎች በነገሮቹ ኹሉ ይተርፋል።
✍️ፍሬው ማሩፍ
📚ጥያቄዎቹ
@zephilosophy
BY ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
Share with your friend now:
tgoop.com/Zephilosophy/1054