tgoop.com/tseomm/6498
Last Update:
ይሁዳን አገኘሁት!
ይሁዳን ስናነሣ በተቀደሰ መንገድ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ያረፉ ቅዱሳን ሰዎች መኖራቸውንም መርሳት የለብንም።
አንዳንድ ሰዎች ሌላ ይሁዳ ያለ ስለማይመስላቸው መልዕክት የጻፈልንን ሐዋርያ ጌታን ከሸጠው ይሁዳ ጋር ሲያምታቱ ይሰማሉ።
“የተረገመ ነበር አንድ ምዕራፍ ያላት መልዕክት ጽፎ ቀረ” ብለው ፈገግ የሚያደርጉን አንዳንድ ሰባኪዎችም ሳናይ ሳንሰማ አልቀረንም።
ለማንኛውም እኔ ለዛሬ ልጽፍላችሁ ወደ ምፈልገው መልዕክት ልመለስና ይሁዳን የት እንዳገኘሁት ልንገራችሁ።
ተመሳስሎብህ እንዳይሆን ካላችሁኝ የለም ራሱ ይሁዳ ነው ብየ በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ። ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ የት አገኘኸው? የሚል ጥያቄ ከልባችሁ ሲወጣ ይታየኛል።
እኔንም ያስገረመኝ እሱ ነበር ግን እናንተም ብትገረሙ ነው የሚሻላችሁ ይሁዳ ዛሬም አለ።
ኃጢአት ከብዶት ወደ ክርስቶስ የመጣው ይሁዳ “እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ማቴ. 11፥28 የሚለውን ጥሪ ሰምቶ የመጣ ቃለ እግዚአብሔር ገብቶት በራሱ ተነሳሽነት የተመለሰ ሰው ነው።
አምላከ መምህራን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ጴጥሮስና እንደ ዮሐንስ ባለበት ቦታ ሂዶ ጠርቶ አላመጣውም፤ ራሱ ከኃጢአት ለመሸሽ የመጣ ሰው ነው።
በጽድቁ ስፍራ ኃጢአት ያገኘኛል ብሎ መች አሰበና እንዲሁ መጥቶ በጌታ ፊት ሰገደ ኃጢአቱ ተተወችለት።
ከመጣ በኋላ የተለወጠችው መንገዱ ይሁዳ ቀድሞ ያሰባትና የጠበቃት አልነበረችም። ይሁዳ ከኃጢአት ከመፈታት በቀር ሌላ ምኞት አልነበረውም። ግን እንዳሰበው መቀጠል አልቻለም። ከኃጢአት ሸሽቶ የመጣው ይሁዳን ኃጢአት በዚህም ስፍራ ጠበቀችው። ለካ ወደ መንፈሳዊ ስፍራ ገብቶ መቆም ብቻ ሳይሆን ልብን መንፈሳዊ ማድረግ ግዴታ ነው።
ካህኑ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት “ኦ እኁየ ሀሉ በዝንቱ መካን እንዘ ትሔሊ ኃጣውኢከ፤ ወንድሜ ሆይ በዚህ ቦታ ኃጢአትህን እያሰብህ ኑር” ብሎ የሚያውጀው በመንፈሳዊ ቦታ መቆማችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገር በማሰብ ጸንተን አለመኖራችን በመንፈሳዊ ቦታ ሥጋዊ ሥራ ሊያሠራን ስለሚችል ነው።
ዛሬም ዓለማዊነት ሰልችቷቸው፣ መንፈስ ቅዱስ ከዕለታት በአንዱ ቀን በልባቸው አድሮ ዕለተ ሞታቸውን አሳስቧቸው ከታሰሩበት ልማድ ሊፈቱ የሚመጡ ብዙዎች ናቸው።
መብላት መጠጣት፣ ማግባት መፍታት፣ መስረቅ መቀማት፣ ጉቦ መብላት ፍርድ ማድላት፣ መተኛት መነሣት ሆኖባቸው ሕይወት ግራ የምታጋባ ሆናባቸው ደግመው ላይመለሱ ምለው ከዓለም የተመለሱ ሰዎች ዛሬ ንስሐ ገብተው ቢያገኛቸው “ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷል” ሉቃ. 15፥24 ብሎ ክርስቶስ የተቀበላቸው ናቸው።
ጠልተዋት የመጧት ኃጢአት መልሳ በሌላ መንገድ ወረሰቻቸው። ያንጊዜ ከሰሩት ይልቅ የከፋ በደልን ወደ መሥራት ተሸጋግረዋል።
ይሁዳ ከጸሐፍት እና ከፈሪሳውያን አንዱ ስንኳ ያልደፈረውን ኃጢአት እንደሠራ እነዚህም በዓለም ሳሉ ከሠሩት ይልቅ ወደ መቅደሱ ከመጡ በኋላ የሠሩት ኃጢአት ይበልጣል።
ከጸሐፍት ከፈሪሳውያን መካከል ክርስቶስን ለመግደል እንጅ ለመሸጥ ያሰበ አልነበረም ይሁዳ ግን ሊሸጠው እየመከረ ነው ማቴ. 26፥15።
ይሁዳ ዓለማዊ ሳለ ያልታወቀች ኃጢአቱን ሊናዘዝ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀረበ፤ መንፈሳዊ ከሆነ በኋላ ግን የተገለጠች ኃጢአቱን በማስመሰል ሊሰውር ፈለገ።
በልቡ ያሰባትን ኃጢአት ገልጾ መናገሩ ተመልሶ እንዲተዋትና ወደ መዳን እንዲመጣ ነበር እሱ ግን አላደረገውም እንዲያውም ከወንድሞቹ ጋር አብሮ “እኔ እሆንን?” ማለት ጀመረ ማቴ. 26፥25 ድሮ ዓለማዊ ሳሉ ሰዎችን ሲዋሹ ይደነግጡ የነበሩት ሰዎች ዛሬ ፈጣሪአቸውን መዋሸትን እንደ ቀላል ነገር ቆጥረዋታል።
ከመቅደስ ወጥተን በገሀነም እንዳንጣል እግዚአብሔር የሰጠንን ዕድል ካለመጠቀም በላይ ይሁዳነት አለ? በዓለም ከሠራነው በላይ ኃጢአትን አብዝተን በመንፈሳዊነት ሰበብ ከመሥራት የሚበልጥ ይሁዳነትስ የት ይገኛል? መጠጥ ቤት ገብቶ ማመንዘር ምናልባትም ወደ ዝሙት የሚገፋፋ መብልና መጠጥ ስላለ ሊሆን ይችላል፤ ቤተ መቅደስ ገብቶ ማመንዘር ግን በምን ሊተረጎም ይችላል? መጠጥ ቤት ያሉ ሰዎች ፈልገውት የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ቤተ መቅደስ ያሉት ግን ሴቶችም ሆነ ወንዶች ይህንን አስበው የመጡ አይደሉም።
ታዲያ መንፈሳዊ አገልግሎትን ጥግ አድርጎ ነውር መሥራት ይሁዳነት አይደለም?
