Telegram Web
#በዓለ_ዕረፍቱ_ለሐዋርያው_ቅዱስ_ሲላስ_ረድኡ_ለቅዱስ_ጳውሎስ_ሐዋርያ

ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
¹⁸ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
¹⁹ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤
²⁰ ወደ ገዢዎችም አቅርበው፦ እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።
²¹ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ።
²² ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤
²³ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
²⁴ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።
²⁵ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር
²⁶ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።
²⁷ የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
²⁸ ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ።
²⁹ መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤
³⁰ ወደ ውጭም አውጥቶ፦ ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው።
³¹ እነርሱም፦ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት።
³² ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው።
³³ በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤
³⁴ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ።
#ጥቅምት_16

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ያቃቱ አረፈ፣ ኢትዮጵያውያን የህኑ የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እረድዕ የነበሩት #አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ በዓለ ዕረፍታቸው ነው፣ ለአርባ ስምንት ዓመታት ከሰው ጋር ሳይነጋገሩ በዝምታ ብቻቸው ለኖሩ #ነብር_ሰባት_ዓመት_ውሃ_ሲቀዳላቸው ሲያገለግላቸው የነበሩ ታላቁ አባት #አቡነ_አሮን_ዘአርምሞ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ያቃቱ

ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ዘጠነኛ የሆነ ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ አረፈ።

ከርሱ በፊት የነበረ አባ ብንያሚን በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም ብዙ ችግር ደርሶበታል ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል አንድ መለካዊ ሰው ነበረ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ወደ ዘይድ ሒዶ ብዙ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሁኖ ተሾመ።

ይህንንም አባት አባ ያቃቱን ሊአስጨንቀው ጀመረ በየዓመቱ ግብር ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከእርሱ እስከተቀበለ ድረስ #እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ ይህን አባት እንዲህ አሠቃየው።

በዘመኑም የብዙዎች ቅዱሳን አባቶች አባት የሆነ የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጸመ።

በአንዲት ሌሊትም ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዚህ አባት ተገለጸለት ፍዩም በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ ሰው መነኰስ እንዳለ ነገረው። ሕዝብን በማስተማርና በመምከርም ይረዳው ዘንድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲአስመጣውም አዘዘው ሁለተኛም ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ገለጠለት።

በዚያንም ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሥራውንም ሁሉ አስረከበው ይህንንም አባት ከብዙ ድካም የሚያሳርፈው ሆነ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

#አርኬ "ሰላም ለአባ ያቃቱ ምሉአ ስብሐት ወውዳሴ። እንተ ነሥአ ክብረ ዘየዓቢ እምክብረ ሙሴ። ፈለሰ ዮም በከመ አመሮ መልአከ ቅዳሴ። ዮሐንስሃ ጻድቅ ብእሴ። እምድኅረ ረሰየ መንበሮ ወራሴ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ

አቡነ ኢያሱ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ሸዋ የተነሡ ሲሆን ምንኵስናቸውን ከደብረ ሊባኖሱ ከዕጨጌ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ያስረዳል። ትውልዳቸው አምሐራ ሳይንት ሲሆን መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳምን የመሠረቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።

እርሳቸው የመሠረቱት ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳም በግራኝ ወረራ ሳይወድም ስለቀረ ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ ስለሚገኝና ታላቅ የበረከት ቦታ የቅዱሳን መናኸሪያ ስለሆነ ብዙዎች ነገሥታት ገዳሙን እየሔዱ ተሳልመው በረከት አግኝተውበታል። የአቡነ ኢያሱን ገድላቸውን ከአቡነ ሀብተ ማርያም ገድል ጋር ጣልያናዊው ራይኔሪ በሀገሩ ሮም እንዳተመው ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጽፈዋል። (0s valdo Raineri, Atti di Habta Māryam (†1497) e.di Iyasu (†1508), Santi Monaci Etiopici, Roma 1990 (Or ChrA 235), 165-265.)

