Telegram Web
🌾 ታዛዥነትና ተዘክሮተ እግዚአብሔር 🌾
🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃🍃

አባ ዮሐንስ ኃፂር ከሚታወቅባቸው መልካም ምግባራት መካከል የሚጠቀሱለት ናቸው ታዛዥነትና ተዘክሮተ እግዚአብሔር፡፡ አንደ ቀን አባ ባሞይ ዮሐንስ ኃፂርን የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማ እስክታፈራ ድረስ ውኃ እንዲያጠጣት አዘዘው፡፡ ያለማንገራገር በትኅትና ሆኖ አሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እያመላለሰ ያጠጣ ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመት ያቺ በትር ለምልማና አብባ ያማረ ፍሬ አፈራች፡፡ አባ ባሞይ በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ፡፡ ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ መነኮሳት እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው፡፡ መነኮሳቱም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ አደነቁ፡፡ ለቅን እና ታዛዥ ሰው ይህን ጸጋ የሰጠ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፡፡

"መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፡፡" ምሳሌ 12፤2


🌿🌹🌿🌹🌿🌹🌿🌹🌿🌹🌿🌹
🕊 🕊 🕊 🕊 🕊

ቃለ ሕይወትን ያሰማን

@Learn_with_John
🕊

† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓለ ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 † ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ † 🕊

† ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን መጠንቆል ነው::

ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ:: ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ የምትላቸው::

🕊 ቅዱስ ተክለ-ሃይማኖት ሐዋርያዊ 🕊


[ ልደት ]

መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ-ዘአብ ካህኑና እግዚእ-ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ : በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል : ጸጋ ዘአብን ከሞት : እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት ፳፬, በ፲፪፻፮ (፲፩፻፺፮) ሲሆን የተወለዱት ታሕሳስ ፳፬, በ፲፪፻፯ (፲፩፻፺፯) ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

[ ዕድገት ]

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው " ፍሥሃ_ጽዮን " ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን [ብሉያት: ሐዲሳትን] ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

[ መጠራት ]

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ ፦

"ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

[ አገልግሎት ]

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ ( ጽላልሽ ) አካባቢ ብቻ በ፲ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያንጊዜ ኢትዮዽያ ፪ መልክ ነበራት::

፩.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::

፪.ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን [ጠንቁዋዮችን] አጥፍተዋል::

[ ገዳማዊ ሕይወት ]

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ፫ ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ፲፪ ዓመታት : በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ፯ ዓመታት : በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ፯ ዓመታት: በአጠቃላይ ለ፳፮ ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ ዞረሬ ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ፳፪ ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም ፮ ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ፯ ዓመታት ጸልየዋል::

[ ስድስት ክንፍ ]

ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-

¤ በቤተ መቅደስ ብስራቱን
¤ በቤተ ልሔም ልደቱን
¤ በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
¤ በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
¤ በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደሰማይ አሳረገቻቸው::

በዚያም :-

¤ የብርሃን ዐይን ተቀብለው
¤ ፮ ክንፍ አብቅለው
¤ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
¤ ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
¤ ከ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
¤ ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
¤ "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

[ ተአምራት ]

የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::

† ሙት አንስተዋል ፥ ድውያንን ፈውሰዋል ፥ አጋንንትን አሳደዋል ፥ እሳትን ጨብጠዋል፥ በክንፍ በረዋል ፥ ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

[ ዕረፍት ]

ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ፺፱ ዓመት: ከ፰ ወር: ከ፩ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬, በ፲፫፻፮ (፲፪፻፺፮) ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: ፲ ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

ይህች ዕለት ለጽንሰታቸው መታሰቢያ በዓል ናት፡፡
††† አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::

† መጋቢት ፳፬ [24] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩. ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት [ጽንሰቱ]
፪. ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
፫. ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

† ወርኀዊ በዓላት
፩. ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
፪. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፫. ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
፬. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮. ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ
† "በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል::" † [ምሳሌ.፲፥፮)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


