tgoop.com/tseomm/6303
Last Update:
በአፌ ገብቶ አያውቅም እያለ ይከራከራል። በመጨረሻም ስለ ራእዩ ሲጨነቅ ከቆርነሌዎስ የተላኩት ሰዎች መጠተው ተጣሩ። እንደ ገና መንፈስ ቅዱስ እኔ የላኳቸው ሰዎች ስለሆኑ አብረህ ሒድ ሲል አዘዘው። ወደ ቂሳርያም ተጓዘ። በዚይም ሲደርስ የተጠራበትን ጠይቆ ከተረዳ በኋላ እንዲህ አለ፦ “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ” /ሐዋ 10 ፤28/ ትንሽ ቆይቶም ደግሞ ፤ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” /ሐዋ 10 ፡ 35/ አለ። ይህ ሁሉ የተደረገው ቅዱስ ጴጥሮስን በውስጡ ተደብቃ ከምትኖር አድሎ ለማለቀቅ እና አሕዛብንም ለማዳን ነበር።
ሆኖም ይኼው ቅዱስ ጴጥሮስ እሥራኤልን ለቅቀው ወደ ሶርያ ከገቡ በኋላ አይሁድ በሚኖሩበት ጊዜ እነርሱን በመፍራት አሕዛብ ጋር ተቀምጦ ለመብላት እንኳ አይደፍርም ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፤ ሊፈረደበት ይገባ ነበርና / ገላ 2፡11/ ሲል ታሪኩን ይነግረናልና ።ይህ ያደረገው ደግሞ ከላይ የተመዘገበው ታሪክ ከተፈጸመ እና ማንንም ሰው እንዳልጸየፍ እግዚአብሔር አሳየኝ ብሎ ከመስከረ በኋላ መሆኑን ስናስብ ሰውነት ምን ያህል ድካምነት እንዳለበት አስበን እንገረማለን። ከዚህ የምንረዳው በውስጣችን ያለች አድሎ ምን ያህል ከባድ መሆኗን ለቅድስና የበቁትን የተመረጡትን ሳይቀር ምን ያህል እንደምትፈትንም ጭምር ነው። በእነርሱ ዘንድ እንኳ እንዲህ ያለ ነገር ጨርሶ ካልጠፋ በእኛ ዘንድማ ምን ያህል ይሰለጥን ይሆን? የብዙዎቻችን አስተያየቶች ከዚህች አድሎ ነጻ የምትሆን አይመስለኝም። ይህን መተረክ ያስፈለገውም ወደ ሌሎቹ አጥብቀን በምርመራ መንፈስ ከምናይ ወደ ራሳችን ብናይ የበለጠ እንጠቀማለን ለማለት ነው። ለማንኛውም መንፈሳቸው፣ አጠቃላይ ሰብእናቸው ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ በተለያየ ምክንያት የማያስተውሏቸው ኑፋቂዎች እና ስሕተቶች ሲያጋጥሙ አበው ለማረም ከሔዱባቸው ታሪኮች ሁለቱን ላቅርብና ነገሬን ልቋጭ።
ስሕተት፣ ኑፋ/ቄ ፣ እርማት፣ እና አራሚዎች
በመጻሕፍት ካነበብኳቸውና አባ ዳንኤል ዘገዳመ አስቄጥስ ከመዘገባቸው ታሪኮች ውስጥ አንዱ የሚከተለው ነው። ቅዱስ ቄርሎስ በእስክንድርያ መንበር ፓትርያርክ በነበረበት ዘመን በብቃቱ የሚታወቅ አንድ ቅዱስ ገዳማዊ አባት ነበር። የዚህ አባት ዋናው ብቃቱ ደግሞ ሰዎች በሆነ ነገር ሲቸገሩ እና ለእርሱ ሲነግሩት ሱባኤ ይገባላቸውና ከእግዚአብሔር የተገለጸለትን ይዞ ምክር በመስጠት የብዙ መናኞችን እና አማኞችን ችግር ይፈታ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ባለማወቅ እና የራሱንም መረዳት በመደገፍ አንድ አዲስ ትምህርት ለገዳሙ መነኮሳት መናገር ጀመረ።
ይኸውም መልከጼዴቅ ወልደ እግዚአብሔር ነው የሚል ነው። ከእመቤታችን ተወልዶ ኢየሱስ ተብሎ የመጣው ቀድሞ ለአብርሃም የተገለጸለት የሳሌሙ ንጉሥ መልከጼዴቅ ነው እያለ ወደ መነኮሳቱ እየዞረ መናገር አበዛ። ይህን ኑፋቄ መናገር የጀመረው ያ በቅድስና ሕይወቱ እና በብቃቱ የታወቀው አባት ነው። ክፉን ያርቅና በእኛ ዘመን እንዲህ የሚል ትምህርት አንድ አባት ይዞ ቢመጣ ምን እንደረጋለን? ምንስ እንለዋለን? ድርጊቱንስ እንዴት እንመለከተዋለን? እስኪ ራሳችንን እንመልከትበት ።
