tgoop.com/tseomm/6544
Last Update:
👉ዮናስ ጎርፌ የተባለው የፕሮቴስታንት ግለሰብ የጻፈው ነው። ተጠንቅቃችሁ በጥንቃቈ አንብቡት
የኦርቶዶክሱ ጳጳስ ቅድስት ድንግል ማርያምን ”ቤዛ” አይደለችም የሚለውን ጉዳይ ማንሳታቸው ሞቅ ያለ ሞቅታ በእኛው ቤት ሰሞኑን ገጥሞት ሳይ፣ “ለመሆኑ ይህ ጉዳይ የእኛ ስነ መለኮት ጥያቄ ጉዳይ ነው? ካልሆነስ እንደው እኛን የዚህን ያህል ከንክኖን የጨዋታው ማእከላዊ ኮከብ ለመሆን ለምን ፈለግን?” የሚለው እንደው ሲያሳስበኝ ከርሟል። በተሀድሶ ስም (ተሀድሶ የተም ሀገር ሰርቶ አያውቅም፣ እነ ሉተርም ካቶሊክን አላደሱም ጥለው ወጡ እንጂ) የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን መንኮታኮት ማየት የሚፈልግ አለ ማለት ነው? ብዬ እንድታዘብም አድርጎኛል።
እንደገባኝ መነኩሴው "ማርያም ቤዛ ልትሆን አትችልም" የሚል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቀኖና ወጪ የሆነ ትምህርት አስተምረው ነበር የሚል ክስ ነው ዋናው ጉዳይ። በኃላም እንደሰማንው ጳጳሱ ለዚህ ጉዳይ መልስ ሲሰጡ ነገሩ እሳቸው ካሉት ሀሳብ ውጪ (out of context) ተመንዝሮብኛል እንጂ እኔ እንደዛ አላምንም የሚል ማስተባበያ ሰጥተዋል። ይህ ማስተባበያቸው የኛን ቤት ሰዎች ብዙም ያስደስተ አይመስልም።
የእኔ ሀሳብ ያለው እሳቸው ያሉትና በኃላም እንደሱ ማለቴ አይደለም በሚለው ውዝግብ ላይ አይደለም። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን ጠበቅ አድርጋ ይዛ ማስተካከያ እንዲደረግበት ማድረጓ ቀነኖዋ ነውና ልክ አድርጋለች። የእኛዎቹም ቤት ሰወች በተለያዩ አስተምህሮቶች ላይ የሚያምኑትንና የቆሙበትን ቀነኖ በትክክል ቢያውቁ ከእነ እዩ ጩፋ ጋር መድረክና ድርጅት ባልተጋሩ ነበር። ይህ ቤተ ፕሮቲስታንቱ (ጰንጠቆስጤው) ትምህርት ሊወስድበት የሚገባ ነገር ነው።
የፕሮቲስታንት/ጰነጠቆስጤው ማሕበረሰብ ማርያም “ቤዛ ናት አይደለችም” የሚለው አስተምህሮት የሚመለከተው ካልሆነ ይህን ያህል በሌላ ቤተ እምነት ውስጥ ገብቶ ለመፈት ፈት ምን ግድ አለው? የሚለው ጥያቄ ለእኔ ሚዛን ይደፋል። የክርስቶስ ልብ አለን እንደሚል አማኝ (ጰንጠቆስጤው) በዛኛው በኩል ክርስቲያን ወንድሞቹ (ኦርቶዶክሳውያኑ) የተካረረ ጠብ ውስጥ ሲገቡ (ጉዳዩ ስነ መለኮታዊ ብቻ ሳይሆን ጳጳሱ ፖለቲከኛ ሹመኛም ናቸው የሚል አስቀያሚ አዝማሚያም ይዞ ስለነበር) አባቶቹዋ ወደተሻል መግባባት እንዲመጡ መጸለይና ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመናጋት እንድትጠበቅ በቅን ልብ ሊመኝ በተገባው ነበር።
ይህ ትውልድ ለዚች ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ባለእዳ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባዋል፣ እስከነ ችግሯ። ጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተች ቤተ ክርስቲያን ባትሆን ዛሬ ኢትዮጵያ ፍጹም በእስልምና አስተምህሮት ውስጥ በወደቅች ነበር። ለዚህ ብዙ ርቆ መሄድ አያስፈልግም፣ ግብጽ፣ ቱኒሲያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ቱርክ ሌሎችም የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ሙሉ በሙሉ የክርስቲያን ሀገራት (መዲናዎች) የነበሩ አሁን ግን ከግብጽ 10 ፐርስንት በቀር ፍጹም ክርስትና ጠፍቷል። ኢትዮጵያ ግን በዚህች ቤተ ክርስቲያን ብዙ ስደትና እንግልት (የነገስታቱም ጣልቃ ገብነት ሳይዘነጋ) ክርስትናን በተጠናከረ መልኩ እዚህ አድርሰዋለች። በዚህም የተነሳ የፕሮቲስታንቱ፣ ማናልባት ከሰማንያ በመቶ በላይ አበል የተገኘው ከዚችው ቤተ እምነት ከፈለሰ ሕዝብ ነው። ሀገሪቷ ከላይ እንደዘረዝርኳቸው ሀገራት በእስልምና ተውጣ ቢሆን ኖሮ ይህ እድል በጭራሽ ባለተገኘ ነበር። ፕሮቲስታንቱ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ባለእዳ ነው። RESPECT THAT!!!!
