tgoop.com/tseomm/6394
Last Update:
መጻጉእና አልጋው
በመጋቤ ሐዲስ ሄኖክ ፈንቴ
በኢየሩሳሌም በበጎች ብር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች
ስሟም ጵሩጳጥቄ ዘቅልንብትራ ትባል ነበር
ጵሩጳጥቄ ማለት
1 ዘፈውስ (በሽተኛ የሚፈወስባት )
2 ዘበዓል (በዓል የሚያከብሩባት )
3 ዘመሥዋእት (መስዋእት የሚሰውባት )
4 ዘጉባኤ (የሚሰበሰቡባት )
5 ዘዓባግእ (በጎች የሚሰማሩባት) ማለት ነው
ቅልንብትራ ማለት በእብራይስጥ ቤተ ሳህዳ ማለት ሲሆን በግዕዝ ቤተ ሳህል (የምህረት የይቅርታ ቤት )ማለት ነው
አምስት እርከኖች አሏት
በዚያም በአምስት ዓይነት በሽታ የታመሙ ብዙ ሰዎች ተይተው የውሃውን መናወጥ ይጠባብቁ ነበር የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውሃውን በሚያናውጠው ጊዜ መጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር።
መጠመቂያ የተባለችው ተጠምቀን ልጅነትን የምናገኝባት ቤተ ክርስቲያን ናት
በጎች የተባሉ ምእመናን ናቸው
አምስት እርከን የተባሉ አምስቱ አእማደ ምስጢራት ናቸው
ውሃው የምንጠመቅበት ውሃ ነው
መልአኩ የሚያጠምቀው ካህን ነው
አምስቱ ሕሙማን
1 ዕውራን ዓይናቸው የታወረ
2ሐንካሳን የሚያነክሱ
3 ይቡሳን የሰለሉ
4 ጽውሳን ልምሾ የሆኑ
5 ጽቡሳን እግራቸው ያበጠ ናቸው
አምስቱ ሕሙማን የአምስቱ ጾታ ምዕመናን ምሳሌዎች ናቸው
አምስቱ ጾታ ምእመናን
1 አዕሩግ ሽማግሌዎች
2 ወራዙት ወጣቶች
3 አንስት ሴቶች
4 መነኮሳት መነኮሱ
5 ካህናት አገልጋዮች ናቸው
1 ዕውራን የተባሉ አእሩግ ናቸው ዕውርነተቸው በፍቅረ ንዋይ ነው የሽማግሌዎች ጾር ፍቅረ ንዋይ ነው ማን ይጦረና?ል ማን ይረዳናል? በማለት የገንዘብ ፍቅር ያሳዎራቸው አእሩግዕ ውራን ተብለዋል
1 ሐንካሳን የተባሉ ወራዙት ናቸው ሐንካስነታቸው በዝሙት ነው ወራዙት ጾራቸው ዝሙት ነው ሁለት ልብ ሁነው አንድ ጊዜ ወደ ጽድቅ አንድ ጊዜ ወደዝሙት ስለሚሄዱ ሐንካሳዎች ተብለዋል
3 ይቡሳን የሰለሉ የተባሉት አንስት ናችው የአንስት ፈተናቸው ትውዝፍት ነው (የጌጣጌጥ ፍቅር )ለጌጣጌት ሲሉ ህገ እግዚአብሔርን ስለሚረሱ መሰናክል ስለሚሆኑ የሰለሉ ተብለዋል
4 ጽውሳን ልምሾ የሆነ የተባሉ መነኮሳት ናቸው የመነኮሳት ፈተናቸው ስስት ነው መነኮሳትን ከገዳማዊነታቸው ህይወታቸው ስስት ልምሾ ስለሚያደርጋቸው ጽሁሳን ተብለዋል
5 ጽቡሳን ያበጡ የተባሉ ካህናት ናቸው የካህናት ፈተናቸው ጾራቸው ትእቢት ነው አእምሯችን ምጡቅ መዓርጋችን ረቂቅ ክህነታችን ሰማያዊ ስራችን ላእላዊ እያሉ ይታበያሉ ስለሚያብጡ ጽቡሳን ተብለዋል።
አምስቱ በሽተኞች ሲጠመቁ እንደሚፈወሱ ሁሉ አምስቱ ጾታ ምእመናንም በጥምቀት ባገኙት የልጂነት ኃይል ጾራቸው ፈተናቸውን ድል ነስተው አሸንፈው ይኖራሉ
በዚያም በመጠመቂያው ሰላሳ ስምት ዓመት ሙሉ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረ አንድ ሰው ነበር
