tgoop.com/tseomm/6304
Last Update:
ከዚህም ብዙ ቁምነሮችን የምናገኝ ይመስለኛል። ይኸኛው እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ሳይጠነቀቅ እዚያው ፊት ለፊት ካህኑን ገጥሞታል። መልአኩ ደግሞ ምን ያህል ጊዜ እንደታገሰው እና እንደጠበቀ እናስተውል። መልአኩ እንዳለው ሰዎች ከስሐተታቸው በሌሎች ሰዎች ሲታረሙ ማየት እግዚአብሔርንም መላእክትንም የሚያስደስት መሆኑ አስገራሚ ነው። ያም በመሆኑ ደግሞ እግዚአብሔር ለመጀመሪያው አባት ቅዱስ ቄርሎስን ለዚህ ካህን ደግሞ አዋቂ ዲያቆን አዘጋጀ። ስሕተት ደግሞ የማትገባበት ጊዜ እና ቦታም እንደሌለ የምትምረውም የሰው ዓይነት እንደሌለ ከታሪኮቹ መረዳት ይቻላል። ከዚህ ታሪክ ሌሎች ብዙ ነጥቦችንም መውሰድ እንችላለን። እንደላይኛው ሁሉ መልአክ ተገልጾለት የሚነጋገር አባት ሳይቀር ሊስት የኑፋ/ቄ ቃላትንም ሊጠቀም መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገረ ግን ሰውየው ውስጡ እምነቱና ሀሳቡ ኑፋቄና ተንኮል ከሌለው እግዚአብሔርም ይታገሰዋል። ቀኑንም ጠብቆ የሚያርመውንና የሚያስተምረውን ሰው ይልክለታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው በሌላ ሰው ስንስተካከል ነው። ለዚህ አባት የተላከለትም ከእርሱ በላይ የበቃ አባት ሳይሆን ከእርሱ በሥልጣነ ክህነትም የሚያንስ ዲያቆን ነው። ዲያቆኑን ተጠራጥሮ አልቀበለም ሲል ደግሞ መልአኩ ተገልጾ ማረጋገጫ የሰጠው ከእኛ ያንሳሉ ብለን ከምናስባቸው ሰዎችም ቢሆን ሰምተን እንድንታረምና እንድንሰተካከል ጭምር ነው።
በሰው መታረምን በተመለከተ ደግሞ ሌላ ታሪክ ልጨምር። ቃለ እግዚአብሔርን ከምጠያየቃቸው እና ከምጫወታቸው አንዱ የሆነው መምህር በረከት አዝመራው ካነበበው የትርጓሜ መጽሐፍ የነገረኝ ነው። ሙሴ ደብረ ሲና ወጥቶ ሲመለስ እሥራኤል ጣዖት አቁመው ሲሰግዱ አግኝቷቸው እነዚያን ጣዖት የሚያመልኩትን እንዲገደሉ አዝዞ በወገኖቻቸው ተገድለዋል። እርሱ እንደነገረኝ መተርጉማኑ አንድ ጥያቄ አንሥተው ይመልሳሉ። እግዚአብሔር እነዚያን ጣዖት አምላኪዎች እንደ ፈርዖን ለምን ራሱ አላጥፋቸውም ወይም ለምን ራሱ አልቀሰፋቸውም? በሙሴ ትዕዛዝ በራሳቸው ወገኖች እንዲገደሉ ለምን አደረገ የሚል ጥያቄ ያነሡና ይመልሳሉ።
እግዚአብሔር ራሱ ሳያጠፋቸው በራሳቸው ወገኖች እንዲገደሉ ያደረገው ስለሁለት ምክንያት ነው። የመጀመሪያው እሥራኤል ታሪካቸው እግዚአብሔርን ክዶ ጣዖት ማምለክ ብቻ ሳይሆን ጣዖት አምላኪዎችንም የማጥፍት ታሪክ እንዳላቸው እንድናውቅ ነው። ሁለተኛም ከላይ እንዳልነው የሰው ስሐተት በሰው ሲታረም እግዚአብሔር ደስ ስለሚለው ነው የሚል ነው። ከላይ ባየነው ታሪክ መልአኩም ያለው ይህንኑ ነው።
ከዚህም ጋር በሁለቱም አባቶች ታሪክ ላይ አንድ ሌላ መሠራታዊ ትምህርት እናገኛለን። ይኸውም ሰዎች በሚሳሳቱ ጊዜ በሁለንተናቸው ኦርቶዶክሳዊ ሆነው የሆነ ኑፋቄያዊ ቃላት እና ሀሳብ ባገኘንባቸው ጊዜ መማማሩ እንዳለ ሆኖ ልናደርገው የሚገባን ጥንቃቄ ፣ ከበሬታ ፣ ልናሳያቸው የሚገባው ፍቅር ተገልጾልናል። ያን አባት ያረመው ያ ዲያቆን በእኛ ዘመን ቢሆን ኖሮ እንኳን በዚያ አባት በመልአኩም ሊናደድ የሚችል ይመስለኛል። ለምን ሳይቀስፈው ብሎም መልአኩንም የሀሳቡ ተባባሪ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። (ይህን የምለው ስለእኛ ሕሊና መሆኑ ሳይረሳ) ምክንያቱም የእኛ ዘመን አንዱ ትልቁ ድክመታችን የመጨረሻ ፍርድ ሁሉ ሰጭዎች መሆናችን ነውና።