ይሁዳ በሌላም ቦታ ዘወር ዘወር ብትሉ ታገኙታላችሁ። በክርስቶስ ጉባኤ ብዙ ዕዳ ያለባት ሴት ቀርባ እግሩን ይዛ እያለቀሰች ይቅርታ ጠየቀች፤ ክርስቶስም ብዙ ኃጢአቷን ተወላት። ይሁዳ እንደ አገልጋይነቱ ብዙ ኃጢአቷ በተተወላት ሴት ደስ ሊሰኝ ሲገባው ይዛው የመጣችው ሽቶ ተሽጦ ለድሆች ባለመሰጠቱ ማንጎራጎር ጀመረ።
ወደ ቤተ መቅደስ መጥተው ንስሓ የሚገቡ ነፍሳትን ሳይሆን የሚያመጡትን ሳንቲም የሚጠባበቁ ሰዎችን ባየሁ ጊዜ ይሁዳን በዘመናችን ባለችው ቤተ መቅደስ መኖሩን አረጋግጣለሁ። “ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ የአምላኬንስ ፊት መቼ አያለሁ?” መዝ. 42፥2 እያሉ በናፍቆት የመጡ ምዕመናንን ማሰናከል እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያሳዝነው ብናስብ እኮ እንዴት ያስፈራል መሰላችሁ!
ለገንዘብ ማስቀመጫዎቻችን የምንጠነቀቀውን ያክል ለምዕመናን ነፍሳት አለመጨነቃችንን ሳስብ ከዚህ በላይ ይሁዳነት አለ? ብየ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ።
አንድ የገንዘብ ሳጥን {ሙዳየ ምጽዋት} ቢጠፋ በዕለቱ ይታወቃል አንድ ምዕመን ቢጠፋ ግን በዓመቱም ላናውቀው እንችላለን። ገንዘብ ተቀባዩን በብዙ ሰነድ አስፈርመን ብዙ ማንነቱን የሚገልጡ ሰነዶች ተቀብለን እንቀጥረዋለን፤ በምዕመናን ላይ የምንሾመውን ካህንስ ካላችሁኝ የትምህርት ችሎታው አያስጨንቀን፣ የምዕመናን አባት አብነት መሆን ይችላል ወይ ብለን አንጠይቅ፣ በእጁ ስላሉ ምዕመናን መረጃ አይጠየቅ እንዲሁ ይዟቸው ወይም ይዘውት ይኖራል።
አንዳንድ ምዕመናን እኮ ለአባቶቻቸው አባት ሆነው እየኖሩ ነው እኛ ይህ ሁሉ አያስጨንቀንም። ከቤታቸው እኩል ለንስሐ አባቶቻቸው ዕዳ የወደቀባቸው ምዕመናን ብዙ ሆነው እንመለከታለን።
በክርስቶስ ያሳመንናቸው የፈረሰ ቤታችንን እንዲሠሩልን ነው? የተጣመመ ኑሯችንን እንዲያቃኑልን ነው? ለዚያውም አንዳች ቃለ እግዚአብሔር ያልነገርናቸው በክርስቶስና በገብርኤል መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን ያላስተማርናቸው የዋሆችን ክርስቶስን በማወቅ ነው እንጅ የኛን ቤት በመሥራት ገነት ይገቡ ይመስል ገንዘባቸውን እንጅ ልባቸውን ያልሰበሰብናቸው ብዙ ናቸው።
አንዳንድ ምዕመናንም የሰበካ ጉባኤ አባል ሆነው ሲመረጡ ልማት የሚመስላቸው ሕንጻ መሥራት ግቢ ማጽዳት ነው እንጅ ምን ያክል ምዕመን ሠርክ ጉባኤ ይከታተላል፣ ስንት ሰው ልጆቹን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ያስተምራል፣ ከተመዘገበው ምዕመን ስንቱ ይቆርባል ብለው አያስቡም።
ዕቅዱን ሁሉ በየቤተ ክርስቲያኑ እየዞራችሁ ብትመረምሩ ስንት ገቢ እናስገባለን፣ ስንት ወጪ እናወጣለን አይነት ነው እንጅ ድኅነተ ምዕመናንን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ብዙም አታገኙም። ፈርታችሁ ካልሆነ እናንተም ይሁዳን አግኝታችሁት ታውቃላችሁ።
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6498