ይህ ትውልድ ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ቢኖር፣ እኳን ሁለት ሺህ አመተ የዘለቀች ቤተ ክርስቲያን ይቅርና (በተለያየ የአስተምህሮት ውጥንቅጥ ውስጥ ማለፏ ማለቴ ነው) የዛሬ 500 አመት የመጣው የተሀድሶ እንቅስቃሴ በሺዎችና በሺዎች ቦታ ተሰነጣጥቆ የክርስትና መዳከም ዋና ምክንያት ሆኗል። አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ለዚህ ሕያው ምስክር ነው። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲነሳ በፕሮቴስታንት (በሉተራዊ) ቤተ እምነት ውስጥ እንዳለ ሰው በታሪካችን ይህን ያህል ደረታችንን ነፍተን የሚያስኮፍሰንና ሌላውን (ኦርቶዶክሱን/ካቶሊኩን) በንቀት አይን እንድናይ የሚያረገን የሞራል ብቃት ያለው ማሕበረ ሰብ አይደለንም። የሰሞኑንን የሟቹን የካቶሊኩን ጳጳስ የሀብት ታሪክ ለሰማ (በባንካቸው ውስጥ 100 ዶላር ብቻ ነው የተገኘው) የኛዎቹ የእግዜር ሰዎች የሀብት ማማና የፎቅ ብዛት ወይም የሚለዋውጡትን መኪናና ሱፍ ብዛት ላየ እንደው በየትኛው የሞራል ሆነ የመንፈሳዊ ብቃቱ ነው ይህ ህዝብ (ፕሮቴስታንቱ/ጰንጠቆስጤው) በነዚህ ሰወች ላይ አፉን ማላቀቅ የሚችለው?! (የኛን ሀገር ጳጳሳትም የሀብት ማማ አልዘነጋሁትም። እርሱም ሌላ ማፈርያ ነው)
ነጥቤ ሲሰበሰብ፣ በወንድሞቻችንና በአባቶቻችን መካከል የተፈጠረውን የስነ መለኮት አስተምህሮ ልዩነት ጉዳይ ሲነሳ፣ ብንችል በዝምታ እየጸለይንላቸው (የክርስቶስ ልብ ያለው ይህን ነው የሚያደርግ) ጉዳዩን ማየት፣ ካልሆነም ደግሞ በጉዳዩ ላይ የስነ መለኮት interest ካለን (ለምን እንደሚኖረን ግን አይገባኝ፣ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ በፕሮቴስታንቱ መካከል ጥያቄ ሆኖ ሲነሳ ሰምቼ አላውቅም) ጉዳዩን ለራሳችን ሰወች በሚመጥን መልኩ ከመጽሐፍ ቅዱሱም ከቤተ ክርስቲያን ታሪክም እያቀረቡ ማስረዳት ነው እንጂ የሌላውን ቤተ እምነት በሚያዋርድና በሚያንቋሽሽ ሁኒታ ማቅረቡ ልክ አይመስለኝም። ንጽጽር ውስጥም መግባቱ በጭራሽ ልክ አይደለም። ምክንያቱም ሁለት የተለያየ ቀኖና ነውና።
በዚህ ላይ ይህ የማርያም ቤዛነት ጉዳይ (ከማማለድ ጋር የተያያዘ መሆኑ ልብ ይሏል) አዲስ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮት አይደለም። Athanasius of Alexandria (c. 296–373 CE)፣ ወላዲት አምላክ/ Theotokos ("God-bearer" or "Mother of God" የሚለውን አስተምህሮት ሽንጡን ገትሮ የተሟገተ ነው። Ambrose of Milan (c. 340–397 CE) ማርያም ያለሀጢያት (sinless) ነበረች ብሎም አስተምሯል። Gregory of Nyssa (c. 335–395 CE) ደግሞ ስለ አማላጅነቷና በድንግልነቷ ወልዳ በድንግልነቷ እንደኖረች (ከዚያ በኋላ አልወለደችም ማላት ነው) ጽፏል። ከዚያም ቤተ ክርስቲያን (“ቤተ ክርስቲያን” ነው ያልኩት “ካቶሊክ ወይም ኦርቶዶክስ” አላልኩም። በዚያን ጊዜ እንዲህ የሚባል ነገር አልነበረምና። አንዲት ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን-One Apostolic Church ብቻ ነበረችና) በ Council of Ephesus (431 CE): Declared officially that Mary is Theotokos — Mother of God, not just mother of Christ’s human nature. (የፈጣሪ እናት እንጂ የክርስቶስ የስጋው እናት ብቻ አይደለቸም) ብላ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ቀንናለች። (ልብ በል ቤተ ክርስቲያን ነች ይህን የቀነነችው፣ ግለሰብ ጳጳሳት አይደሉም) እንግዲህ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን የነዚህ ጥንት አባቶች አስተምህሮት ተከትዬ ነው የመጣሁት ነው የምትለው። አንዳንዶች፣ በተለይ ከተሀድሶ መጣን ከሚሉት እንደምንሰማው ዘረ ያቆብ ነው ይህቺን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያበላሻት እንድሚሉን አይደለም ታሪክ የሚነግረን።
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6544