🕊 💖 🕊
+ Mark of a True Christian +
“What is the mark of a Christian? It is to watch daily and hourly and to stand prepared in the state of total responsiveness pleasing to God, knowing that the Lord will come at an hour that he does not expect.”
St. Basil The Great
“የክርስቲያን መለያው [ምልክቱ] ምንድን ነው? ባልጠበቀው ሰዓት ጌታ እንደሚመጣ አስቦ በየዕለቱ በየሰዓቱ ነቅቶ መጠበቁ እና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅቶ መቆሙ ነው”
[ቅ. ባስልዮስ]
@Learn_with_John
"ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን"
🍂🍃🍃🍂🍃🍂🍃🍂🍃🍂🍃🍂🍃


🪵 "እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።"
(ሮሜ 12: 5)*

🪵 በቋንቋ፣ በትምህርት፣ በጎሳ፣ በኑሮ፣ በደረጃ ልንለያይ እንችላለን፤ ነገር ግን በክርስቶስ ካመንበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ህብረት፣ አካል ሆነናል።*

🪵 ልናደርጋቸው፣ ልንተገብራቸው፣ ልናተርፍባቸው. . . የሚገቡ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኩል፤ በፀጋ ስጦታነት የሰጠን ነገሮች፦*

👉 1- አገልግሎት

ለሌሎች እንትጋ፤ ያዘኑትን እናፅናና፣ የተጠሙ የተራቡ እናብላ.... እግዚአብሔር በሰጠን ፀጋ እንትጋ! እናትርፍ!

👉2- መምከር

- የእግዚአብሔርን ቃል መነሻ በማድረግ... የመምከር ፀጋ ያለው ክፉዎችን፣ ኃጢአተኞችን፣ በተሳሳተ ጎዳና ያሉትን፣ ታናናሾቹን. . . በመምከር ልንተጋ ይገባል።

👉3- የሚሰጥ

- በልግስና፣ ሳይሰስት፣ ደስ እያለው. . . ይስጥ!

👉4- የሚገዛ

- የሚገዛ ያለ ስንፍና በትጋት ይምራ!
- ስንፍና ያፈርሳል፣ ይበትናል፣ መከራ ያመጣል!
- መሪዎች በትጋት ግዙ!

👉5- የሚምር

- የሚምር በደስታ፣ በፍጹም ይቅርታ፣ ቂም ባለመያዝ. . . ይማር!

*ሮሜ 12 ሙሉውን አንብቡት!*

🪵 እግዚአብሔር ዝም ብሎ አልተወንም፤ ብዙ ስጦታዎች ሰቶናል።

🪵 የሚያገለግለው በአገልግሎት ይትጋ! የሚመክረው በመምከር ይትጋ! የሚሰጥም በልግስና ይስጥ! የሚገዛም በትጋት ይምራ! የሚምርም በደስታ ይማር!*

🪵 በክርስቶስ አንድ አካል መሆናችንን አምነን፤ ሌሎችን ይቅር እያልን፤ በእግዚአብሔር ምህረት ተጠብቀን እንድንኖር የእግዚአብሔር ፍቃድ ይሁን!*


👉 መጋቤ ብሉይ መልአክ ጌታነህ

@Learn_with_John
እንኳን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን፤ ለፈጣሪያችንና ለአዳኛችን መድኀኔ ዓለም ጥንተ ስቅለት ክብረ በዓል አደረሳችሁ፥ አደረሰን፡፡
#ጥንተ_ስቀለት
#ክርስቶስ_የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን #ከሆነ _እንደገና_በሌላ_ጊዜ_በዓለ_ስቅለትን_ማክበር_ለምን_አስፈለገ?
#ጥንተ_ትንሣኤ

