tgoop.com/tseomm/6520
Last Update:
በአባ ገብርኤል የስሕተት 'ስብከት' ላይ የቀረበ ሙሉ ትችት
************************************************************
አባ ገብርኤል ከውጭ ወደ ውስጥ ያስተጋቡትን ትችት አዘል፣ በስሕተት የተሞላውን ስብከታቸውን በተመለከተ ትናንት ማታ ከመምህር በረከት ጋር በነበረን የቲክቶክ መርሐ ግብር በሰፊው ዳስሰነዋል፡፡
በዚህ ጽሑፍ በጥልቀት የዳሰስንባቸውን ነጥቦችና ዋና ዋና ትችታቸውን በቲክቶክ ላይ በነበርው ውይይታችን ያነሣነው ቢሆንም ያንን ላልተከታተሉትም ጭምር ይሆን ዘንድ አሰናድቸዋለሁና ተጋበዙ፡፡
በነገራችን ላይ ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጡ መልሶች ላይ እስከ አሁን ባደረኩት ዳሰሰ፣ ‘እመቤታችን ቤዛዊተ ዐለም አይደለችም’ ከሚለው ትችታቸው ውጭ ጠቅላላ ስብከታቸውን ተመልክተው በዚያ ስብከት በኩል ከውጭ ወደ ቤተ ክርስቲያን የተጮኹ የሌላ አካል ድምጾችን በተመለከተ ትችትና አስተያየት ሲሰጥ አላየሁም፡፡
ርብርቡንና የሁሉንም ጥረት ባደንቅም ሁሉም የተረባረበው አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑ ጉዳዩን ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል ባይ ነኝ፡፡ ለዚያ ነው ይኸንን ጽሑፍ ጨርሶ ማንበብ ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳትና የሊቀ ጳጳሱን መልእክት በጠቅላላው ለመረዳት ሊያግዝ ይችላል የምለው፡፡
ሙሉ ቪዲዮውን ተመልክቼ ስጨርስ አባ ገብርኤል ያቀረቧቸው ነቀፋዎች አንድ ቤተ ክርስቲያንን ‘ቤቴ፣ መጠጊያ፣ አካሌ’ ከሚል አባት ወይም መምህር ሳይሆን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ‘ጠላት፣ ሌላ፣ ውጭ’ አድርገው ከሚያዩት፣ ተሐዲሶና ፕሮቴስታንት በተደጋጋሚ የሚጮኹትን ጩኸትና እነሱን ተክተው፣ መስለውና አህለው የጮኹት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ነው ያደረሰኝ፡፡
መግቢያ
*********
ስብከቱን የሰበኩት አባ ገብርኤል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ የሰበኩበት ቦታ ደግሞ ባለሃብቱ አቶ ጸጋየ ለስቅለት ባዘጋጀው የአዳራሽ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ እኔ የተመለከትኩት ስብከት የ51 ደቂቃ ቪዲዮ ነው፡፡
የስብከታቸው ርእስም ‘የሰባ ግብዣ’ የሚል ሲሆን ቅዱሳት መጻሕፍቱን በግእዝ ጠቅሰው፣ በአማርኛ ተርጉመው፣ በቀጥታ ወደ ራሳቸው ትችት የሚያዘነብሉበትን አካሄድ የተከተሉበት ነው፡፡ ርእሳቸውን የመረጡበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኢሳ 25፡ 6 ላይ ያለውን ወይገብር እግዚአብሔር በዝንቱ ደብር ለኲሉ ሕዝብ ከመ ይብልዑ መግዝአ ስቡሐ ወመሥዋዕተ ስሙረ፣ እነሆ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ በዚህ ታላቅ ተራራ የሰባ ግብዣን ያደርጋል፡፡ ያረጀ የከረመ፣ የቆየ የወይን ግብዣንም ያደርጋል፡፡ በወገኖች ላይ የተጣለውን መጋረጃ በአሕዛብ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛም ያስወግዳል የሚለው ነው፡፡
ጠቅላላ አስተያየት
***************
ስብከቱ የተሰበከው ክርስቶስ በእለተ ዐርብ የከፈለውን የቤዛነት ሥራ ለማሳየትና የቀኒቱን ታላቅነት ለማጉላት ይመስላል፡፡ የመረጡትም ‘የሰባ ግብዣ’ የሚለው ርእስ አብ ለሰው ልጆች ያዘጋጀው፣ ያረጀ፣ የከረመ የወይን ጠጅ (ሊቀ ጳጳሱ ባይጠቅሱትም፣ ያረጀ፣ የከረመ የወይን ጠጅ የሚለው ብሉየ መዋዕልነቱን ለማሳየት ነው ኢሳይያስ ያንን የተጠቀመው) ሲሆን፣ ታላቅ ግብዣ የተባለበትም አንዴ ተበልቶ ለዘላለም የማያስርብ አስደናቂ ግብዠ በመሆኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ ስለ ሰባኪው አስተያየት ብንሰጥ፣ ርእስ አመራረጣቸውም ይሁን፣ ለመረጡት ርእስ የሚጠቅሷቸው መጻሕፍት ጥንቅቅ ያሉ ናቸው፣ ግእዙንና አማርኛውንም በደንብ አድርገውና አቀናጅተው የሚጠቅሱ ብቻ ሳይሆኑ ንባባቱን የሚረዱበትና ለሰማዕያኑ የሚያቀርቡበት መንገድ ቀልብን የሚስብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከስብከታቸው ለመታዘብ እንደሞከርኩት ሁለት ወጥ ችግሮች አሉባቸው፡፡ 1ኛ) የመጻሕፍቱን ንባባት አስቀድመው በግእዝ፣ ከዚያ በአማርኛ ያስከትሉና ቀጥታ የሚገቡት የራሳቸውን ትርጓሜና ብይን ወደ መስጠት ነው፡፡ ይኸ ከተለመደው፣ በተጠቀሰው ንባብ ላይ ከጥንት ጀምሮ ሊቃውንቱ እንዴት እንደተረጎሙትና እንዳመሰጠሩት ካስረዱ በኋላ ወደ ሕይወታችን መተርጎም የሚለው ስልት ያላገናዘብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ 2ኛ) በሚያነሧቸው ርእሰ ጉዳዮች ሁሉ ንባባቱን ለሐሜትና ሌሎችን ለመዝለፊያነት ወይም ትውፊትን ለማጣጣያነት ይጠቀሙበታል፡፡ ይኸም በወንጌል ስም ወይም ወንጌል ለራስ ፍላጎት ማስገደድ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፣ ይኸ መንፈሳዊነት ሳይሆን ፖለቲከኝነት ነው የሚባለውም፡፡ አይደለም ወንጌል መድረክ ላይ ተቁሞ ሐሜት መቼም የትም ቦታ ቢሆንም ነውርም ሐጢአትም ነው፡፡ ይኸ ወደ ጎን የሚተኩሱት ወይም ከውጭ ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት ላይ የሚያደርጉት ተኩስ ጥሩ የነበረውን ትምህርታቸውን ፈጽሞ ገድሎባቸዋል፡፡
ዝርዝር ትችት
************
የእኔ ዝርዝር ትችት የሚያተኩረው ከጉዳዩና ከመረጡት ርእስ ጋር የማይገናኙ ወይም ባያካትትቷቸው ስብከታቸውን ሙሉዕ ከመሆን የማያግደዷቸውን፣ ነገር ግን በዐላማና የተደራጀ በሚመስል በልኩ ባስተላለፏቸው ስሕተቶች ላይ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ቢያንስ አምስት አካባቢ የሚሆኑ ነጥቦች ላይ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትችት አቅርበዋል ወይም የተሐዲሶና የፕሮቴስታንትን ድምጸት አስተጋብተዋል ብየ ስለለየሁ ስሕተቱ ከዚያ ቢልቅም ከዚህ ቀጥሎ የማተኩረው በአምስቱ ስሕተቶቻቸው ላይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለመከተል ይመቻችሁ ዘንድ የማደርገው ሊቀ ጳጳሱ የተናገሩትን በጥቅስ ውስጥ አስቀምምጥና፣ በማስቀጠል ትችቴን ወይም ጥያቄዎችን አስከትላለሁ፡፡
1) ከ13ኛው ደቂቃ ጀምሮ ስለ ኦሪት ያላቸው ትችትና ምልከታ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡
እንዲህ ይላሉ፣
‘የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፣ የኃጢአትም ኃይል ደግሞ ሕግ ናት ይላል፣ ኦሪት ይላታል፡፡ ኦሪት ገዳይ ነች፣ ጨካኝ ነች፣ ኦሪት ጥላ ናት፣ እግዚአብሔር ኦሪትን አሳልፏል፤ የኦሪቱ መሥዋዕት አልፏል፣ የኦሪት መሥዋዕት ወይም ሕገ ኦሪት ማለት የወላጅ ቤት ማለት ነው፡፡ እንደ እናት አባት ቤት የሚቆጠር፣ አንድ ሰው እናት አባቱ ቤት እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ነው የሚኖረው እንጂ እድሜ ልኩን ለእርሱ መኖሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን 40፣ 50 60 ዐመታቸው ድረስ ተዘፍዝፈው የሚኖሩ አሉ፣’
ይኸ ምልከታ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ ኦሪት ጨካኝ አይደለችም፣ ኦሪት ሞግዚት ነበረች፣ እናት ወንጌል እስከምትመጣ ልጆችን በአሳዳጊነት የጠበቀች ናት ኦሪት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‘ኦሪት ኃጢአቴን አበዛችብኝ’ ያለው፣ ሕግ የሚያስቀጡትን ነገሮች ዘርዝራ፣ ቆጥራ ስለምታሳውቅ ነው፣ ያለሕግ ሲያደርገው የነበረውን ሕግ ስተመጣ ስለከለከለችው ‘ቆጠረችብኝ፣ አበዛችብኝ’ አለ እንጂ ኦሪትን በሞግዚትነቷማ አመስግኗታል፡፡ የተሰጣትን ሚና ተወጥታለች፣ ኦሪት ያልተሰጣትን ታሳካ ዘንድ አልተጠየቅችም፣ በሌላ በኩል መጽሐፋዊው መረዳት ልጆች የወላጆች ወራሾች ናቸው፣ 'በአባቴ ቤት መኖሪያ አዘጋጅላችኋለሁ' ያለው ለዚያ ነው፡፡ የአባታችን ወራሾች ነን፡፡ የሊቀ ጳጳሱ ንጽጽርና ምሳሌም በዚህ ረገድ ደካማ ነው፡፡ በዋናነት ግን ይኸ ምልከታ የተሐዲሶና የፕሮቴስታንታት ነው፡፡
ቀጥለውም ሌላ በጣም ጎደሎ ምሳሌ ይጠቀማሉ፣
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6520