tgoop.com/Zephilosophy/1069
Last Update:
ብርሃናዊና ፅልመታዊ
ደራሲ-ስብሃት ገ/እግዚአብሔር
መኖር-ማንበብ - መፃፍ። እዚህ ላይ ገፀባህሪ የሚባለው ፍጡር ይመጣና ራሱን ያስተዋውቃል። ፔሲሚስት Pessimist ነው። በአማርኛ ምን እንደሚባል ቃሉን እስክንፈልግ ድረስ ተቃራኒው ኦፕቲሚስት Optimist ማንሳት የማይቀር ነው። እንዲህ ይላል። ግማሽ ብርጭቆ ወይን ጠጅ ቢያሳዩዋቸው ኦኘቲሚስት ለመሙላት ግማሽ ጐደለው ሲል አቶ ፔስሚስት ግን ገና ግማሽ ብርጭቆ ይቀራል ይላል።
የዲክ ግሬጐሪ አባት ደግሞ አስቀድሞ ማን እየቀዳ እንደሆነ ማወቅ ያሻል ይላሉ።
ነብሳችን በፔሲሚስትና በኦፕቲሚስትነት መሀከል እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ብርሃናዊነትና ዕልመታዊነት ይፈራረቁብናል። እቺ ምድራዊት ህይወታችን ስንኖራት የሲኦልና የገነት ስብጥርጥር ትመስላለች። ራብ ክፉኛ ሲሞረሙረን ጊዜዋ አንገብጋቢት ሲኦል ብትሆንም፤ አግኝተን ስንበላ አግኝተን ስንበላ ደግሞ ምግቡ መጣፈጡ የገነት ያህል ነው። ውሀ ጥም ለረዥም ጊዜ ሲያቃጥለን ጊዜው የሲኦል በመሆኑ ቢከፋንም፤ ውሀ አግኝተን ስንጠጣበት ገነት ሲበዛ መጣፈጥዋን እናውቃለን። ከአቅም ውጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሽንታችን ቢወጥረንና ከዚያም እየባሰበት ሄዶ ፊኛችን ሊፈነዳ እየቃጣ ቆይቶ ቆይቶ በለስ ቢታረቀንና ሽንታችንን ብንሸና ያቺ እፎይታ
የገነት ሌላ ገፅታ ናት።
እንደ መፈላሰፍ ቢያሰኛቸው ፔሲሚስቱ ንጉስ
ሰሎሞንን ይጠቅሳሉ። “ከቆሙት የሞቱት ይሻላሉ፤ ከሞቱት ደግሞ ጭራሹኑ ያልተፈጠሩት ይሻላሉ። ከንቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው።” ኖረን ኖረን ማብቂያችን ሞት እስከሆነ ድረስ እንዴትስ ብንኖር ምን ልዩነት ያመጣል?
“ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባህር ይሄዳሉ፣ ባህሩ ግን አይሞላም። ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ።ነገር ሁሉ ያደክማል፣ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፣ አይን ከማየት አይጠግብም፣ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፣ ለኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሱት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። ከፀሀይ በታች የተሰራውን ስራ ሁሉ አየሁ፣ እነሆ ሁሉ ከንቱ ነው። ነፋስንም እንደመከተል ነው። ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፤ ጐደሎም ይሞላ ዘንድ አይችልም።
...
ጥበብና እብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፤ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደመከተል እንደሆነ አስተዋልሁ። በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና እውቀትንም የሚጨምር ሀዘንን ይጨምራልና...
... ልጄ የሰራቻትን ስራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ተመለከትሁ፣ እነሆ ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሀይ በታችም ትርፍ አልነበረም...!!"
