tgoop.com/yenetube/54698
Last Update:
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ ምርጫ ቦርድ “ነጻና ገለልተኛ” ሆኖ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫው ለማስፈጸም “አንዳችም አስቻይ ሁኔታ የለም” አለ!
የስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያካተተው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ነጻና ገለልተኛ ሆኖ” 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫው ለማስፈጸም “አንዳችም አስቻይ ሁኔታ የለም” ሲል ገለጸ።ኮከሱ፤ ሰኔ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ የምርጫ ቦርድን “በወገኝተኝነት” እና “ለገዢው ፓርቲ በታዛዥነት” ከሷል። በዚህም "የገዢው ፓርቲ አሸናፊነት አስቀድሞ የሚታወቅ ነው" ብሏል።
መግለጫው፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከነባር አመራሮቹ “ሶሰቱን (60 በመቶ) ለመቀየር ጫፍ መድረሱን እያሳወቀን ነው” ብሏል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ “ልምድ በሌላችው ኮሚሽነሮችና በወቅታዊው የፖለቲካ ያለመረጋጋት፣ የግጭትና ጦርነት ውጥረትና ሁለንተናዊ ውስብስብ ተጨባጭ ሁኔታ” ውስጥ የሚደረግ ምርጫ “ጣጣና መዘዙ” እንደሚያስከትሉ አስጠንቅቋል።በመሆኑም በዚህ ተጨባጭ እውነታ ምርጫ ቦርድ "ነጻና ገለልተኛ" ሆኖ ምርጫውን ለማስፈጸም "አንዳችም አስቻይ ሁኔታ የለም" ያለው ኮከሱ፤ “ጉዳዩ ወደከፋ አደጋና ትርምስ እንዳንገባ በእጅጉ የሚያሳስብና የሚያሰጋ ነው” ሲል በአጽንዕኦት ገልጿል።
ኮከስ ከምርጫ ቦርድ በተጨማሪ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይም ትችት ሰንዝሯል። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የቀረቡ የማሻሻያ ኃሣቦችና የተነሱ ጥያቄዎች “ቦታ ሳይሰጣቸው”፣ እንዲሁም የኮሚሽነሮች ሹመት “የብልጽግናውን አዋጅ እንኳ ያልተከተለና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎትና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው” ብሏል።በመሆኑ የተሰጠውን ከፍተኛ ተግባርና ኃላፊነት “በህግ፣ በዕውቀትና እውነት በነጻነትና ገለልተኝነት በሚዛናዊነት ከአገራዊ ተልዕኮው አንጻር ለመፈጸም ይቸገራል” ሲል ገልጿል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከምስረታው ጀምሮ ኮሚሽኑ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎችና ባከናወናቸው ተግባራት ኮከሱ ያነሳቸውን ችግሮች የሚያረጋግጡ አፈጻጸሞች፣ በተለይም የኮከሱን “የመፍትሄ ኃሳቦች ከመቀበል ይልቅ እንደተጻራሪና ተቃዋሚው በማየት ሲያገለኝ ቆይቷል” በማለት ከሷል፡፡አክሎም፤ “በያዘው አግላይ አካሄድ ቀጥሎ”፤ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሥራውን “ሊያጠናቅቅ ቀርቶ አጀንዳ አሰባስቦ ባለመጨረሱ” የአንድ ዓመት ተጨማሪ ዕድሜ ተሰጥቶታል ሲል ተችቷል።
Via AS
@YeneTube @FikerAssefa
BY YeneTube
Share with your friend now:
tgoop.com/yenetube/54698