የገዳማቱ አባቶች በትምህርቱ ታወኩ። የሚያደርጉትም ቸገራቸው። ሁኔታው ለፓትርያርኩ ለቅዱስ ቄርሎስ ደረሰ። እርሱም ሲሰማ አዘነ፣ ተጨነቀም። በኋላ ግን አንድ ነገር አስታወሰ። ይህ አባት እንዲህ ያለ ሁከተ ኅሊናም ሆነ ሌላ መንፈሳዊ ችግር ለገጠማቸው ሁሉ በጥብቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ እና በተገለጠው ብቻ እንዲመሩ ሱባኤ ገብቶ የተገለጠለትን በመናገር እና በመምከር የታወቀ ነበር። ለርሱ ፈተና ጊሼ የሚሆን ሰው ግን በወቅቱ አልነበረም። ስለዚህ ቅዱስ ቄርሎስ ይህን አባት አስጠራው። ይህ አባት ሲመጣም ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ አለው። አባቴ ሆይ እኔ በሁለት ሀሳቦች ተጨነቅሁኝ። አንዱ አእምሮዬ መልከጼዴቅ ወልደ እግዚአብሔር ነው ይለኛል። ሌላው አእምሮዬ ደግሞ አይ መልከጼዴቅ ሰው ነው እንጂ ወልደ እግዚአብሔር አይደለም ይለኛል። እባክህን ሱባኤ ገብተህ የትኛው ትክክል እንደሆነ ከእግዚአብሔር የተገለጸልህን ንገረኝ አለው። ያ አባትም ችግሩ የራሱ መሆኑን ረስቶ ለአባ ቄርሎስ ሦስት ቀን ስጠኝ አለው። ከሦስት ቀን በኋላ በገዳሙ እየዞረ መልከጼዴቅ ሰው ነው። ከአባቶች አንዱ እንጂ ወልደ እግዚአብሔር አይደለም እያለ መናገር ጀመረ። መነኮሳቱም በምን አወቅህ ሲሉት ጌታ ከአዳም እስከ አብርሃም ያሉትን አባቶች አምጥቶ ሲያሳየኝ አንዱ መልከጼዴቅ ነበር። ስለዚህ እርሱ ከአባቶች አንዱ እንጂ ወልደ እግዚአብሔር አይደለም እያለ ያጠፋውን አረመ። ቅዱስ ቄርሎስም ነገሩ ሲሰማ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ችግሩንም እጂግ መንፈሳዊ በሆነ መንገድ ፈታው።
በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ቁምነገሮችን መውሰድ የምንችል ይመስለኛል። በመጀመሪያ እነማን ሊስቱ እንደሚችሉም መረዳት እንችላለን። እግዚአብሔር ካልጠበቀን በቀር በተምሪያለሁ፣ አንብቤያለሁ ፣ አውቃለሁ ባዮች ይቅርና እንደዚህ አባት የበቁትም ሳይቀሩ የመሳት ሁኔታ ይገጥማቸዋል። እንኳንስ ነገሮችን በትንሽዬ ዕውቀት የምናየው የእኛ ትውልድ ይቅርና በቅድስና ያላቸው ሳይቀር ለስሕተት እንደሚጋለጡ በቂ ምስክር ይመስለኛል። ይህ አባት በሁለንተናው ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ነበር። ይህም ሆኖ ሕሊናው የራሱን መረዳት መከተል ስትጀምር ደግሞ ስሐተት ወዲያው ስታጠምደው እንመለከታለን። ይህ እንግዲህ የተጻፈው ለሰው የታወቀ ስሕተት ስለሆነ እንጂ ለሰው ያልታወቀማ ብዙ ስሕተት ሊኖረን እንደሚችል ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም። ሁለተኛው ነገር ኦርቶዶክሳዊያን የሆኑ ሰዎች ትልቅ ስሕተት እንኳ ቢሳሳቱ እንዴ መፍታት እንዳለብንም ከዚህ ታሪክ መረዳት እንችላለን። በርግጥ መፍቻ መንገዱ እንዲህ ዓየነት ብቻ ነው ማለም አይደለም። ወደ ሌላ ታሪክ ላምራና ሌላ መንገድም እንመልከት ።
አሁንም በአበው ሕይወት ውስጥ እንዳነበብኩት ታሪክ የተፈጸመው በመጀመሪያው ምዕተ ዓመተ ክርስትና ነው። ለብቃት የደረሰ አንድ ካህን ነበር። ይህ ካህን ረዳት ካህንም ዲያቆንም ስላልነበረው ብዙ ጊዜ ብቻውን እየቀደሰ አማኞችን ያቆርብ ነበር። በዚህም ምክንያት በቅዳሴ ጊዜ ሁልጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ በመሰዊያው አጠገብ ቆሞ ይታየውና ያጸናው ነበር። አንድ ቀን ግን አንድ ዐዋቂ ዲያቆን ሊጠይቀው ሲመጣ ቅዳሴ እንዲረዳው ይዞት ገባ። ያ ዘመን እንዳሁኑ የቅዳሴ መጻሕፍት በመጽሐፍ ተጽፈው ስላልነበሩ በትውፊት የተቀበሉትን መሠረታዊ ነገር ይዘው በቃላቸው እየጸለዩ እየቀደሱ ነበርና የሚያቆርቡት ይህም አባት በዚያው መንገድ ቅዳሴውን ወደ መቀደስ ገባ። ቅዳሴው መካከል ላይ እያሉ ያ እንግዳ ዲያቆን በቅዳሴው ላይ ከምትጸለያቸው ጸሎቶች መካከል አሳፋሪ የሆኑ የኑፋ/ቄ ቃላትን ተጠቅመሃል አለው። ያ አባትም ደንገጥ ብሎ በቅዳሴ ጊዜ ሁሉ የማይለወን መልአክ ዘውር ብሎ ይህ ዲያቆን የሚናገረኝ እውነት ነውን ሲል ጠየቀው። መልአኩም አዎን ሲል መለሰለት ። በዚህ ጊዜ ያ ካህን ታዲያ እስከዛሬ ለምን አልነገረከኝም ሲል መልአኩን መልሶ ጠየቀው። መልአኩም ሰዎች ስሕተታቸውን ከሰው ተምረው ሲያስተካክሉ እግዚአብሔር ስለሚደሰት ለዚህ ብዬ ነው ዝም ብዬ የጠብቅሁት አለው ይላል ታሪኩ።
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6303