የጻድቁ በዓለ ዕረፍታቸው ጥቅምት 16 በገዳሙ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ስለ ጻድቁ ገድል በዝርዝር ተጽፎ አላገኘንም፣ ይልቁንም አቡነ ኢያሱ ስለገደሙት ታላቁ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ ገዳም ነው በብዛት የሚነገረው።

አቡነ ኢያሱ ጀር ስላሴ ከመምጣታቸውም በፊት አስቀድመው በአቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ በተጋድሎ ሲቀመጡ ‹‹ቦታኸ ይኸ አይደለም›› ተብለው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ነው ወደ ጀር #ሥላሴ የመጡት። ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት አካባቢው ባእድ አምልኮ የተስፋፋበት ነበር፣ ነገር ግን ጻድቁ ሕዝቡን ክርስትናን አስተምረው ወደ አምልኮተ #እግዚአብሔር መልሰውታል። የምንኵስናን መሠረት ጥለውበታል። የአቡነ ኢያሱ የዕረፍታቸው ቦታ ደብረ ሊባኖስ ቢሆንም መታሰቢያቸው በመራቤቴ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ይታሰባል። በገዳሙ በክብረ በዓሉ ወቅት ታቦት አይወጣም፣ ከበሮ አይመታም። ምክያቱም ፍጹም የጸሎት የጽሞና ቦታ ስለሆነ ነው።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በደንቢ ግራርጌ ቀበሌ ጀር በሚባል ስፍራ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ ከአዲስ አበባ 137 ኪ.ሜ ከደብረ ብርሃን 91 ኪ.ሜ ከለሚ ከተማ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ከጥንት ጀምሮ ስዉር ገዳም ሆኖ የቆየ ነው። ገዳሙ በ1495 ዓ.ም በዐፄ ናኦድ ዘመነ መንግሥት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጻዲቁ አቡነ ኢያሱ ወደዚህ ቦታ መጥተው መሥርተውታል። በጅረት ታጂቦ ስለሚገኝ ነው ጀር #ሥላሴ የተባለው። የክብር ባለቤት #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በራእይ አስመልክቶ ከመሠረታቸው ገዳማት አንዱ ነው። አቡነ ኢያሱም በገዳሙ በሚገኘው አንድ ትልቅ ዋርካ ሥር ቆመው ይጸልዩ እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ። አሁንም ድረስ ዋርካው በሥፍራው ላይ ሕያው ማስረጃ ሆኖ ይገኛል።

ገዳሙ ከአቡነ ኢያሱ ዕረፍት ከዘመናት በኋላ በግራኝ አህመድ ወረራ ጥቃት ደርሶበት መነኰሳቱም ተበታትነው ለ247 ዓመት ጠፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1747 ዓ.ም አቡነ ዮሴፍ የተባሉት ጻድቅ በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከአምባሰል ተነሥተው መጥተው ገደሉን ቦርቡረው ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና ቅዱሳንን ያሟላ ቤተ መቅደስ በማነጽ ዳግም ገዳሙን በማቅናት የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ ማስቀጠል ችለዋል። በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ቅርሶቹና ነዋየ ቅዱሳቱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አባቶች ሰብስበው በስውር ከቀበሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ የቀበሩበት ቦታ ጠፍቶባቸው ነበር ነገር ግን የወንዙ ውኃ አቅጣጫውን ቀይሮ ሽቅብ ፈስሶ ቅርሶቹ ያሉበትን ቦታ አመላክቷል።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር #ቅድስት_ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም የበርካታ መናንያን አበው በኣት ከመሆኑም ባሻገር የወንዶች ብቻ ገዳም ሲሆን መናንያኑ ከአራዊት ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ነው። ዙሪያው በገደል የተከበበ ሲሆን ወደ ገዳሙ ለመውረድ የዕንጨት መሰላልን ተጠቅሞ መጓዝ ግድ ይላል። ወደ ገዳሙ መግቢያ የሚያስወርደው መሰላል ደቡብ ወሎ ከሚገኘው ከታላቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም መግቢያ ጋር ይመሳሰላል። የመሰላሉ ርዝመት ከ15 ሜትር በላይ ይሆናል።

