tgoop.com/yadengillej/1512
Last Update:
📜✨ሰሙነ ሕማማት✨📜
፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት
(የሕማማት ሳምንት) በማለት ትዘክረዋለች። ሕማማት የሚለው ቃል ሐመ፣ ታመመ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው። ሰሙነ ሕማማት በላቲን Hebdomas Sancta or Hebdomas Maior፣ በግሪክ ደግሞ Ἁγία καὶ Μεγάλη Ἑβδομάς , Hagia kai Megale Hebdomas (ታላቁ ሳምንት) ተብሎ ይጠራል። በኛ ደግሞ ሰሙነ ሕማማት ይባላል። ሰሙነ ሕማማት ከሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ጌታችንን ለመያዝ አይሁድ የመከሩበት፣ ምክራቸውን ያፀኑበት፣ ጌታችንን ሳይዙ እህል ላለመቅመስ ክፉ መሐላ የተማማሉበት፣ጌታችንን የያዙበት፣ የገረፉበት እና በዕለተ ዐርብ በቀራንዮ የሰቀሉበት ሳምንት ይህ ሰሙነ ሕማማት ተብሎ ይጠራል። ሰሙነ ሕማማት እስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር። በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ። ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል። የምሥራቃውያን
(ኦርየንታል) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን አርባውን ጾም ጨርሰን
ከሆሣዕና ቀጥሎ ያለ አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን።
፡
በሌላ በኩል ሰሙነ ሕማማት የኦሪት ዘመን ምሳሌም ነው። በዘመነ ኦሪት (አዳም ከገነት ከተባረረበት እስከ ጌታችን በቤተ ልሔም እስከተወለደበት ዘመን) የሰው ልጅ የጽድቅ ሥራው ለመንግሥተ ሰማያት የማያበቃው ነበር። ይልቁንም ነቢዩ ‘’ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ’’ ኢሳ. 64፥6 እንዳለ የአዳም ዘር በሙሉ እስከ ዕለተ ዐርብ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ እስካዳነን ድረስ በዲያብሎስ ባርነት ሥር ነበርንና ሰሞነ ሕማማትም የዘመነ ፍዳ ምሳሌ ነው። ይህንንም ለማሰብ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደርስም፣ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ሥርዓተ ተክሊል፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተሰርዮም አይደረግም፣ ጥምቀተ ክርስትና አይፈጸምም፣ በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታሕ ማለት አይኖርም። ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ።በሰሞነ ሕማማት ከዚህ ዓለም በሞት የሚለይ ሰውም የፍትሐት ጸሎት አይደረግለትም። ይህ ማለት በዕለተ ሆሣዕና በአካለ ሥጋ እያለን ካህናት አባቶቻችን የፍትሐት ጸሎት ያደርጉልናል።
፡
ሰሙነ ሕማማት የተለየ ሳምንት ነውና፣ እንኳን ሥጋዊ ደስታና ሳቅ ጨዋታ መንፈሳዊ ደስታም የሚገባ አይደለም፡፡
በሰሙነ ሕማማት ምእመናን እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ አይለዋወጡም። ይህም ይሁዳ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ ሰጥቷልና ያንን ለማሰብ ነው። በሰሞነ ሕማማት መጻሕፍተ ኦሪት፣ መጻሕፍተ ነቢያት፣ የዳዊት መዝሙር ይነበባል። በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን በመጓዝ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ። "እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን" ኢሳ. 53፥4-7 ተብሎ የተነገረው ቃል ተፈጽሞ ጌታችን ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ደረት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚዘከርበት ሳምንት ነው። ነቢያት መቼ ወደ ዚህ ዓለም መጥተህ ከዓመተ ፍዳ ታድነናለህ? ሲሉ የተማፀኑበት ጸሎት፣ የጌታችንን ስለእኛ ሲል የመያዙን፣ የመገረፉን እና የመሰቀሉን ነገር ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው በትንቢት መነፀር እየተመለከቱ የተጻፉ የነቢያት መጻሕፍት ይነበባሉ፣ ይጸለያሉ።
፡
ከቤተ ክርስቲያናችን ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ውስጥ የረቡዕ እና ዐርብ ጾም የሚጾምበት ምክንያትም በሰሙነ ሕማማት አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ከዕለተ ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ
ክፉ ምክር ሲመክሩ ቆይተው በዕለተ ረቡዕ ምክራቸውን ያፀኑበት ቀን ሲሆን በዕለተ ዐርብ ደግሞ ጌታችንን የሰቀሉበት ቀን ስለሆነ ነው። በሰሞነ ሕማማት ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማት የተባለ መጽሐፍ ይነበባል። ግብረ ሕማማት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለዘሩ ድኅነት የተቀበለውን መከራ
የሚዘክር መጽሐፍ ነው፡፡ ግብረ ሕማማት ማለት የሕመም፣ የመከራ ሥራ ማለት ነው፡፡ የጌታን መከራውን ሥቃዩን ሕማሙን በሰዓትና በጊዜ ከፍሎ የሚናገር፣ እንዲሁም ምን በማን መጸለይ እንደሚገባውም በዝርዝር የሚገልጽ በመሆኑና የጌታችንን ሕማም በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት በዋነኝነት አገልግሎት ላይ የሚውል በመሆኑ ግብረ ሕማማት ተባለ። መጽሐፉ ግብረ ሕማማት እንዲባል
በውስጡ የታዘዘ መሆኑን የአማርኛው ትርጉም መቅድም ይገልጻል። በግብረ
ሕማማት መግቢያ ላይ ‘ሐዋርያት ለስብከት ወንጌል በሚፋጠኑበት ጊዜ፣ ስለ እርሱ ስለ ጌታችን ታሪኩና ተአምራቱን ይከታተሉ ከነበሩት መካከል የተከበሩና የታወቁ ሊቃውንት በኢንፎስና በገማልያል እጅ ተፅፎ በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም በክብር ቦታ ተቀምጦ የተገኘ ነው’ ይላል።
፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት 'ሐመ' ማለት ታመመ ማለት በመሆኑ የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው። ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው። ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው። በዚህ ሳምንት በመራብ፣ በመጠማት፣ በመውጣት፣ በመውረድ፣ በመስገድ፣ በመጸለይ፣ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል።
✨ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት ሳምንት ያድርግልን! ለበዓለ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን!
✍... መ/ር ክብሮም ካሣ
ሰንበት፦ ፬/፰/፳፻፲፪ ዓ/ም
#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
@popeshenoudaa
@popeshenoudaa
BY 💒ዓምደ ሃይማኖት✝️
Share with your friend now:
tgoop.com/yadengillej/1512