tgoop.com/tseomm/6342
Last Update:
የአዝማች ኮሚቴ ተቋቋመ፣ ዘማች አብያተ ክርስቲያናትም ተለይተው ታወቁ፡፡ በዘመቻውም ታቦት፣መስቀል፣ ንዋያተ ቅድሳት ቃጭል፣ጥላዎች እና ድባቦች ይዘው ከሊቃውንቱና ካህናቱ ጋር እንዲዘምቱ ተወሰነ፡፡
ከአዲስ አበባ እስከ ዐድዋ በነበረው የዘመቻ ጉዞ ቤተክርስቲያኗ ግምባር ቀደም ሆና ሕዝቡን ከጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ጋር በአንድነት በመምራት የዘማቹን ወኔ በመገንባት፣ ስለ አገር ፍቅር በመሰበክ፣ በጾምና በጸሎት ወደፊት ትገሰግስ ነበር፡፡ በጉዞው ወቅት በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስና በዕጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ አስተባባሪት መንፈሳዊ አገልግሎቱ በመዓልትና በሌሊት በሰዓታት፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ በነግህና በሠርክ ጸሎት ሳይቋረጥ ይከናወን ነበር፡፡ የጦር መሪዎቹ ሳይቀር በጸሎታቸው የተጉ የመንፈሳዊ ልዕልና ያላቸው ነበሩ፡፡ በየካቲት 14 ቀን 1888 ዓ.ም ዐፄ ምኒልክ ዐድዋ ሲደርሱ ከመላው ትግራይ የተውጣጡ ካህናትና ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በደማቅ ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል፡፡ ከዚያም ለአንድ ሱባኤ ምህላ ታዟል፡፡ ዐፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ሱባኤ ይዘው የቆዩት በእንዳ አባ ገሪማ ገዳም ነበር፡፡ ለጦርነቱ ዝግጅትና መሰናዶ ሲጀመርም አስቀድሞ የታወጀው የጸሎትና የምህላ ዐዋጅ ነበር፡፡ ወደ ጦር ግንባር ሲዘምቱ ታቦታት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ተይዘው ነበር፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የአብነት ተማሪዎች ሳይቀር በጦርነቱ ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም ለመላው ዘማች ለሰባት ቀናት የቁም ፍታት ተካሂዷል፡፡
በጦርነቱ ዋዜማ ዐፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ዐድዋ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ያስቀድሱ ነበር፣ ቅዳሴውም የተመራው በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ነበር፡፡ አቡነ ማቴዎስ “ልጆቼ ሆይ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነውና ሂዱ ለሃይማኖታችሁ ለአገራችሁ ሙቱ እግዚአብሔር ይፍታህ” ሲሉ መኳንንቱ ሁሉ እየተሽቀዳደሙ የአቡኑን መስቀል ተሳልመው ወደ ጦርነት መሄዳቸው፣ ሊቀ ጳጳሱም ወደ ጦርነት የሚገባውን ወታደር ሁሉ እግዚአብሔር ይፍታህ እያሉ ይናዝዙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዐፄ ምኒልክም በበኩላቸው ነጋሪት እያስጐሰሙ ሠራዊቱን “የጦርነት ድምፅ ብትሰሙም አትደንግጡ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ሆኖ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋ አትፍሩ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፊታችሁ እየኼደ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋላችሁ፣ እናንተንም ስለሚያድናችሁ ከፊታቸው አትሽሹ” በማለት ያበረታቱ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም አንጸባራቂው የዐድዋ ድል በየካቲት 23 ቀን በዕለተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተበሰረ፡፡
እንደ ማጠቃለያ
የዐድዋ ድል ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በነጻነት የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ፣ ዳር ደንበሯ ተከብሮ ለዚህ ትውልድ እንድትደርስ በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያደረገችው የላቀ፣ ዘመን ተሻጋሪና ዘርፈ በዙ አስተዋጽኦ አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባቶችና እናቶች ታሪክና ቅርስን ብቻ ሳይሆን በከፈሉት መሥዋዕትነት ሀገርንም አቆይተውልናል፡፡ ይህ ትውልድ እንደ አባቶቹ ታሪክ መሥራት ባይችልም እንኳ ታሪኩንና ቅርሱን ማወቅና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የቤተክርስቲያንንም አስተዋጽኦና ውለታ መርሳት የለበትም፡፡ የዐድዋ ድል የኢትዮጵያዊ አንድነታችን ውጤት ነው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት፣ በረከት፣ አማላጅነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣልያ፡፡
✍️ አድዋና ምኒልክ
✍️ ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፡፡
✍️ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፡፡
✍️ ታሪክ ነገሥት ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፡፡
✍️ Memories of the Victory of Adwa
✍️ The Life and Times of Menelik II of Ethiopia 1844-1913.
✍️ The Battle of Adowa
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6342