tgoop.com/tseomm/6174
Last Update:
የነባሕታዊ ገብረ መስቀል ውርስ (የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላለቀ የቤት ሥራ)
+ + + + +
የደርግ መንግሥት እንደወደቀ አንድ የ27 ዓመት እጅግ ቆንጆ እና ንግግር አሳማሪ ወጣት ከሆነ ቦታ ብቅ አለ፡፡ ‹‹ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከስልጣን እንደሚወርድ ነግሬው ነበር›› በሚል እና እግዚአብሔር መሐሪ ሳይሆን መቅሰፍት አውራጅ እንደሆነ በሚያስጠነቅቁ መልእክቶች ተሞልተው እጅግ በሚገርም ፍጥነት የአዲስ አበባን ብሎም የአንዳንድ የሀገራችንን ቦታዎች ምዕመናን ተቆጣጠረ፡፡ ይህ የዛን ጊዜ ወጣት ራሳቸውን ባሕታዊ ገብረ መስቀል በማለት አሳወቁ፡፡
የቡና ተክልን ጌታችን ሲሰቀል ሌሎች ሲጠወልጉ እርሱ ብቻ ለምልሞ የተገኘ ነው የሚል ምንጩ ያልታወቀ ትምሕርት በማስተማር በየሰዉ ቤት ያለ ሲኒና ጀበና አሰበሩ፣ ወጣቶችን በባዶ እግር ከአንድ ደብር ወደ አንዱ ደብር እንዲሄድ አደረጉ፡፡ የተከተላቸውን ሕዝብ ይልቁንም ወጣቱን እርሳቸው ወደፈለጉበት ቦታ ብቻ መንዳት ተያያዙት፣ ቅዱስ ፓትርያሪኩን፣ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን ሊቃውንትን እንዳይሰማ ከእጃቸው መስቀል እንዳይባረክ አደረጉ፡፡ አንድ ጊዜ በረከታቸው ይደርብንና የቅዱስ አማኑኤል ቀን አቡነ ሰላማ (የባሌው) ቀድሰው ‹‹ከኃጢአት ማሠሪያ እግዚአብሔር ይፍታ›› ሲሉ እጅግ ብዙ ሆነው ቤተ መቅደሱን የሞሉት ተከታዮቻቸው ‹‹ተክልዬ ይፍቱን›› ብለው ማስደንገጣቸውን አስታውሳለሁ፣ እንደዚሁ በወቅቱ የሆነ ንግሥ ያለበት ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመጡ የባሕታዊ ተከታዮች መንገድ ዘግተው አናሳልፍም ሲሉም አስታውሳለሁ፡፡
በወቅቱ ባሕታዊ ገብረ መስቀልን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ አንጻር መቃወም ከስድብ እስከ ዱላ የሚደርስ የመልስ ምት ነበረው፡፡ አንዳንዶች እንደመከራከሪያ የሚያቀርቡት ደግሞ ‹‹ወጣቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን አመጡት እንጂ ሌላ ምን አደረጉ? .. .. . ከቡና እና ከጫትና ከሲጋራ ሱሰኝነት አላቀቁት እንጂ ምን አደረጉት? .. . . እናንተ ሊቃውንት የምትሏቸው የሳቸውን ሩብ ሰርተዋል? ምቀኝነተት ነው እንጂ ድሮም ሰው ሲሠራ አይናችሁ ደም ይለብሳል›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ባሕታዊው ተቃውሞዎችን የሚያረግቡበት አንዳንድ በጎ ሥራዎችን በመሥራት እጅግ ሃብታም ሆኑ፣ ምዕመኑ አስራትና በኩራቱን ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለባሕታዊ መመገበር ተያዘ፡፡ ባታዊው በመሐል ሚስትም አገቡ፣ በብራቸው መጠን አሁን ድረስ የሚደግፏቸው ትላልቅ ሰዎች አሏቸው፡፡ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን መርሐ ግብርም አላቸው፡፡
ይህን የባሕታዊ ገብረ መስቀል በማር የተለወሰ ክፋት ያስታወሰኝ ትናንትና እጅግ በሚገርም የባለሙያ እና የአመራር ጥበብ ታድሶ የተመረቀውን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር እና ለማስቀደስ ስሄድ መንገድ ላይ ከተገናኘዋቸው ሰዎች ጋር የነበረኝ ውይይት ነው፡፡
አብረውኝ የሚጓዙ ምዕመናን በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨውን ‹‹መስቀሉን ለመርገጥ አትሂዱ›› የሚለውን የአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ‹‹ተቆርቋሪዎችን›› ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ትዕዛዝ አፍርሰው የመጡ ቢሆንም ቅሬታቸውን ግን መደበቅ አልተቻላቸውም፡፡