#ጥንተ_ስቀለት
የጥንተ ስቅለቱ የመታሰቢያ በዓል በሚከበርበት በመጋቢት ፳፯ ቀን ሰማያዊ አምላክ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራዎችን የተቀበለበትና በሞቱ ሞትን ሽሮ የአዳምን ዘር ሁሉ ከሞት ሞት ያዳነበት፣ ለዓለሙ ሁሉ ፍቅሩን የገለጠበት፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ዓለምን ነፃ ያወጣበት፣ ሕማማተ መስቀልን በትዕግሥት ተቀብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው #በገዛ_ፈቃዱ የለየበት የስቅለቱና የሞቱ መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ጥንተ ስቅለት ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓሉም በዓለ መድኃኔዓለም እየተባለ በየዓመቱ #በመድኃኔዓለም ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ ይከበራል ፡፡ የመጋቢት ጽንሰት ( ብሥራት ) ታሕሣስ 22 እንደሚከብረሁ ሁሉ ማለት ነው ፡፡
#ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ከሆነ እንደገና በሌላ ጊዜ በዓለ ስቅለትን ማክበር ለምን አስፈለገ?
ክርስቶስ የተሰቀለው በዕለተ ዓርብ ሲሆን ከመቃብር የተነሣውም በዕለተ እሑድ በመሆኑ #ስቅለት ከዕለተ ዓርብ፣ #ትንሣኤም ከዕለተ እሑድ፣ #ዕርገት ደግሞ ከዕለተ ሐሙስ እንዳይወጡ፤ ሌሎቹም በዓላትና አጽዋማት በተወሰነላቸው ቀን እንዲውሉ ማድረግ ይቻል ዘንድ የቀድሞ አባቶችና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሰባት አዕዋዳት አዘጋጅተው እና ቀምረው ሁሉም ሥርዓቱን ጠብቆ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቀን እንዲከበር የወሰኑ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ቀን በየዓመቱ እየታሰበ በዓለ ስቅለቱ ደግሞ ከሰሙነ ሕማማቱ ጋር በዓመት አንድ ጊዜ በዕለተ ዓርብ በጾምና በጸሎት እንዲሁም በአክፍሎትና በስግደት እንዲከበር በማድረግ ሕግና ሥርዓት ስለሠሩ በዚሁ መሠረት ይፈጻማል::
#ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነው የጌታችን #የጽንሰቱ_በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ቀን ከመሆኑ የተነሣ በዓሉን በዓል ተጭኖት ነው እንጂ ፫ኛው ቀን መጋቢት ፳፱ኝም ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት #ጥንተ_ትንሣኤ በመሆኑ እንደ ጥንተ ስቅለቱ ሁሉ ጥንተ ትንሣኤውም ከበዓለ ጽንሰቱ ጋር አብሮ የሚታሰብ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡
#በኢትዮጵያ_በዋነኛነትና_በግንባር_ቀደምትነት_የስቅለት_በዓል_የሚከበርበት
#ታላቁ ገዳም #ዋልድባ (ዋሊ)፡፡
#142 ዓመታትን ያስቈጠረው ጥንታዊው የጮቢ ደብረ መድኀኒት መድኀኔ ዓለም፡፡ በ1868ዓ.ም. የተመሠረተ፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በጀልዱ ወረዳ በጮቢ የሚገኝ፡፡
#በሃገራችን ከሚገኙ የመድኀኔዓለም ገዳማትና አድባራት ጥቂቶቹ፤
፤ ዋልድባ አበረንታት መድኀኔዓለም ገዳምና
ኤልሻማ ደብረ ማኅቶት መድኀኔዓለም ቤ.ክ.
፠ አንድ ላይ ያሉት፤
✤1. ዋልድባ አበረንታት መድኀኔዓለም ገዳም፤
✤2.ላሊበላ መድኀኔዓለም
✤3. ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም
✤4. መንዳባ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም፤ ጣና
