tgoop.com/nshachannel/1159
Last Update:
+ አምናለሁ እና አላምንም +
ልጁ የታመመበት አባት ነው:: ጌታን "ቢቻልህስ ልጄን ፈውስልኝ" አለው:: ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡ አለው።
ይህን ጊዜ ሰውዬው "ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው፡ አለ" ማር. 9:24
የዚህ ሰውዬ ንግግር ፍቺ የሚፈልግ ቅኔ ይሆንብኛል "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው"
ይኼ ሰውዬ ያምናል ወይንስ አያምንም?
ያምናል እንዳንል "አለማመኔን" ይላል ፤ አያምንም እንዳንል "አምናለሁ" ይላል:: የቸገረ ነገር ነው? ሁሉን አዋቂው መድኃኔዓለም ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶት ልጁን ፈወሰለት:: እኔ አላዋቂው ግን "አምናለሁ አለማመኔን እርዳው" የሚለውን ቃል እየደጋገምኩት ቀረሁ::
እያመኑ አለማመን እንዴት ያለ ነው? ብዬ መላልሼ ሳጤነው ግን ሰውዬው የእኔኑ ድክመት እየተናገረ እንደሆነ ገባኝ::
አምናለሁ እላለሁ:: በእርግጥም በፈጣሪ መኖር አምናለሁ:: ሁሉን እንደሚችልም አምናለሁ::
ግን ደግሞ በእርሱ ታምኜ አላውቅምና በሥራዬ እክደዋለሁ:: ኑሮዬ "በሥራቸው ይክዱታል" ከተባሉት የሚመደብ ነው:: (ቲቶ 1:16) አቅዋሜ የማመን ኑሮዬ ያለማመን ነውና አምናለሁ አለማመኔን እርዳው ብል ለእኔ የሚገባ ጸሎት ነው::
ወረደ ተወለደ ተጠመቀ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ ዐረገ ብዬ አምናለሁ:: በትሕትና መውረድን ፣ በንስሓ መወለድን ፣ በታናሽ እጅ ዝቅ ብሎ ጽድቅን መፈጸምን ፣ መከራን በትዕግሥት መቀበልን ፣ ከመከራ ሞት ወዲያ ተነሥቶ በክብር ከፍ ማለትን ግን እኔ ሕይወት ላይ አላውቀውም:: የምተርከው ክርስቶስ እንጂ የሚተረክ ክርስትና የለኝም:: ስለዚህ አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በልኬ የተሰፋ ጸሎት ነው::
መች በዚህ ያበቃል::
እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳው::
ከምግብ እጾማለሁ ከኃጢአት ግን አልጾምም:: ሥጋ መብላት ትቼ የሰው ሥጋ በሐሜት የምበላ ነኝና እጾማለሁ አለመጾሜን እርዳሁ እላለሁ::
እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው::
ቆሜ የማደርሰው ጸሎትስ አለኝ:: ግን ልቤ ሠላሳ ቦታ ደርሶ ይመለሳል:: የምጸልየው ማናገር የማልፈልገውን ሰው በግድ የማናግር ያህል የግብር ይውጣ እንጂ ነፍሴ እርሱን ሽታ አይደለምና እጸልያለሁ አለመጸለዬን እርዳው እላለሁ::
እሰግዳለሁ አለመስገዴን እርዳውስ?
ላቤ እስኪወርድ ሰግጄ አውቃለሁ:: ልቤ ግን አንዴ አልሰገደም::
ጌታ ሆይ እመጸውታለሁ አለመመጽወቴን እርዳው:: እዘምራለሁ አለመዘመሬን እርዳው:: አስቀድሳለሁ አለማስቀደሴን እርዳው:: እማራለሁ አለመማሬን እርዳው:: ሆኜ ያልሆንሁትን አድርጌ ያላደርግሁትን ሁሉ አንተ ታውቀዋለህና እርዳኝ::
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
BY ፍኖተ ሕይወት
Share with your friend now:
tgoop.com/nshachannel/1159