tgoop.com/tseomm/6522
Last Update:
ይኸንንም ያነሡት ከውጭ ያሉት አካላት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያነሡትን ለማጥራት ቢሆን ኖሮ ባላስነቀፋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ‘‘አሁን በእኛ ቤትና በሌላ ቦታ እንደትልቅ መጨቃጨቂያ ተደርጎ’ የሚለው አባባል ራሳቸውን ሦስተኛ ወገን አድርገው ያቀረቡት፣ ኦርቶዶክስ ይኸንን የማታምንና የማታውቅ አስመስለው የሚከሱትን ክስ ያስተጋቡበት ሌላው ስሕተታቸው ነው፡፡ በመሠረቱ ለማብራሪያነት ያቀረቡት ጥሩ ቢሆንም በሌላው ቤት ‘አማላጅ ነው’ ሲሉ ምን እያሉ እንደሆነና ለምን እንደምቃወም ላይናገሩ ነገር ነው ጥቅሱን ለክስ ያነሡት፡፡
4ኛ ከ40ኛው ደቂቃ ጀምሮ ስለፍያታዊ ዘየማን ያንሡበትና በዚያው ላይ የትርጓሜ ባሕልና ትውፊትን አጥብቀው የተቃወሙበት ክፍል ነው፡፡ ቀደም ብሎ ከ37ኛ ደቂቃ ጀምሮ በሰሙነ ሕማማቱ የምናደርጋቸውን መከራውን ማሰብን፣ ስግደቱን፣ ምንብባቱን የሚቃወም የሚመስል ንግግር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እኔን በጣም ያስገረመኝና በሕስተት የተሞላው ንግግራቸው ያለው በሚከተለው ውስጥ ነው፣
‘እንኳን ለእኛ ይቅርና በቀኙ የተሰቀለው ፍያታዊ ዘየማንን ታስታውሱታላችሁ? ሉቃ 23፡39 ላይ ያለው፣ ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ትመጽእ በመንግሥትከ በጣም ነው የምወደው ይኸን ሰው እኔ፡፡ እኛ በእንደዚህ ዐይነት መከራ ተይዘን ሳለን፣ በውኑ እግዚአብሔርን አትፈራውምን? እኔና አንተ የሚገባንን ቅጣት ተቀብለናል፣ ይኸ ግን ኃጢአት የለበትም፣ ማን ገለጸለት? ማነው ልቡን ያበራው? ማነው ዐይኑን ያበራው? ሌላ ነገር አይደለም፡፡ ሰማዋ፣ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የሚለውን ቃል ነው፡፡ ሌላውን ድርሰት ተረት ተውት፡፡’
ሊቀ ጳጳሱ ይኸንን የሚሉት ስለፍያታዊ ዘየማን በትርጓሜው ውስጥ ያለውን ማንነቱን በተመለከተ የተቀመጠውን ታሪክና ሐተታ ነው ‘ድርሰትና ተረት’ የሚሉት፡፡ ይኸ የጥራዝ ነጠቆቹ የተሐዲሶን የፕሮቴስታንት ክስ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ንግግራቸውን ይጨርሱና ስለምንተቸው አሁን አባን እንስማቸው፣
‘ስለዚህ ምን አለ ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ትመጽእ በመንግሥትከ፣ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፡፡ አሳስብልኝ አላለም፡፡’
‘አሳስብልኝ አላለም፡’ ሲሉ አማላጅነትን እየተቃወሙ መሆኑን ልብ አድርጉ፡፡ ድምጹ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንት ነው ያልነው ይኸንንና መሰሉን ይዘን ነው፡፡ አሁንም እንስማቸውማ፣
‘በዚያ ያን የተዋረደውን፣ የተሰቀለውን፣ እርቃኑን እንደሱ የተሰቀለውን፣ የመንግሥት ባለቤት መሆኑን አውቆ መለኮታዊ እግዚአብሔር መሆኑን አውቆ፣ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፣ እስኪ እንደሱ እንሁን፣ እግዚአብሔር የዚህ ሰው እድል ይስጠን በእውነት፡፡ በጣም እድለኛ ሽፍታ ነው፡፡ እኛ መቀባባት ስለምንወድ፣ እንደዚህ፣ ተሸክሞ፣ ምርኩዙ ተሰብሮበት፣ እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው፤ ክርስቶስ እኮ ልዩነት ነው፣ ሁለቱ ሽፍቶች እንኳን ተለያዩ በክርስቶስ፣ ለመግደል የተባበሩ ነበር፣ ለመስረቅ አይለያዩም ነበር፤ ለመድፈር አንድ ነበርሩ፤ ችግር አልነበረባቸውም፣ ግን በክርስቶስ ተለያዩ፣ ለምን? ክርስቶስ እውነት ነዋ፡፡ እውነት አንዲት ቅንጣት፣ የማትከፈል፣ ጥያቄ የማይነሣባት፣ ኮሜንት የማይሰጥባት እውነት፣ ጌታው በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፡፡ በዚህ ደረጃ የተዋረደውን ሰው፣ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አውቆ ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለ፡፡ ቤተልሔም ሲወለድና ሰብአ ሰገል ወርቅ እጣን ከርቤ ስያቀርቡለት አልነበረም፣ ፍያታዊ ዘየማን፣ ወደ ግብጽም ሲሰደድ አላየም፣ አልነበረም ፍያታዊ ዘየማን፣ ቃና ዘገሊላ ላይም አልነበረም በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ፣ ደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ አልነበረም፡፡ ሲጠመቅና አባቱ የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው ሲል አላየም አልነበረም፣ ነገር ግን ቀን አገናኛቸው፡፡’
አሁን ይኸንን በስሕተት የተሞላ ንግግራቸው እንተቸው፣ ‘እኛ መቀባባት ስለምንወድ፣ እንደዚህ፣ ተሸክሞ፣ ምርኩዙ ተሰብሮበት፣ እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር!’ የሚለው ንግግራቸው ፍጹም ሰፊ ችግር ያለበት ቁንጽልና ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንት ጩኸት ነው፡፡ ‘እኛ መቀባባት ሰለምንወድ እንጂ’ ያሉት የፍያታዊ ዘየማን ታሪኩ በትርጓሜ መቀመጡንና መነገሩን ነው፡፡ ‘ፍያታዊ ዘየማን እመቤታችን ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ ላይ ካገኟት ሽፍቶች አንዱ ነበር’ የሚለውን ነው፡፡ አሁን ሊቀ ጳጳሱን ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል፣ ለመሆኑ እርስዎ ይኸንን ከመጻሕፍት ስላላገኙት አልቀበሉም እንበል፣ እርስዎስ ‘እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው’ ያሉት በምን ማስረጃ ነው? የዛን ቀን ብቻ ያየው መሆኑን ከየት አገኙት? ሁለቱ ሽፍቶችስ ሲሰርቁ ይተባበሩ እንደነበር አብረው አልነበሩ፣ ከየት አገኙት? የግል ትርጉምና ፍልስፍናዎትን ለማስተላለፍ የተጻፈንና ታሪክን ማጣጣል ምን የሚሉት ነው? ተቃርኖ አይታይዎትም ወይ? ሽፍታው ስለክርስቶስ አይቶም ይሁን ሰምቶ የማያውቅ መሆኑን ከየት ያለተጻፈ ነውና ከየት አመጡት? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ያስገድደናል፡፡ አምስት ገበያ ሕዝብ የሚያክል ይከተለው የነበረን ጌታ፣ የአይሁድና የሮማውያን አለቆች ‘ሕዝቡን ሁሉ ወሰደብን’ ብለው የቀኑበትን እርሱን፣ ሲወለድ የጥበብን ሰዎች ኮከብ የመራቸው እርሱን፣ በመወለዱ የተቆጣ ሄሮድስ ‘እገድለዋለሁ’ ብሎ 2000 ሕጻናትን የፈጀበትንና በይሁዳ ምድር ዐዲስ ክስተት የሆነውን እርሱን፣ ለምድራውያኑ ነገሥታቱ የሥልጣናቸው ተጋሪ መስሎ ጭንቅ የሆነባቸው እርሱን ከሕዝብ ወገን የሆነው ፍያታዊ ዘየማንን እንዲያ በጨበጣና በቆረጣ ‘እርሱ አይቶትም አያውቅም፣ እንዴ የት ያየዋል? እውነቱን ነው እንጂ መናገር! ጌታን የዛን እለት ብቻ ነው ያየው’ ሲሉ አልዘገነነዎትም ወይ? ፍያታዊ ዘየማን እኮ ጎልማሳ፣ ሽፍትነቱን ሐዋርያት ሳይቀሩ የመሰከሩበት ታሪክ ያለው በምድር ላይ የኖረ ሰው ነበር እንጂ በእለተ ዐርብ ድንገት ከዐለት ሥር የበቀለ አይደለም፡፡ ያንን የሽፍታውን የቀደመ ታሪኩን ፈልጎ መዝግቦ ከሥሩ ለማስረዳት ሊቃውንቱ ያደረጉት ጥረት የሚያስደንቅ እንጂ እንዴት የሚያስተች መሰሎት? የዚህ ሁሉ ጣጣ ከውጭ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለጮኹት፣ ጩኸቱን የአባት ሳይሆንና ለተሐዲሶና ፕሮቴስታንት በውክልና የተጮኸ በመሆኑ ነው፡፡
5ኛ በመጨረሻው ከ 47፡20 ጀምሮ ስለመስቀል ያላቸውን ተቃውሞ ያሳዩበትና በትርጉም ከመናፍቃኑ ጋር የተስማሙበት ጠባብ የሆነ ትርጉም ያለበትን ንግግር የተናገሩበት ነው፡፡ ይኸንን ብዙም አልሄድበትም፡፡ ልክ እንደቤዛ ትርጉም መስቀልንም መከራ ብቻ ተብሎ እንድተረጎምና ዕፀ መስቀል ትርጉም የሌለው አስመስለው የተናገሩበት ክፍል ነው፡፡
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6522