ገዳሙ ከ #እግዚአብሔር ጋር በሱባዔ ለመገናኘት ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ረድኤተ #እግዚአብሔር ያለበት ቅዱስ ቦታ ነው። ዋሻው የሚከፈተው ዐቢይ ጾም ላይ እና በ #እመቤታችን የፍልሰታ ጾም ወቅት ነው። በዋሻው ውስጥ ሱባዔ የሚያዘው በደረቅ ሽምብራ ቆሎ እና በአንድ ኩባያ በሶ ብቻ ነው። አባቶች በኣት ዘግተው ጾመ ፍልሰታን፣ ጾመ ነቢያትን፣ ጾመ ሐዋሪያትን በይበልጥ በምነና ሕይወት የሚያሳልፉበት የበረከት ገዳም ነው።
በጀር #ሥላሴ የሚገኘው ታሪካዊ ታላቅ ተራራ በልበሊት ኢየሱስን ግራኝ አሕመድ ሲያቃጥል ሁለት በወርቅ የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በፍቃደ #እግዚአብሔር እንደሰወረ አባቶች ይናገራሉ። ይኸም ጥንታዊና ታሪካዊ ተራራ አሁንም በቦታው የሚገኝ ሲሆን በዋሻው ውስጥ የክብር ባለቤት #ጌታችን በስደቱ ወራት ከእናቱ ድንግል #ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰለሜ ጋር ለጥቂት ጊዜ የተቀመጠበት ሲሆን አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በምነና የተጋደሉበት ታላቅ ዋሻ ነው። ዋሻው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ ሲሆን በውስጡ ከ40 በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰወሩበት አባቶች ይናገራሉ።

በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት የግራኝ ሠራዊት አብያተ ክርስቲያናቱን እናጠፋለን ብለው ሲመጡ በተኣምራት ሰምጠው እንደጠፉ አባቶች ያስረዳሉ። አዛዦቹንም በዋሻ ውስጥ የሚገኙት ወፍ የሚያህሉ ተርቦች ነድፈው ጨርሰዋቸዋል። እነዚያ ተርቦች አሁንም ድረስ በገዳሙ ውስጥ ያልተፈቀደ ነገር ሲደረግ በመናደፍና በመከልከል ዋሻውን የሚጠብቁ ሲሆኑ አንዱ ተርብ ከነደፈ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ። ከዚኸም በላይ ዋሻው በነብርም ይጠበቃል።

ገዳሙ ባለብዙ ቃልኪዳን ሲሆን ብዙ ስውራን አበው ዛሬም የሚኖሩበት ትንቢታቸው የማይነጥብ ብዙ ግሁሳን የከተሙበት ነው። ስውራኑ አበው ዛሬም #እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው ይገለጣሉ። ደገኞቹ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት የገዳሙን ክብር በመረዳት ቦታው ድረስ በመሔድ በረከት ይቀበሉ ነበር። ዳግማዊ ምኒሊክ ለጀር #ሥላሴ ገዳምና ለገዳማውያኑ አለኝታ ስለነበሩ በገዳሙ የታሪክ መዝገብ ስማቸው ዘወትር ይነሳል። ግርማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቦታውን ይንከባከቡት የነበረ ሲሆን ለገዳሙ መርጃ የሚሆን አዲስ አበባ ላይ የሚከራይ ቤት አሠርተው በኪራዩ ገቢ ገዳሙ እንዲጠቀም አድርገው ነበር። በአካልም ገዳሙ ድረስ በመሔድ በረከትን ይቀበሉ ነበር።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አሮን_ዘአርምም

መጽሐፍ አሮን ዘከትሞ ወዘአርምሞ ይላችዋል። የትውልድ ሀገራቸው ትግራይ ተንቤን ነው። ለ48 ዓመታት ከሰው ጋር ምንም ሳይነጋገሩ በዝምታ ብቻ የኖሩ ታላቅ አባት ሲሆኑ ቀዳማዊ ዘኢትዮጵያ ከተባሉት የመጀመርያዎቹ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው። ቤተ መቅደስ ገብተው ሲያጥኑ ርግብ ዕጣን ታመጣላቸው ነበር። ምግባር ቱሩፋታቸው እጅግ ያማረው እኚህ አባት በዘመናቸው ድርቅ በሆነ ጊዜ የእህል እጦት ሆኖ ሕዝቡን ሰብስበው እግዚኦታ ካደረሱ በኋላ የሀገሩን ሁሉ ጎተራ በተአምራት በእህል ሞልተው አትረፍርፈውታል። በዚህም አስገራሚ ተአምራቸው ሕዝቡንም ከችግርና ከርሃብ አድነውታል።

