tgoop.com/tseomm/6277
Last Update:
እመቤታችን ጥንተ አብሶ የለባትም!!!
አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢያት (ጥንተ አብሶ ያላገኛት)፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ከመውለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሀሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ከተለዩ የተለየች፣ ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት። መኃ 4፥7 ምልዕተ ጸጋ፣ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ!ተብላ በመላእክት አንደበት በቅድስናዋ ትመሰገናለች
ሉቃ 1፥28-30።እመቤታችን በውስጥ በአፍአ
በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል።
አምላክን ለመውለድ፣ ያስመረጣት፣ ያበቃት፣ ድንግልናዋ ንጽሕናዋ ነው። ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።
እንዲያው ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ (መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠበቃት) የሚለው ምንድን ነው? በሉቃ 1፥28-38 ያሉትን የቅዱስ ገብርኤል ብሥራታዊ ቃላት በኃላፊና በትንቢት የግስ ዐመላቸው በመዘርዘር የዐቀባን መሠረትነት ያስረግጣሉ። ጸጋን የተመላሽ ሆይ የሚለው ቃል በኃላፊ (past tense) እንጅ በትንቢት (future tense) አልተነገረም፣ ማለትም ወደፊት ጸጋን ይሞላብሻል፣ ከሴቶችም ሁሉ የተባረክሽ ትሆኛለሽ አላላትም። እንደገና መልአኩ በሰላምታው መደንገጧን አይቶ ማርያም ሆይ
በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻል አትፍሪ
አላት። አሁንም የመላአኩ ማረጋጊያ ዐረፍተ ነገር ኃላፊ እንጅ ትንቢት አይደለም፣ አግኝተሻል
አላት እንጅ ወደፊት ታገኛለሽ አላላትም። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ከመፀነሷ በፊት ወይም ወደዚህ ዓለም ከመምጣቷ በፊት ጀምሮ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ ያልነበረባት መሆኑን ያሳያል።
ኤርምያስን በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሸሃለሁ ኤር1፥5 ሲል ለነቢይነት ለመረጠው ኤርምያስ ይህን ያህል ክብር የሰጠ አምላክ ለእናትነት የመረጣትን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ አንጽቶ ቀድሶ ለመጠበቅ ምን ይሳነዋል?
ከቅዳሴ ማርያም ንጽሕናሽን ባወቀ ጌዜ መልአኩን ላከ አለ እንጅ ሊያነጻሽ መልአኩን ላከ አላለም።ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖት አበው የዮሴፍ የእመቤታችን ንጽሕና አለመረዳት ሲገልጽ "ከንጹሕ ዘር የተፈጠረች
ድንግል የእግዚአብሔር ማደሪያ እንድትሆን
አላወቀም።ቅዱስ ቄርሎስ በሥጋ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም፣ከአብርሃም፣ከዳዊት፣ከተገኘ ባሕሪይም ኃጢያት የሌለበት በነፍስ በሥጋም
ፍጹም የሆነ አካልን ሊዋሐደው ፈጠረ እንደሚል በመጥቀስ የእመቤታችን ንጽሕና ጥንቱን በማኅፀነ ሀና ስትፈጠር ከጽንሰቷ ጀምሮ እንጂ ከመልአኩ ብሥራት ወዲህ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ለእናትነት የመረጣት ማደሪያውን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ከኃጢያት፣ከርኩሰት ከእድፈት፣ሁሉ ጠብቋታል።የሰው ልጆች የተያዙበት በአዳም በደል ወይም በራሳቸው በደል ምክኒያት የረከሱበት የኃጢያት ቅሬት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የለባትም አላገኛትም።ምክኒያቱም እርሱ ለራሱ ማደሪያ
አድርጎ ስለመረጣት ነው።
እመቤታችን ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ታስባ የኖረች፣የአዳም ኃጢያት ያልነካት፣ለአዳም ድኅነት ምክኒያት የሆነች፣ንጽሕተ ንጹሐን፣ቅድስተ ቅዱሳን፣በመሆኗ በሥጋም በነፍስም ፍጽምት
ትባላለች።ፍጽምት ማለት እንከን እና ጉድለት
የሌለበት ማለት ነው።ስለዚህ ቅድስት ድንግል
ማርያም የአዳም ኃጢያት የሌለባት በሥጋም
በነፍስም ንጽሕት በመሆንዋ መንፈስ ቅዱስ
ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ያ!በዘር የሚተላለፍ የመጀመሪያ በደል ፣ጥፋት ወደርሷ እንዳይተላለፍ ጠብቋታል።ሉቃ 1፥28፤መኃ 4፥12።
© መ/ር ፍሬው እውነቱ።
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6277