ብርሀናማው ኦፕትሚስት የበኩሉን ይቀጥላል። እየለመድነው መሄዳችን መውለድ ምንኛ የሚያስደንቅ ተአምር መሆኑ እየተረሳን ይሄዳል እንጂ ከወንዱና ከሴቷ መተቃቀፍ ህፃኑ መመንጨቱ ማደጉ በጣም የሚገርም ነው። በየእንስሳቱ በየእፅዋቱ ተአምራት መባዛቱ። የህይወትን ችቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፉ ማለፍ።
የአፍላነት እድሜያችን ወደነበረው ወደ ህፃንነታችን እንመለስና እናቴን ከየት መጣሁ ስላት ወልጄህ ነው ትለኛለች። አንቺስ ከየት መጣሽ? እናቴ ወለደችኝ። እሷስ ከየት መጣች?እናቷ ወለደቻት። ማለቂያ የለውም? ሄዋንን እግዚአብሄር ፈጠራት። እሱስ ከየት መጣ? እሱማ ፈጣሪ ነው። እሺ እሱንስ ማን ፈጠረው? እሱማ አልተፈጠረም ፈጣሪ ነው። እሺ ከየት መጣ ኧይ!? ተወኝ እንግዲህ አታድርቀኝ!
በአዛውንትነት እድሜያችንም ከጥያቄ ወደ ጥያቄ እየነጠርን እንሄድ እንሄድና በመጨረሻ ፍጥጥ! መልስ የለም።
በአዳም ሀረግ ብንሄድ ወይም በኢቮሉሽን (በዝግመታዊ ለውጥ) ብንጓዘው የመጨረሻው ጥያቄያችን “ይሄ ሁሉ መዋለድ መፈጣጠር እንዴት ተጀመረ? የጀማሪውስ ጀማሪ ማን ወይም ምንድነው? ምንም ይሁን። ብቻ ሂደቱ ተጀምሯል። በራሳችን ላይ እያየነው ነው። ከአለመኖር ወደ መኖር መጥተናል። ቀጥሎ እንግዲህ በጊዜ ውስጥ ነብሳችን የኖረባትን ስጋችንን እና ያኖረችን ምድራችንን ተሰናብታ ለዘለአለም ወደምንኖርበት ሰማይ ቤት ታርጋለች። ሂደቷን ለመቀጠል። እቺ የመጨረሻዋ ምኞት ናት የሚሉ ቢኖሩ የመፈጠር ወይም የመወለድን ተአምር በገዛ ራሳቸው ሂደት ያዩት መሆኑን የማይገነዘቡ ወይም የረሱ ናቸው። እንጂ ካለመኖር ወደ መኖር (ከአልቦ ወደ ቦ) የነጠረ ተአምር በመሞት ሌላ ተአምር ከመኖር ወደ ዘለአለማዊ ህይወት ሊነጥር ለምን አይችልም? ተስፋ አለ። እምነትም አለ። የዛፍ ፍሬ ያንን የማናውቀው መነሻና መድረሻችንን የሚያውቅ ሀይል በማመንዋ ትረግፋለች። በእምነት ስትጠብቅ ሰንብታ ዝናብ ይመጣላታል። በእምነት ቅጠልዋ ብቅ ትላለች ከፀሀይ ጋር የፈጠራ ስራዋን ትቀጥላለች...
እነዚህ ብርሃናዊና ዕልመታዊ ተቃራኒ ገፀባህሪያት ከውስጣችን ተወስደው በማህበራዊና በአለማዊ ገፅታ ሲታዩ ወደ ሩቅ ምስራቅ ወደ ህንድ ወደ ቻይና አስተሳሰብ ይወስዱናል። ቀንና ሌት፣ ላይና ታች፣ ወንድና ሴት፣ በጋና ክረምት፣ ራብና ጥጋብ፣ እጥረትና ርዝመት፣ርቀትና ቅርበት፣ ደስታና ሀዘን፣ ብርድና ሙቀት...ሁለት ሁለት መሬትና ሰማይ
እነዚህ ሁሉት ሁለቶች መሐልኮ የሚመሳሰል ሶስተኛ አለ። ሶስተኛውን ማወቅ ግን የፈጣሪውን ምስጢር ገልጦ ማየት ስለሚሆን ለኛ ለፍጡራን ክልክል ነው።
ምናልባት እነሱ ሁለት፣ ሁለት እየሆኑ ያሉት እኔ ሶስተኛቸው ወይ እነሱ የፈጠሩኝ ወይ እኔ የፈጠርኳቸው ወይ በየተራ ያኛውም ይኸኛውም። ክልክል ነው!!
@zephilosophy
BY ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
Share with your friend now:
tgoop.com/Zephilosophy/1069