✤5. ሽረ እንዳሥላሴ መድኀኔዓለም ወመስቀል ክብራ
✤6. ቆላድባ መድኀኔዓለም፤ ጎንደር ከተማ አጠገብ
✤7.ቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ፤ (ቦሌ የመድኀኔዓለም ታቦት )
✤ 8.ድሬዳዋ መድኀኔዓለም
✤9.#ቀጨኔ_ደብረ_ሰላም_መድኀኔዓለም ✤ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፤ ፤ የ 110 ዓመታት ዕድሜ ያለው ጥንታዊ የኢያሱ ደብር፡፡ ‹‹በወርቅ ወበዕንቊ ሥርጉት ደብረ ሰላም፤ ወነገሥት ይትቀነዩ ለኪ›› ይህችን ደብረ ሰላምን በመጀመሪያ አቤቶ ኢያሱ /አልጋ ወራሽ ልጅ ኢያሱ/ (ክፍለ ያዕቆብ) በሐምሌ 26 ቀን 1903 ዓ.ም. መሠረታት፤ ንግሥት ዘውዲቱ አሁን ያለውን ሕንፃው ቤ.ክ ጥቅምት 27 ቀን 1913 ዓ.ም አስፈጸመች፡፡)
የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ፤ የላይ ቤት አቋቋም፣ የተክሌ ዝማሜና የሸዋና የራሱ የደብሩ ቀለም እንደ ወንዝ የሚፈስባት፤ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ቤተ መዘክር (Museum)ና ቤተ መጻሕፍት የሚገኙበት፤ ስዕለት ሰሚ ታቦታት ያሉበት፤ 4ት የሚጠጉ ፈዋሽ ጠበሎች የሚገኙበት፡፡ ጽዶቹ ሳይቀሩ በ72 አርድዕት ቅዱሳን አምሳያ የተተከሉበት፤ በቀድሞ ዘመን መዐዛ ቅዳሴ የተሰኘው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ቅዳሴ በወርኃ ጽጌ የሚቀድስበት፤ 3 ጳጳሳትን ያፈራ፣ ……. ደብር ነው፡፡
✣ ለደብረ ሰላም ይደልዋ ስብሐት፤ እስመ በውስቴታ ኀደረ መድኀኔዓለም (በደብረ ሰላም በውስጧ መድኀኔዓለም ስላደረ ምስጋና ይገባታል፡፡)
10 #መናገሻ_ጋራ_መድኀኔዓለም፤ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት፤ ቀድሞ የቅዳሴ ቤቱን ታላቁ አባት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቀድሞ የልደታ ቤ.ክ) በአካል በመገኘት በመስቀሉ የባረከው፤ በድርሳነ ራጕኤል ላይ የተገለጸና ቅዱስ ራጕኤል የማይለየው፤ በአረማዊው ግራኝ ወረራ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ ካህናቱን መነኮሳቱንና ምዕመናኑን እንደያዘ በምድር ውስጥ ገብቶ የተሰወረበት በሥጋ ዕረፍተ ሞት ያልተገቱ ሥውራን ግሩማን አበው የሚኖሩበት "ዛቲ ይእቲ አምባ ማርያም መካነ ክብሮሙ ወጸሎቶሙ ለቅዱሳን ወለነገሥታተ ኢትዮጵያ በሐ በልዋ ተሳለምዋ ጊሱ ሐቤሃ ኢትርሐቁ እምኔሐ" ብለው አበው ያወደሷት የጸሎት የአርምሞና የትኅርምት ቦታ፡፡
11. #ገዳመ_አባ_ጽጌ_ድንግል (መድኀኔዓለም ቤ.ክ)፤ ማኅሌተ ጽጌ የተደረሰበት ወሎ፤ ወግዲ፤ ወለቃ ወንዝ አጠገብ፤ የበረሃው ዕንቊ ገዳም፤ አባ ጽጌ ድንግል የፈለፈሉት ባለ 3 መቅደስ እጅግ ሰፊ ዋሻ ቤ.ክ፡፡
12. #ደብረ_ቀራንዮ_መድኀኔዓለም ቤ.ክ፥ አዲስ አበባ፤ በአዲስ አበባ ከተመሠረተ ከ1826 ዓ.ም ጀምሮ ፍልሰት ሳያጋጥመው በመቆየቱ፤ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቤ.ክ፡፡ (ነገር ግን በመሃል ፍልሰት እያጋጠማቸው እንጂ በአዲስ አበባ ከ1600 ዓመታት በፊት ደብረ ኤረር፣ የካ ዋሻ ተክለሃይማኖትና /ኋላ የካ ሚካኤል/ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን፤ እንዲሁም እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት መመሥረታቸውን ልብ ይሏል)
#በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋነኛነትና በግንባር ቀደምትነት የስቅለት በዓል የሚከበርባችው ፪ቱ ታላላቅ ገዳማት
፩ኛ. ኢየሩሳሌም ዴር ሡልጣን
፪ኛ. #ዋልድባ (ዋሊ)፡፡

