tgoop.com/tseomm/6436
Last Update:
ሂሳባዊ አእምሮ የኦርቶዶክስ አይደለም!
ብዙ ጊዜ አንድን ጉዳይ አንስተው "ይህን ባላደርግ ሲኦል እገባለሁ ማለት ነው?" ብለው የሚጠይቁ ክርስቲያኖች አሉ። ለምሳሌ " ቤ/ክ ሀዘን ላይ በነበረችበት ግዜ ጥቁር ባለመልበሴ ብቻ ስእል እገባለሀ? ሌላውን አድርጌ ግን ባልፆም እኮነናለሁ? ሌላውን የክርስትና ትዕዛዛትን ተቀብዬ ግን አንዱን ገድል ባልቀበል፣ ወይም ለአንዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ ባልገዛ ሲኦል እገባለሁ?" ወዘተ ቀጥተኛ የፍርድ ጉዳይ አድርገው ይጠይቃሉ።
በርግጥ የጥያቄዎቹ መሠረት የተደበቀ ያልተነገረ ፍላጎት ለመሆኑ ይታወቃል። ለምሳሌ ሰው የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ የማያከብረው ከሃይማኖቱ የፖለቲካ አመለካከቱን ወይም ፍልስፍናውን ሲያስቀድም፣ ወይም በሌላ ትምህርት ተፅዕኖ ምክንያት ነው። በቀጥታ ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ አለማክበር ኃጥአት ነው። ጥያቄው ደግሞ "ይህ ኃጥአት ብቻ ሲኦል ያስገባኛል?" ብሎ እንደመጠየቅ ነው የሚሆነው።
ይህ ደግሞ ክርስትናን በቀመር፣ በሂሳብ፣ በስሌት መኖር ይሆናል። ይህ ሂሳባዊ አእምሮ ደግሞ የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት መሠረታዊ ፍኖት (ካርታ) የሌለን ሲሆን የምንገባበት ጉድጓድ ነው። ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ፣ ኦርቶዶክሳዊ ሕሊና፣ ክርስቲያናዊ ልብና ሥነ-ልቦና ሳይኖረን ሲቀር የምንገኝበት የአስተሳሰብ ባህሩ ይህን ይመስላል።
በርግጥ በቅዱስ መጽሐፋችን ይህን ሂሳባዊ አእምሮ (Calculative Mind) ይዘው ኖረው የጠፉበት ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የኖህ ዘመን ሰዎችን እንውሰድ! ለየትኛው የኖህ ትምህርት ምላሻቸው ኃጥአት የሚሰሩበትንና ለንስሃ የሚቀራቸውን ጊዜ ማስላት ነበር። የሚሠሩት ኃጥአት መሆኑን አልዘነጉም። ወደ ጥፋት ወሃም የወሰዳቸው ሂሳባዊ አእምሮአቸው ያመጣባቸው ጣጣ ነው። ለኃጥአትና ፅድቅ ጉዳይ የራስን ቀመር መሥራት፣ መቁጠርና ብልጣ ብልጥ ለመሆን መሞከር።
የይሁዳም ሕይወት ይህንኑ ያስተምረናል። ጌታችን እንደሆነ ለመሞት ነበር የመጣ። ይሁዳ ግን ጌታችንን ሲሸጥ ከሚያገኘው ትርፍ አንስቶ እራሱ ቢታነቅ ከሲኦል ነፍሳት ጋር ወደ ገነት የሚገባበትን ፍጥነት እስከማስላት የደረሰ ነበር። ውጤቱ ደግሞ የምናውቀው ነው።
ቤተክርስቲያን ላይ ብልጥ ለመሆን በጣር ቁጥር ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላካችን ላይ ብልጥ ለመሆን እየሞከርን መሆኑን አንዘንጋ። ሁሉም የጮሌነት ታሪኮች በውርደት ተደምድመዋል። በማንኛውም አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያን ላይ ሂሳብ የሚሰሩ ሰዎችም መጨረሻ ይኸው ነው። ባይሆን የወደቅንበትን የኃጥአት ማጥ አምነን፣ ችግሩ የራሳችን መሆኑን ተቀብለን "እርሱ በፈቀደ ጊዜ ይመልሰን " ማለቱስ ይቀላል። ለዚህም ነው ቅን ልቦና የክርስትና ውበት፣ እግዚአብሔርን የምናይባት መስታወት የሆነችው።
ቤተክርስቲያን ላይ በፍፁም ብልጥ ለመሆን አንሞክር!
አክሊሉ ደበላ እንደጻፈው
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6436