አቡነ መድኃኒነ እግዚአ ዘደብረ በንኰል አህያቸውን የበላባቸውን አንበሳ በአህያው ምትክ ሰባት ዓመት ውኃ እንዳስቀዱት ሁሉ አቡነ አሮንም ነብርን ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱ እንዲያገለግላቸው አድርገውታል። ሌሎች የዱር አራዊትም ያገለግሏቸው ነበር። በአንድ ወቅት በሀገሩ ድርቅ ሆኖ ሰው ግማሹ ተሰዶ ግማሹ ደክሞ ስለነበር ጻድቁ ግን የዱር አራዊትን ጠርተው ሠራተኛ አድርገው በማዘዝ ጥንቸልን ውኃ በማስቀዳት፣ ጅብን ጭቃ በማስረገጥ፣ አንበሳን በአናጺነት እንዲሠራ፣ ነብርን ደግሞ አቀባይ በማድረግ እያዘዙ በማሠራት በ #እመቤታችን ስም እጅግ አስደናቂ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 10 ቀን ሠርተዋል። የአቡነ አሮን ዘአርምሞ የአንድነት ገዳማቸው ትግራይ ሽሬ ውስጥ ይገኛል።

#ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_16ና #ከገድላት_አንደበት)
🌹 "በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹

🌹 እንኳን #ለዘመነ_ለማኅሌተ_ጽጌ_ለሦስተኛ_ሳምንት ለዕለተ እሑድ #እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

🌹 #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ ፫ "#ወመኑ_መሐሪ_ዘከማከ፤ ምስለ #ኖኅ_ኪዳነ ዘአቀምከ #ለደቂቀ_እስራኤል መና ዘአውረድከ፤ አዝ፣ #ወበጽጌያት_ምድረ_አሠርጎከ ወሥነ ገዳምኒ ምስለ ቅዱሳኒከ፤ አዝ፣ ወከመ ወሬዛ ኀየል መላትሒሁ ጒርዔሁ መዐርዒር አምሳሉ ዘወይጠል፤ አዝ፣ ሰማየ ወምድረ ዘአንተ ፈጠርከ #ፀሐየ_ወወርኃ_ዘአስተዋደድከ፤ አዝ፣ በከዋክብት ሰማየ ዘከለልከ ወበጽጌያት ምድረ አሠርጎከ፤ አዝ፣ #ቀደሳ_ወአክበራ_አዕበያ_ለሰንበት ወአልዓላ እምኲሉ ዕለት ወመኑ መሐሪ ዘከማከ ወኲሉ ይሴፎ ኪያከ"። #ትርጉም#እንደ_አንተ_ያለ_ይቅር ባይ ማነው? #ከኖኅ_ጋር_ቃል_ኪዳንን ያቆምህ (ያጸናህ)፤ #ለእስራኤል_ልጆች_መናን_ያወረድህ#በአበቦች_ውበት_ምድርን_ያስጌጥክ፣ የገዳምን ውበት ከቅዱሳንህ ጋር ነው አስጌጥክ እንደ ኃይለኛ ጎልማሳ እንደ ዋሊያ ጉረሮው ጣፋጭ ነው ሰማይና ምድርን የፈጠርህ፣ #ፀሐይና_ጨረቃን_ያስማማህ፣ በከዋክብት ሰማይን የጋረድክ፣ በአበቦችን አሳየ፣ ቁጥር የሌለው ብዙ አበቦችን አሳይ፣ ለሕዝብህ በረከትን ስጥ፣ #ሰንበትን_ቀደሳት_አከበራት_ከዕለታት_ሁሉ_ከፍ ከፍ አደረጋት እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋል። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ

                    
#የጥቅምት_16_ግጻዌ

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤
² ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
³ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፥ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤
⁴ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።
⁵ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና።
⁶ እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን።
⁷ ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ።
⁸ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን።
⁹ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
² እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።
³ በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።
⁴ ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።
⁵ በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤
²⁰ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።
²¹ እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና።
²² ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና።
²³ ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው።
²⁴ እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥
²⁵ በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ፦ አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ?
²⁶ የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ።
²⁷-²⁸ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ።
²⁹-³⁰ አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ። ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ #እግዚአብሔር"። መዝ 91፥12-13።

