tgoop.com/tseomm/6506
Last Update:
የጌታን ጎን በጦር የወጋ፤ ዃላም ጎኑን ለወጋው ጌታ ሰማዕትነት የተቀበለ የሮማ ወታደር፤
ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ይህም 9 ሰዓት ሲሆን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በባሕርይ ሥልጣኑ ለይቷል። ዃላም ከሮማ ወታደሮች አንዱ ‹‹ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው›› ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ከጎኑ ትኩስ ደምና ውኃ ፈሷል፡፡
ለንጊኖስ ማለት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት ዘመን የዺላጦስ ወታደር የነበረ ሰው ነው። ለንጊኖስ አንድ ዓይኑ የጠፋ ሰው ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት የጌታችንን ጎን ሲወጋው የደሙ አንዷ ፍንጣቂ ሔዳ የታወረች ዐይኑ ላይ ዐርፋ ዓይኑ በራለት፡፡ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ''ለ'' ቅርጽ በመሆን በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆኖ ፈሰሰ፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ብርሃን ቀድተው በምድር ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው እግዚአብሔር ባወቀ ደሙ የነጠበበት ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር በደሙ የዋጃትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን›› በማለት የቅድስት ቤተክርስቲያንን ክብር የሚመሰክረው፡፡ ዛሬም ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው በዕለተ ዐርብ ከጌታችን ጎን ወደ ፈሰሰው ማየ ገቦነት (የጎን ውኃ) ይቀየራል፡፡
ከጌታችን ትንሳኤ በኋላ ለንጊኖስ ወደ ቅዱስ ዼጥሮስ ዘንድ ሒዶ ስለ እውነት ስለ ሃይማኖትም ተማረ። ተጠምቆ ምድራዊ ወታደርነቱን ትቶ እየሰበከ ከኢየሩሳሌም ወደ ቀዸዶቅያ ወረደ። ለዘመናትም ጌታችን ክርስቶስን በሥርዓተ ወንጌል አገለገለ።
በመጨረሻም በጢባርዮስ ቄሣር ዘመን አይሁድ አሳደዱት አንገላቱት። የነርሱ ወገን ስለነበረም መከራ አጸኑበት። የጽድቅ አርበኛና የክርስቶስ ሐዋርያ ቅዱስ ለንጊኖስ ግን ጸና። በእምነቱ የጸናው ለንጊኖስ አይሁድ አንገቱን ሰይፈውት ለሰማዕትነት በቃ። ቅዱሱ በሕይወቱም በዕረፍቱም ተአምራትን ሠርቷል::
ጌታን በመስቀል ላይ ጎኑን በጦር የወጋው ሰው መጨረሻ ክርስቶስን ወንጌል ሰባኪ ብሎም ጎኑን ለወጋው ጌታ ሰማእትነትን እስከመቀበል ደረሰ። ቤተክርስቲያን ሊንጊኖስን ቅዱስ ብላ ሰይማዋለች። ሰማዕትነት የተቀበለበትን እለት በስንክሳሯ መስግባ ትዘክረዋል።
የጌታን ጎን የወጋ የኋለኛው ሰማዕት ቅዱስ ሊንጊኖስ።
👉 ማርያማዊት ሄኖክ
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6506