ጌታችንም አምላካችን ሲያልፍ አየውና ልትድን ተወዳለህ ?ብሎ ጠየቀው
ጌታዪ ሰው የለኝም ውሃው በተናወጠ ጊዜ
ቀድሞ የሚያወርደኝ
ሰው ያለው ቀድሞኝ ይወርዳል ይፈወሳል እንጂ መዳን እፈልጋለው አለው ጌታችንም ተነስ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው የፈቃድ አምላክ መሆኑን ለመግለጽ ጠይቆ ፈቃደኛ ሲሆን ፈውሶታል።
ወዲያውኑ ተፈውሶ አልጋውን ተሰክሞ ሔደ
4 ዓይነት በሽታዎች አሉ
1 ደዌ ዘእሴት 2 ደዌ ዘንጽሕ 3 ደዌ ዘመቅሰፍት
4ደዌ ዘኀጢአት
1 ደዌ ዘእሴት ዋጋ የሚያሰጥ መጨረሻው የሚያስደስት በሽታ አለ የኢዮብ ደዌ ዘእሴት ይባላል
2 ደዌ ዘንጽሕ በንጽህና ምክንያት የሚመጣ በሽታ አለ የጢሞቴዎስ ደዌ ዘንጽሕ ይባላል
3 መቅሰፍት የሚያመጣ በሽታ አለ የሳኡል እና የሄሮድስ ደዌ የመቅሰፍት ደዌ ነው
4 ደዌ ዘኀጢአት በኀጢአት ምክንያት የሚመጣ አለ የመጻጉእ በሽታ የኀጢአት ደዌ ነው
ጌታችን መጻጉእን በቃሉ ብቻ ፈውሶታል
በቀሉ የፈወሳቸው አሉ
በሀልዮ የፈወሳቸው አሉ
በመዳሰስ የፈወሳቸው አሉ
በሀልዮ በነቢብ በገቢር ሁሉን መስራት የሚችል አምላክ መሆኑን ለማስረዳት
መጻጉእ ከግማሽ እድሜው በላይ በበሽታ ያሳለፈ ሰው ነው ዛሬም በየሆስፒታሉ የሚጠይቃቸው አጥተው የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ
እንደ መጻጉእ ሰው አጥተው ሰው የተራቡ መጻጉእ ከጎኑ የነበሩት ሰዎች ተፈውሰው ሲሄዱ እያየ እሱ ግን መፈወስ አልቻለም ነበር
ምክንያቱም የሚረደው የለምና ደግሞም የሚድነው አንድ ሰው ብቻ ቀድሞ የገበው ነበርና
ረዳት ያለው ሰው ቀድሞት ይገባል
ያም በየቀኑ አልነበረም በሳምት አንድ ቀን ቅዳሜ ብቻ ነበር
መልአኩ ከሰማይ ወርዶ ውሃውን የሚያውጠው በዚሁ ዕለት ስለሆነ
ሳምንት ጠብቀው ቀድሞ የገበው ይፈወስ ነበር
ያውም የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር
ለምን ሁሉ በአንድ ቀን አልዳኑም ቢባል
በብሉይ ኪዳን ፍጹም ድህነት እንደሌለ ለመግለጽ ነው
ለመሆኑ በ38 ዓመት ውስጥ መጻጉእ ስንት ሰው ሲፈወስ ዓይቶ ይሆን ?
በሳምንት አንድ ሰው ሳያቋርጥ ይፈወሳል
በዓመት 52 ሰዎች ይፈወሳሉ
በ38 ዓመት ዓመት 1976 ሰዎች ሲፈወሱ ተመልክቷል እነዚህ ሕሙማን ቀድመው በመግባት የተፈወሱ ናቸው ሰው ረድቷቸው እንደምንም ጥረው ቀድመው ውሃው ውስጥ ገብተው የተፈወሱ ናቸው
መጻጉእ ግን የሰዎችን መዳን እያየ እሱ መዳን ያልቻለ ወደ መዳኒቱ የሚያደርሰው አጥቶ ከዛሬ ነገ እድናለው በማለት በሕመም ሲሰቃይ የኖረ ሰው ነበር ነገር ግን በመጨረሻ ሰው ባይኖረው ሰውን የፈጠረ አምላክ በቃሉ ብቻ ፈውሶት
38 ዓመት ሙሉ የተሸከመችውን አልጋ እሱ ተሸከማት ወደቤቱ ይዷል ::
መጋቤ ሐዲስ ሄኖክ ፈንቴ
የካቲት 24\2010
ዱባይ አላይን
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6394