#ትርጉም፦ "ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በ #እግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ"። መዝ 91፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_16_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር።
² ፈሪሳውያንም አይተው፦ እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።
³-⁴ እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?
⁵ ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?
⁶ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
⁷ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።
⁸ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።
⁹ ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ።
¹⁰ እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት።
¹¹ እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?
¹² እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው።
¹³ ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች።
¹⁴ ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
¹⁵ ጌታችን ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤
¹⁶-¹⁷ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦
¹⁸ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።
¹⁹ አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።
²⁰ ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።
²¹ አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የ #ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል፣ ዕለተ ሰንበት፣ የማኅሌተ ጽጌ ሦስተኛ ሳምንትና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_17

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ #ቅዱስ_እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ነው፣ የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት #ቅድስት_ነቢይት_ሐና የተወለደችበት ነው፣ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ፊልያስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ የከበረ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ካልዕ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቀዳሜ_ሰማዕት_ቅዱስ_እስጢፋኖስ

ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነ የከበረ እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ናት።

ለዚህም ለከበረ እስጢፋኖስ የ #እግዚአብሔርን ኃይልና ጸጋ የተመላ ሰው እንደነበረና በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ እንደነበረ የሐዋርያት ሥራ የተባለ መጽሐፍ ስለርሱ ምስክር ሆነ።

ከዚህም በኋላ አይሁድ ቀኑበት የሐሰት ምስክሮች የሚሆኑ ሰዎችንም አስነሡበት ይህን ሰው በሙሴና በ #እግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃልን ሲናገር ሰምተነዋል እንዲሉ ሐሰትን አስተማሩአቸው። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጸሐፊዎችንም አነሣሡአቸው አዳርሱን ብለው ከበው እየጐተቱ ወደ ሸንጎ ወሰዱት።

የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት እነርሱም ይህ ሰው በቤተ መቅደስ ላይ በኦሪትም ላይ ስድብን ሲናገር ተው ብንለው እምቢ አለ። የናዝሬቱ #ኢየሱስ ቤተ መቅደሳችሁን ያፈርሰዋል ሙሴ የሰጣችሁን ኦሪታችሁንም ይሽራል ሲል ሰምተነዋል አሉ።

በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ተመለከቱት ፊቱንም የ #እግዚአብሔርን መልአክ ፊት ሁኖ አዩት። ሊቀ ካህናቱም እውነት ነውን እንዲህ አልክ አለው። እርሱም እንዲህ አለ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ስሙ ወደ ካራን ከመምጣቱ አስቀድሞ በሶርያ ወንዞች መካከል ሳለ ለአባታችን ለአብርሃም የክብር ባለቤት #እግዚአብሔር ተገለጠለት። ካገርህ ውጣ ከዘመዶችህም ተለይ እኔ ወደማሳይህ ሀገርም ና አለው።

ከዚህም በኋላ ከከላውዴዎን ወጥቶ በካራን ተቀመጠ አባቱም ከሞተ በኋላ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች አገር አመጣው። ከዚህም በኋላ የግዝረትን ሥርዓት ሰጠው ይስሐቅንም በወለደው ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገዘረው እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን ገዘረው ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን ነገድ አባቶችን ገዘረ።

የቀደሙ አባቶቻችንም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብጽ አገር ሸጡት #እግዚአብሔር ግን አብሮት ነበር። ከመከራው ሁሉ አዳነው በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ዕውቀትን መወደድን ሰጠው በግብጽ አገር ሁሉና በቤቱ ሁሉ ላይ ሾመው። ነገርም በማስረዘም በሰሎሞን እጅ እስከተሠራችው ቤተ መቅደስ ያለውን ተረከላቸው።

ከዚህም በኋላ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እናንተም እንደ አባቶቻችሁ ዘወትር #መንፈስ_ቅዱስን የምታሳዝኑት ዐይነ ልቡናችሁ የታወረ ዕዝነ ልቡናችሁ የደነቈረ አንገተ ደንዳኖች አላቸው። አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ያልገደሉት ማን አለ እናንተ ክዳችሁ የገደላችሁትን የአምላክን መምጣት አስቀድመው የነገሩዋችሁን ገደላችኋቸው።

በመላእክት ሥርዓት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁም። ይህንንም ሰምተው ተበሳጩ ልባቸውም ተናደደ ተነሣሣ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። በእስጢፋኖስም #መንፈስ_ቅዱስ አደረበት ሰማይም ተከፍቶ #ኢየሱስ_በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የ #እግዚአብሔርን ክብር አየ። እነሆ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በ #እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ አለ።