ማጠቃለያ
እንዲህ ያሉ ነገሮች ለምን ተነሡ? ምን ሲል እንዲህ ተባለ? ለምን እነእገሌ እንዲህ ይላሉ? ... ለምን ዝም ይባላል? የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማቆም ይኖርብናል። በየትኛውም ዘመን በየትኛውም መዓርግ ባለ መንፈሳዊ ሰውም ላይ ብዙ የምናውቃቸውም የማናውቃቸውም ስሐተቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ መረዳት ተገቢ ነው። እባብ ያዬ በልጥ በረዬ የሚባልላቸው መሆንም የለብንም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት ታሪኮች ሁልጊዜም ማስተማሪዎች በመሆን አንዱ የእግዚአብሔር የመግቦት መገለጫዎች፣ የየዘመኑን ሰው ማንቂያዎች፣ ወዳጆቹንም መጠበቂያዎች (በተለይ ከትዕቢትና ኩነኔ ከሚያመጣ ጥፋት) ናቸው። ዋናው የሚያስፈልገን ነገር ከሁሉም ነገር እግዚአብሔር ሊያስተምረን የፈለገው፣ እኛ ውስጥ ሊያርመው የፈለገው ነገር ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ መሆን አለበት ። ካስተዋልን ሁላችንም የየራሳችንን ስሐተቶች የማየት እና የመታረም ዕድል እናገኝበታለን።
ማር ይስሐቅ መላእክትን ለማየት ከበቃ ሰው ይልቅ የራሱን ስሕተት ለማየት የበቃ ሰው የበለጠ ብቃት ደረጃ ላይ ደርሷል ይላል። ቅዱሱ አባት መላእክትን የሚያይ የውጭ ዐይኑ የተከፈተለት ነው፣ የራሱን ስሕተት የሚያይ ግን የውስጥ ዓይኑ የተከፈተለት ነውና እርሱ የበለጠ በቅቷል እንዳለ ወደ ሰው ስሕተት ከማየት ይልቅ ወደራሳችን ስሐተት ማየት ኦርቶዶክሳዊም መንፈሳዊም መንገድ መሆኑን እናስተውል። በዚህ ጽሑፍ ላነሣቸው ያልፈልኳቸው ብዙ ድክመቶች እንዳሉብን ይሰማኛል። ለሁላችንም የሚጠቅመን ግን የራሳችን ስሐተት ማየት እንጂ የሌሎቹ ላይ ማፍጠጥ እና ከፍ ዝቅ አድርጎ መናገርም ሆነ መጻፍ አይደለምና አጥብቀን እንታረም። ይልቁንም ያለነው በዐቢይ ጾም ዋዜማ ላይ ስለሆነ በቀሩን ቀናት ይቅርታ ተጠያይቀን ከቡድነኝነት፣ ከተሳሳቱ ግምቶች እና ግምታዊ ንግግሮች፣ ከፍረጃ እና ከአጸፋዊ ፍረጃ፣ በማናውቀው እና በማይገባን ነገር ከመነጋገር ወጥተን ወደ መንፈሳዊ ድንኳናችን እንሰብሰብ። ያን ጊዜ ስሕተቶቻቸን ይታዩናል። ለሰዎችም ፍቅር ሐዘኔታ የተመላ የማስተካከያ መንገድ ይገለጽልናል። እግዚአብሔር ቢፈቅድ ስለኦርቶዶክሳዊ ነገር ዕውቀት ትንሽዬ ማስታወሻ ለጾም ቅበላችን እጨምራለሁ፤ መልካም ጾም ያድርግልን። ልዑል እግዚአብሔር ከሚታወቅም ከማይታወቅም ስሐተት ሁላችንንም በቸርነቱ ይጠብቀን፤ አሜን።
✍️ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ እንደጻፈው
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6304