‹‹የመስቀሉ መረገጥ ግን በጣም ያሳስባል፣ መምሕር ደረጄ ዘወይንዬ እና አንዳንድ በግልጽ የሚናገሩ የቤተ ክርስቲያን መምሕራን ቢናገሩም ለ ‹‹ሆዳቸው ያደሩና ከመንግሥት ጋር ተሻርከው ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው የሰጡ ጳጳሳት›› ለማስተካከልና መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም›› አለ፡፡
ሌላዋ ቀጥላ ‹‹መንግሥት ለምን ይመስልሃል ፈቃድና ገንዘብ የሰጠው? .. .. . መስቀሉ እንዲረገገጥ ስለሚፈልግ ነው›› አለች፡፡
ዝምታዬ ተጨማሪ ሐሜቶችን ለመስማት እንጂ ሌላ ጥቅም ስለሌለው ‹‹በወለሉ ላይ ያሉት የመስቀል ምልክቶች ዛሬ የተሠሩ ሳይሆን ከ81 ዓመትም የነበሩ ናቸው›› አልኩ፡፡
‹‹እንዴት ሊሆን ይችላል? . .. .. እኔኮ እዚህ አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግሁት ዛሬ ብቻ ነው ምንጣፍ የተነሳው ብዙ ጊዜ ተቀይሯል እና የዛን ጊዜ ሳይታይ ዛሬ እንዴት ታየ? . .. . ውሸት ነው አሁን ነው የሠሩት›› አለ፡፡
ሌላኛዋ ተለሳልሳ ‹‹ቢሆንም አሁን ሲታወቅ መነሳት አለበት፣ እ ደግሞ ለምዕመናን ጳጳሳት ይበልጥም ፓትርያሪኩና የአዲስ አበባ አቡነ ሔኖክ መግለጫ መስጠት ነበረባቸው›› አለች
‹‹በብጹዕ አቡነ ሔኖክ የሚመራው ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ላይ ስለጉዳዩ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ በመግለጫውም (ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም የተሰጠ ነው) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የእድሳት እና የማስተካከያ ሥራዎችን ለመሥራትም ጊዜ እንደሚፈልግ ገልጸዋል›› አልኩ፡፡
ተጨማሪ ውይይት ሳናደርግ ሁላችንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገብተን ተለያየን፡፡
ግን እስከመቼ ነው እነ ደረጄ ዘወይንዬ . .. .. እነ መምሕር እገሌ፣ እነ ዲያቆን እገሌ፣ እነ ወጣት እገሌ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ባልሆነ መዋቅር የሚመሯት እስከ መቼ ነው?. .. .. የእነዚህ ሰዎች ልክና ገደብ የት ድረስ ነው? . . . በተለያየ አገጋጣሚ ቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትን ‹‹ሆድ አደር . .. . መለካዊ እያሉ የሚሳደቡት እስከመቼ ነው? ሃሳባቸው ካልተሳካ ባላቸው ሚዲያና ኔትወርክ እንደፈለጉ የሚፋንኑት እስከ መቼ ነው? በእኔ ልክ ካልጮሃችሁ ተሳስታችኋል፣ ምዕመኑን አሳልፋችሁ ሰጥታችኋል እያሉ ምዕመኑን ተሳዳቢ፣ አባቶቹን የማያከብር የሚያደርጉት እስከመቼ ነው? .. . . ሲፈልጋቸው ምዕመነኑን ቤተ ክርስቲያን ሂድ ሲያሰኛቸው አትሂድ የሚሉት እስከመቼ ነው?
ከቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መዋቅር የበለጠ ታምነው አስራትና በኩራት የሚሰበስቡት እስከመቼ ነው? .ምዕመኑ በሰጣቸው ገንዘብ የሆነ ቦታ ሄደው የሆነች ነገር አድርገው እግረ መንገዳቸውን የቤተ ክሕነተት ሰዎችን አንቋሸው የሚመለሱት እስከ መቼ ነው?
🖍 Abrham Yiheyis
BY ኦርቶዶክሳዊ መጻሕፍት እና ጽሑፎች Tsegaye kiflu
Share with your friend now:
tgoop.com/tseomm/6174