tgoop.com/tseomm/6480
Last Update:
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዙሪያ የተሠራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ገዳማውያኑ ተናገሩ !
ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም [ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ]
''የዋልድባ አብረንታትን ገዳም በሰላም መደፍረስ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደ ደረሰበት የገዳሙ አባቶች ገለጹ!'' በሚል መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም መረጃ መተላለፉ ይታወሳል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 03 2017 ዓ.ም ከገዳሙ ተወክለው የመጡ መነኮሳት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገዳሙ በማያውቃቸው አባቶች አማካይነት የተሠራጨው ዘገባ ከገዳሙ ዕውቅና ውጪ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱ ማኅበረ መነኮሳቱን እንዳሳዘነ ተናግረዋል።
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክም ቅሬታ ማቅረባቸውን የገለጹት የገዳሙ ተወካዮች የሆኑት አባ ገ/ሥላሴ፣ መ/ር ዓምደ ሥላሴ እና አባ ገ/ማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ለተሠራጨው መረጃም ዕውቅና እንደሌላቸው ነግረውናል ብለዋል።
በተለይም በአሁኑ ሰዓት አንድነት ገዳሙ በእግዚአብሔር እርዳታ በጾምና በጸሎት በሚተጉ ማኅበረ መነኮሳት ተጠብቆ እንደሚገኝ እና ሰላም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ በፊት የተሠራውን የሐሰት ዘገባ ተከትሎ ገዳሙ የማያውቃቸው ሕገ ወጥ አካላት ነገ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የገቢ ማሰባሰቢያ ሊያካሂዱ በመሆኑ ሕገ ወጥ ተግባሩ እንዲቆም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመሆኑም በዚህ በጾም ሰዓት ሱባኤ አቋርጠው ወደዚህ ለመምጣት እንዳስገደዳቸው የተናገሩት ገዳማውያኑ ምእመናንም የገቢ ማሰባሰቢያ በሚል የተጠሩበት ቦታ ላይ እንዳይገኙ ገልጸዋል።
የተከሠተው ጉዳይ በገዳሙ ላይ የመጣ ፈተና ስለሆነ በተቻለ ዓቅም ሕገ ወጥ ተግባሩ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
©ማኅበረ ቅዱሳን
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu

Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6480