tgoop.com/nshachannel/1110
Last Update:
+ የሚካኤል ክንፉ +
ቅዱሳን መላዕክት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ብዙ ጊዜ ሲዖልን በምልጃቸው በርብረው ሰይጣንን ጉድ ቢሰሩትም የቅዱስ ሚካኤል ግን ይለያል። በእርግጥ ሲዖልን በርብሮ ነፍሳትን በማውጣት እመቤታችንን የሚተካከላት የለም፤ ምክንያቱም በወለደችው በአንድ ልጇ ሲዖልን ባዶ አስቀርታበት ሰይጣንን ጉድ ሰርታው ነበር። ለዚህም ነው ከፍጥረት ሁሉ አስበልጦ ሰይጣን እመቤታችንን የሚጠላት። ከእመቤታችን ቀጥሎ ግን ነፍሳትን ከሲዖል በምልጃው በርብሮ በማውጣት ቅዱስ ሚካኤልን የሚተካከል ያለ አይመስለኝም። አንድ ሰው ወፍጮ ቤት ገብቶ የወፍጮ ብናኝ ሳይነካው መውጣት እንደማይችል ሁሉ ቅዱስ ሚካኤልም ለየሆነ ጉዳይ ሲዖል ደረስ ብሎ ሲወጣ በክንፉ ነፍሳትን ሳይዝ መውጣት አይችልበትም።
ገና ሲነበብ አጋንንትን በሚያርደው በድርሳነ ሚካኤል ጥቅምት ንባብ ላይ እንዲህ ያለ ውብ ተዓምር ተጽፎልናል። "ከደቂቀ አዳም ወገን ሰውነቱ በኃጢአት የረከሰ አንድ ሰው ነበረ፤ ያ ሰውም ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ከተንኮልና ከክፋት በስተቀር አንዳችም በጎ ሥራ ሰርቶ አያውቅም። ነገር ግን አንድ ዓላማ ብቻ ነበረው፤ ይኸውም በየወሩ ቅዱስ ሚካኤልን በዓል ማክበር፣ ዝክሩን እየዘከረ ለነዳያን ማብላት ማጠጣት ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ያ ሰው ሞተና አጋንንት ይህች ነፍስ የኛ ናት በማለት ሲደነፉ ሚካኤል ግን የኔ ናት እያለ ይከራከር ነበር።
እንዲህም የኔ ናት፣ የኔ ናት በመባባል ከጌታ ዙፋን ፊት ስለቀረቡ ጌታ አራት አማራጭ ነገሮች አቀረበላቸው። ይህም፦ ሚካኤል ወስዶ ይደብቀው፣ እናንተ ግን ፈልጋችሁ ብታገኙት ውሰዱት፤ ወይም እናንተ ወስዳችሁ ሸሽጉትና ሚካኤል ፈልጎ ካገኘው ይውሰደው፤ ከእነዚህ አንዳቸውን ምረጡ አላቸው። እነርሱ ግን ሚካኤል ወስዶ ከመንበረ መለኮት ቢሸሽገው ምን ለማድረግ እንችላለን እያሉ በሃሳብ ጭንቅ ተዋጡ። ከብዙ የሃሳብ መለዋወጥ በኋላም እኛ እንሸሽገዋለን ብለው ያን ሰው ዕመቀ ዕመቃት አውርደው የገሃነመ እሳት አዝዋሪት ባለበት ጥልቅ ባሕር ውስጥ ደበቁትና እንግዲህ ሚካኤል ፈልጎ ያግኘው ተባባሉ።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል እነዚያን አጋንንት ከዚህ ቦታ አካባቢ ዘወር በሉ አላቸውና ወደ ሲዖል ገብቶ መፈለግና መበርበር ጀመረ፤ ነገር ግን የሚፈልገውን አላገኘም ነበረ። ነገር ግን ፈልጎ ሲወጣ በአንድ ክንፉ ፯ ዕልፍ ነፍሳት አወጣ፤ በሁለተኛውም ክንፉ እንዲሁ አወጣ፣ በሦስተኛውም አወጣ፣ በመደጋገምም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነፍሳትን አወጣ፤ ሆኖም ሊያገኘው አልቻለም። በዚህ ሰው ምክንያት ያወጣቸው ነፍሳት ቁጥራቸው 7540 ደረሰ፤ ከነዚህም ውስጥ ያልተጠመቁ አረመኔዎች ይገኙባቸው ነበር። ያን ጊዜ የሰማይ መላዕክት ሁሉ ይህስ እጅግ በጣም አስደናቂ ነገር ነው አሉ።"
ከዚህ ውብ ታሪክ የምንማረው ነገር ቢኖር ቅዱስ ሚካኤልን ይሁን ማንኛውንም ቅዱስ መዘከር በፍርድ ቀን ጠበቃ ማቆም ማለት ነው፤ ስለ እኛ ነፍስ ከአጋንንት ጋር ይከራከሩልናልና። የሚገርመው ደግሞ በዚያ ኃጥእ ሰው ቅዱስ ሚካኤልን መዘከር ምክንያት ብዙ ሺህ ነፍሳት ምሕረትን አገኙ። እኛም የፈለገ ኃጢአተኛ ብንሆን ቅዱሳንን መዘከራችን ከእኛ አልፎ የብዙ ነፍሳት መዳኛቸው ሊሆን ይችላልና ቅዱሳንን ከመዘከር መባዘን አይገባንም።
BY ፍኖተ ሕይወት
Share with your friend now:
tgoop.com/nshachannel/1110