ጆሮአቸውን ይዘው በታላቅ ድምፅ ጮኹ በአንድነትም ከበው ጐተቱት። እየጐተቱም ከከተማ ወደ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገደሉት የገደሉትም ሰዎች ልብሳቸውን ሳውል ለሚባል ጐልማሳ ልጅ ያስጠብቁ ነበር። #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል እያለ ሲጸልይ እስጢፋኖስን በደንጊያ ወገሩት።

ዘለፍለፍ ባለ ጊዜም ድምፁን ከፍ አድርጎ አቤቱ ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው በደልም አታድርግባቸው ይህንንም ብሎ አረፈ። ደጋግ ሰዎችም መጥተው የእስጢፋኖስን ሥጋ ወስደው ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ነቢይት_ሐና

ዳግመኛም በዚህች ቀን የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት ቅድስት ነቢይት ሐና ተወለደች።

ይችም ቅድስት ከሌዊ ነገድ ናት የታኅርም ልጅ ሕልቃና አገባት ፍናና የምትባልም ሌላ ሚስት አለችው እርሷም ወላድ በመሆኗ ሐና ልጅ ስለሌላት መካንም ስለሆነች ሁልጊዜ ትገዳደራት ነበር።

ሐና ግን ፈጽማ በማዘን አትበላም አትጠጣም ባሏ ሕልቃናም ያረጋጋታል ማረጋጋቱንም አልተቀበለችውም በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመንም ወደ ቤተ #እግዚአብሔር ወጣች እያለቀሰችና እያዘነች በ #እግዚአብሔር ፊት ጸለየች እንዲህም ብላ ስለትን ተሳለች አቤቱ ልጅ የሰጠኸኝ እንደሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የሚያገለግል አደርገዋለሁ።

ካህኑ ኤሊም አያትና እርሷ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንደ ሰከረች አሰበ እርሷ በዝምታ በልቧ ትጸልይ ነበርና በቊጣና በግሣጼ የወይን ጠጅ ጠጥተሽ ወደዚህ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ለምን መጣሽ አሁን ሒጂ ስካርሺን በእንቅልፍ አስወግጂ አላት።

እርሷም እንዲህ አለችው የወይን ጠጅ ከቶ አልጠጣሁም ልጅ ያጣሁ በመሆኔ በልቤ አዝናለሁ እንጂ ካህን ኤሊም አጽናናት እንዲሁም ብሎ ባረካት የእስራኤል ፈጣሪ የለመንሽውን ይስጥሽ በሰላም ሒጂ በቃሉም አምና ወደ ቤቷ ገባች።

ከዚህም በኋላ ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ጡትንም በአስጣለችው ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ይዛው ወጣች ወደ ካህን ኤሊም አቀረበችውና እንዲህ ብላ አስረዳችው ከአሁን በፊት ልጅን ይሰጠኝ ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ስጸልይና ስለምን ያየኸኝ ሴት ነኝ ልመናዬንም ሰምቶ ይህን ልጅ ሰጠኝ አሁንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለ #እግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ አመጣሁት።

ከዚህም በኋላ ሐና #እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ልቤ በ #እግዚአብሔር አምኖ ጸና የሚለውን ጸሎትና ትንቢት እስከ መጨረሻው ተናገረች። ይቺም በዳዊት መዝሙር መጨረሻ ከሙሴ መኀልይ ቀጥላ ተጽፋለች።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግላ በሰላም ጥቅምት 6 አርፋለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፊልያስ_ሰማዕት

ዳግመኛም በዚች ቀን የሀገረ ቀምስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ፊልያስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህንንም ቅዱስ በመኰንኑ ቊልቊልያኖስ ዘመን ወደ ፍርድ አደባባይ አቀረቡት ቊልቊልያኖስም ለአማልክት ሠዋ አለው። ፊልያስም እኔ ከብቻው #እግዚአብሔር በቀር ለአማልክት አልሠዋም አለ። ቊልቊልያኖስም #እግዚአብሔር ምን አይነት መሥዋዕት ይሻል አለ ቅዱስ ፊልያስም ቅን ትሑት የሆነ ንጹሕ ልቡናን ዕውነተኛ ፍርድን ቁም ነገርን እንዲህ ያለ መሥዋዕትን #እግዚአብሔር ይወዳል አለው።

ቊልቊልያኖስም የምትጋደል ስለ ነፍስ ነው ወይስ ስለ ሥጋ አለ ቅዱስ ፊልያስም ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ ነው እነርሱ በአንድነት ይነሣሉና አለ። ቊልቊልያኖስም የምትወዳት ሚስት የምትወዳቸው ልጆች ወይም ወንድምና ዘመድ አለህን አለው ቅዱስ ፊልያስም ከሁሉም የ #እግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል አለ።
ቊልቊልያኖስም #እግዚአብሔር ከበጎ ሥራ የሠራው ምንድን ነው አለ ቅዱስ ፊልያስም #እግዚአብሔር ያደረገልን ይህ ነው ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጠረልን። ዳግመኛም ከጠላታችን ከሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ሰው ሁኖ ተወለደ የሕይወት መንገድንም በዓለም ውስጥ ተመላልሶ አስተማረ መከራንም በሥጋው ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ በሦስተኛውም ቀን ተነሥቶ በአርባ ቀን ዐረገ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ይህን ሁሉ ስለ እኛ አደረገ።

ቊልቊልያኖስም አምላክ ይሰቀላልን ይሞታልን አለ ቅዱስ ፊልያስም አዎን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ፍቅር ሞተ አለው።

ቊልቊልያኖስም እንዲህ አለው እኔ እንዳከበርኩህ ልጣላህም እንዳልፈለግሁ አላወቅህምን አንተ በወገን የከበርክ እንደሆንክ አውቃለሁና አሁንም ለአማልክት ሠዋ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት አለው። ቅዱስ ፊልያስም እኔን ደስ ማሰኘት ከወደድክ እንዲያሰቃዩኝና እንዲገድሉኝ እዘዝ አለው በዚያንም ጊዜ በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት አዘዘ።

ሊገድሉት ሲወስዱትም ዘመዶቹና የሀገር ታላላቆች ወደርሱ መጡ ለመኰንኑም በመታዘዝ ለአማልክት እንዲሠዋ እጆቹን እግሮቹን እየሳሙ ለመኑት። እርሱ ግን የ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስን መከራ #መስቀልን ልሸከም እሔዳለሁና እናንተ አሳሳቾች ከእኔ ወግዱ ብሎ ገሠጻቸው።

ከሚገድሉበትም ሲደርስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እጆቹን ዘርግቶ ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጸለየ ሕዝቡን አደራ ወደ #ጌታ አስጠበቀና ተሰናበተ ከዚህም በኋላ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መስተጋድል አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ሊቅ_ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

በዚችም ዕለት የኑሲስ ኤጲስቆጶስ የባስልዮስ ወንድም የከበረ ጎርጎርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

ይህም ቅዱስ ጎርጎርዮስ እጅግ የተማረ አዋቂ ነበረ በደሴቶችም ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እነሆ በዚህ ወር በአሥራ አምስት ቀን የሆነውን ከገድሉ ጥቂት እንጽፋለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ መሥዋዕቱን ለማክበር በሚቀድስ ጊዜ በመሠዊያው ላይ ሲወርድ #መንፈስ_ቅዱስን የሚያየው ሆነ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኪሩብን አየው በደረቱም ውስጥ አቀፈው በመሠዊያውም ላይ ሳለ ወደ ዝምታና ተደሞ አደረሰው ሰዎችም ሁሉ ሥጋዊ እንቅልፍ የሚያንቀላፋ ይመስላቸው ነበር።

በኤጲስቆጶስነት ሹመት ሠላሳ ሦስት ዘመናት በተፈጸሙለት ጊዜ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ እርሱ ከተጋድሎ ብዛት የተነሣ በጽኑ ደዌ የሚታመም ሁኖ ነበርና በቅዱስ ባስልዮስ መምጣት ደስ አለው።

ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደ ልማዱ ሊቀድስ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ የከበረች ድንግል እመቤታችን #ማርያም ተገለጸችለትና ዛሬ ወደኔ ትመጣለህ አለችው የቊርባኑንም ቅዳሴ ሲጨርስ ሕዝቡ በቀናች ሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ይመክራቸውና ያስተምራቸው ዘንድ ወንድሙን ባስልዮስን ለመነው እርሱም እንደሚያንቀላፋ ሆነ በቀሰቀሱትም ጊዜ ሙቶ አገኙት ቅዱስ ባስልዮስም ሣጥን እንዲሠሩለት አዘዛቸው። ጸሎታትንም በመጸለይ መዝሙራትንም በመዘመር በማመስገንም እንደሚገባ ገንዞ በመቃብር ውስጥ አኖሩት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ትኑር ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ካልዕ