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
•➢ ሼር @Learn_with_John
Audio
ወደ ማደሪያው ገብቼ
በእንግሊዝኛ
#የጌታ_ስቅለት_በአበው

"አደምን የፈጠሩ እጆቹ በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ የማይሞተው ሞተ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡" #ቅዳሴ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

“እጆቹን እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማሥተሥረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፣ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፤ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡” #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ሊቀ_ጳጳስ

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡›› #ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

‹‹ታመመ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፤ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዐት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዛ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ›› #ቅዱስ_ቄርሎስ_ዘእስክንድርያ

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፤ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ›› #ቅዱስ_አቡሊዲስ_ዘሮም

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፤ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፤ እጁን እግሩን ተቸነከረ፤ ጎኑን በጦር ተወጋ፤ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡›› #ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሳሪያ
@Learn_with_john
🔥 ዲያቢሎስ ለዚህ ትውልድ ስለነፃነት ያስተማረው ትምህርት የተሳሳተ ነው። ይህን ትምህርቱንም ተጠቅሞ ሰው የወደደውን ሁሉ ለማድረግ ነፃነት እንዳለው ይነግረዋል።ከዚህ በኋላም ምንም እንኳ ለህብረተሰቡ አደገኛ ፍፃሜ ሊያመጡ ቢችሉም የተለያዩ ሀሳቦችን፣ እምነቶችንና ጠባያትን እርሱ በሚፈልገው መልኩ በዓለሙ ውስጥ ያስፋፋል...እግዚአብሄር የሰውን ልጅ ነፃ አድርጎ ቢፈጥረውም ሊፈፅማቸው የሚገቡትን ትዕዛዛት ሰጥቶታል። በመጨረሻም በሰጠው በዚህ ነፃነት ሌሎችን ወይም ራሱን ሲጎዳበት ከቆየ ነፃነቱን ትክክለኛ አግባብ ባለው መንገድ ስላልተጠቀሙበት እግዚአብሄር ይቀጣዋል።

🔥 ዲያቢሎስ የሚለፍፈው ፍፁም ነፃነት ግን የራሱ የሆኑ የጠባይና የእምነት እንቅፋቶች አሉበት። በባህርይ ወይም በጠባይ ላይ ከሚያመጣው አደገኛ ሁኔታ አንዱን "ሂፒ" በሚሏቸው ሰዎች ወይም ደግሞ አንዳንድ አረማውያን(አህዛብ) ላይ የሚንፀባርቁትን ጠባያት መመልከቱ በቂ ነው።እነዚህ ሰዎች እርቃናቸውን በየጎዳናው ላይ መዘዋወርና ዝሙትን በተገኘው ቦታ በመፈፀም ኅብረተሰቡን የሚያሳፍሩ ናቸው። እነዚህንና የመሳሰሉ መጥፎ ተግባራት ሁሉ ዲያቢሎስ በነፃነት ሽፋን ሰዎችን የሚያታልልበት መንገድ ነው።

ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ
📚የዲያቢሎስ ውጊያዎች
ያላችሁን አስተያየት 👇 ይላኩልን
@JohnDPT27
+ Mark of a True Christian +
“What is the mark of a Christian? It is to watch daily and hourly and to stand prepared in the state of total responsiveness pleasing to God, knowing that the Lord will come at an hour that he does not expect.”
St. Basil The Great
“የክርስቲያን መለያው [ምልክቱ] ምንድን ነው? ባልጠበቀው ሰዓት ጌታ እንደሚመጣ አስቦ በየዕለቱ በየሰዓቱ ነቅቶ መጠበቁ እና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅቶ መቆሙ ነው”
[ቅ. ባስልዮስ]
@Learn_with_John
2025/07/06 18:21:12
Back to Top
HTML Embed Code: