tgoop.com/DrYonasLakew/2611
Last Update:
ሠላም ዶር ዮኒ! መጽሐፉን ጨርሸዉ በስተመጨረሻ ያለኝን ሃሳብ ላካፍል ብዬ ነው
ቀላሉን ነገር አታካብድ መጽሐፍ ላይ የግሌ ዕይታ
ቀላሉን ነገር አካበድክ አትበሉኝና😁…ይህ መጽሐፍ አጠገባችን ያሉትን ትናንሽ የሚመስሉ ግን ሲተገበሩ ትላልቅ አዎንታዊ ዉጤቶችን የሚያመጡ መርሆችን በማወቅ እንዴት ህይወተችንን ቀለል አድርገን በደስታ መሙላት፤ ስኬታማ እና ዘና ያለ ሠላማዊ ህይወት መኖር እንደምንችል የሚያሳየን ተግባር ተኮር መጽሐፍ ሆኖ አገኝቸዋለሁ። ሃሳቦቹም አስተማሪ ምሳሌዎች እና ታሪኮችን ባካተቱ እና በጣም በቀላል አቀራረብ በቀረቡ ከ1 እስከ 100 በተዘረዘሩ መርሆች ዉስጥ የተካተቱ ናቸዉ።
አሁን ባለንበት ዓለም ቀላል የመረጃ ፍሰት መኖሩ ብቻዉን የምናየዉን፣ የምንሰማዉን፣ የሚያስደስተንን እና የሚያስከፋን-የሚያበግነንን ነገር አብዝቶታል። ብቻ በዚህም ሆነ በአጠቃላይ ህይወታችን የሚያስፈልገንን እንዴት መለየት እንደምንችል እና በምንፈልገዉ ነገር ላይ ብቻ እንዴት ማተኮር እንደምንችል እና ያለዉን ፋይዳ ይህ መጽሐፍ ያስረዳናል። ጥቂት ሃሳቦችን ለማየት ያክል ምስጋናና ትዕግስት ያላቸዉን ሀይል እና ጠቀሜታ ያሳያል ፤ ምርጫችንን እንዴት ለአዎንታዊ ፋይዳ እንደምንጠቀም ያስረዳናል ፤ የጊዜ አረዳድን እና አጠቃቀምን ያብራራል ፤ እራስን እንዴት እና ለምን መቀበል እንዳለብን በምክንያት ያስረዳል ፤ የጊዜያዊ ስሜት ዉጣ ወረድን እንደምንችል ያስተምረናል ወዘተ። በአጭሩ ሆደ ሰፊነት ለዘላቂ ዉስጣዊ ሠላም የሚል ይመስላል።
በሁሉም ረገድ መጽሐፉ የዘነጋነዉን እያስተወሰን ፤ ዋጋ የነሳናቸዉን ጉዳዮች ዋጋ እያሳየን ፤ ያላወቅነዉን እያስተማረን በሆደ ሰፊነት ወደ ደስተኛ፣ ቅን፣ የዋህ እና ሠላማዊ ማንነት የሚመራ ድንቅ መጽሐፍ ሆኖ አገኝቸዋለሁ። ቀላሉን የማናካብድ ከባዱን ነገር የማያንኳስስ በሳል ማንነት እንዲኖረን ያለን ደግሞ ዋጋዉን እንድንረዳ የሚያደርግ አስተማሪ የአሁኑ እና የመጪዉ ትዉልድ መጽሐፍ ይመስለኛል። ተደጋግሞ ሊነበብ የሚገባ ነዉ። የተጠቀሱ ልምምዶች ደግሞ ተደጋግሞ ቢተገበሩ ትልቁን ዉጤት የሚያስገኙ ናቸዉ።
ስለሁሉም ዶር ዮናስ ላቀዉ ከምትሰራቸዉ ግሩም ስራዎች ጎን ለጎን ይህን ድንቅ መጽሐፍ ተርጉመህ ስላቀረብክልን ከልብ አመሰግናለሁ።
ምስጋናዉ ገ/ሚካኤል
BY Mental wellness የአእምሮ ጤና
Share with your friend now:
tgoop.com/DrYonasLakew/2611