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮስቆሮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ። ይህም አባት በዘመኑ ካሉ ትውልድ እርሱን የሚመስል ያልተገኘ በጠባዩ ቅን የዋህ በእውቀቱ አስተዋይ በበጎ ሥራው ፍጹም የሆነ ነው።

#መንፈስ_ቅዱስ ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ መልእክትን ጽፎ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጰሳት ቅዱስ ሳዊሮስ ላካት ። እርሱም ልዩ ሦስት የሆኑ #ሥላሴ በመለኮት አንድ እንደሆኑ እየገለጠና እያሳሰበ ነው። ስለ ወልደ #እግዚአብሔርም ሰው መሆን እርሱ ፍጹም ሥጋን ነባቢትና ለባዊት ነፍስን ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም እንደ ነሣ በመለኮቱና በትስብእቱም አካል ያለው አንድ ልጅ እንደሆነ ከተዋሕዶውም በኋላ በሥራው ሁሉ የማይለያይ ጭማሪ ወይም ጉድለት የሌለው ነው።

መልእክቱም ወደ ቅዱስ አባት ሳዊሮስ በደረሰች ጊዜ አነበባትና ፈጽሞ ደስ ተሰኘባት ለአንጾኪያም ሕዝብ አስተማረባት ሁሉም ደስ አለቸው።

ከዚህም በኋላ አባ ሳዊሮስ ለአባ ዲዮስቆሮስ የመልእክቱን መልስ እንዲህ ብሎ ጻፈ ። በኒቅያ ከተማ ተሰብስበው ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ቅዱሳን አባቶቻችን በቀናች ሃይማኖት አጽንተው የሠሩዋትን ቤተ ክርስቲያኑን እንድትጠብቅ ለዚች ለከበረች አገልግሎት የመረጠህ #እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ዳግመኛም በዚሁ እንዲጸና ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ እንዳይል አስገነዘበው ደግሞም በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ሕዝቡን ሁል ጊዜ አስተምራቸው አለው።

የአባ ሳዊሮስም መልእክት ወደ አባ ዲዮስቆሮስ በደረሰች ጊዜ ደስ ተሰኘባት በሁሉ ቦታም እንዲአስተምሩባት አዘዘ ይህም አባት ሕዝቡን ሁል ጊዜ የሚያስተምራቸው ሆነ። ሁል ጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ያስተምራቸዋል ኤጲስቆጶሳቱንና ካህናቱንም መንጋዎቻቸውን ስለ መጠበቅ ያዛቸዋል መልካም አገልግሎቱንም አድርሶ #እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_17)
🌹#የጥቅምት_17_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጢሞቴዎስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³ ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤
⁴ እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።
⁵ በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።
⁶ ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ።
⁷ እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።
⁸ እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤
⁹ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
¹⁰-¹¹ አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።
¹² ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።
¹³ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤
¹⁴ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵⁴ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
⁵⁵ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦
⁵⁶ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።
⁵⁷ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥
⁵⁸ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ።
⁵⁹ እስጢፋኖስም፦ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር።
⁶⁰ ተንበርክኮም፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ፦ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
   "ወጽንሐሐኒ ኢትሠምር። መሥዋዕቱ ለ #እግዚአብሔር መንፈስ የዋህ። ልበ ትሑተ ወየዋሃ ኢይሜንን #እግዚአብሔር"። መዝ. 50፥17

#ትርጉም፦ "የ #እግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ #እግዚአብሔር አይንቅም"።

ወይም👇

"ልበ ንጹሕ ፍጥር ሊተ እግዚኦ። መንፈሰ ርቱዕ ሐዲስ ውስተ ከርሥየ። ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ"። መዝ.50÷10

#ትርጉም፦ "አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ"። መዝ.50÷10
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ።
² አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና፦
³ እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤
⁴ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ።
⁵ አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ፦ ይህማ የምታዩት ሁሉ፥
⁶ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ እስጢፋስ የሢመት በዓል፣ የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2025/10/26 14:22:57
Back to Top
HTML Embed Code: