tgoop.com/nshachannel/1034
Last Update:
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን! †
እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን።
በአንድ ሀገር አስተራኒቆስ የሚባል መኮንንና ሚስቱ አፎምያ ይኖሩ ነበር፡፡ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ቅዱስ ሚካኤልን የሚወዱ ነበሩ፡፡ ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ በቅዱስ ሚካኤልም ስም ድሆችን እየረዱ ሲኖሩ አስተራኒቆስ ይታመማል፡፡ ያን ጊዜም ሚስቱ አፎምያ እኔን ይጠብቀኝ ዘንድ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አሠርተህ ስጠኝ አለችው፡፡ እርሱም እንደለመነችው በልዩ ልዩ ጌጣጌጥ በወርቅ ቅብ አሠርቶ ሰጣት፤ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ባሏ ሞተ፡፡
ቅድስት አፎምያ ባሏ ከሞተ በኋላ ዘወትር በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ፊት እየቆመች የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ እዘንልኝ ምሕረትን ከአምላክህ ለምንልኝ ጠብቀኝ እያለች ትፀልይ ነበር፡፡ ሰይጣንም በጾም በጸሎቷ በምጽዋቷ ቀናባት ሊያሳስታትም ፈልጎ ብዙ ልጆች የየዘች ሴት መስሎ ወደ እርሷ መጣ፡፡ ቅድስት አፎምያንም ‹‹ጾም አታብዢ በኋላ ትከሻለሽ ፤ ለድሆች አትመጽውቺ በኋላ ድሀ ትሆኛለሽ፤ ጸሎት ማብዛት ምንም አይጠቅምሽም፡፡ ደግሞ ባል አግብተሽ ልትኖሪ ይገባል፤ እኔም የመጣሁት ከንጉሡ ተልኬ ነው፤ ንጉሡ አንቺን ሊያገባ ይፈልጋል፤ አንቺም ይህን እድል ተጠቀሚበት›› አላት፡፡ ቅድስት አፎምያ ግን በሰይጣን ንግግር አልተታለለችም፤ ይልቅ ጾም ጸሎት እንደሚያስፈልግ
ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እየጠቀሰች ነገረችው፡፡ ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል እንዲሳለም ብታመጣ ሰይጣን ፈርቶ ሮጠ፡፡ ቅድስት አፎምያንም ‹‹በያዝሽው ሥዕል አትመኪ በሰኔ 12 ቀን ሚካኤል በአምላኩ ፊት ሊሰግድና የሰዎችን ልመና ሊያቀርብ በእግዚአበሔር ፊት ሲቆም ያን ጊዜ መጥቼ አስትሻለሁ›› አላት፡፡ እርሷም በትእምርተ መስቀል ብታማትብ ከአጠገቧ ጠፋ፡፡ እርሷ ግን ዘወትር በጾም በጸሎት ትተጋ ነበር፡፡
በሰኔ 12 ቀን ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ተገለጠ፡፡ ለቅድስት አፎምያም "ሰይጣን ያለውን ሰምቻለሁ እጠብቅሽም ዘንድ ከሰማይ ወረድኩ ስለዚህ ለእኔ ስገጂልኝ" አላት፡፡ ቅድስት አፎምያም "እውነት አንተ ሚካኤል ከሆንክ በቤቴ ውስጥ እንዳለው ሥዕል የመስቀል ምልክት የታለ የያዝከው? አለችው፡፡ ሰይጣንም "ለእኛ ለመላእክት እኮ ምንም ምልክት የለንም አላት፡፡ እርሷም መልሳ ንጉሥ ማኅተም የሌለውን ደብዳቤ ቢልክ የሚያመነው የለም እንዲሁ መስቀል ያልያዘን መልአክ ሁሉም ይንቀዋል አይቀበሉትም" አለችው፡፡ ያን ጊዜም ሰይጣን መልኩን ለውጦ ጨለማ መስሎ ዘሎ አነቃት፤ እርሷም ‹‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ከጠላቴ አድነኝ›› አለች፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ሊያጽናናት ታላቅ ብርሃን ለብሶ መጣ ቤቱንም በብርሃን ሞላው፡፡ ሰይጣንንም በበትረ መስቀሉ መታውና መሬት ላይ ጣለው ሰይጣንም "እባክህን አታጥፋኝ" ከእንግዲህ ሥዕልህ ወዳለበት ስምህ ወደተጠራበት አልደርስም አለው፡፡ ያኔም ሰይጣንን አዋርዶ አሳፍሮ ተወው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም "አፎምያ ሆይ! ዛሬ ነፍስሽ ከሥጋሽ ትለያለች መላእክትም ነፍስሽን ወደ ገነት ያሳርጓታል ስለዚህም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒጂና ጸሎት አድርጊ" አላት፡፡ እርሷም ንጹሕ ልብስ ለብሳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደችና የጌታችንን ሥጋና ደሙን ተቀበለች፡፡ ከዚያም ንብረቷን በሙሉ ሸጣ ለድሆች እንዲሰጥ ለጳጳሱ አደራ ሰጠችው፡፡ በቤቷ የነበረውም ሥዕል በርሮ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ገባ ካለ ገመድ ተንጠለጠለ፤ ቅጠል አወጣ ፍሬም አፈራ፡፡ ብዙ አጋንንት ያደረባቸው የታመሙም ሰዎች ቅጠሉን ቆርጠው ወስደው ይታጠቡበትና ይድኑ ነበር፡፡
"ኦ ሚካኤል! ኦ ሚካኤል! ኦ መተንብል!
ካህነ አርያም ትሰመይ ቢጸ ሱራፌል፥
ዘእምርኡሳን ርኡስ ወዘእምልዑላን ልዑል
ጊዜ ጸዋዕኩከ ቅረበኒ በምሕረት ወሣህል!"
ቅዱሳን መላእክት እንደ ታላቅ ወንድም የሚያስቡልን የሚንከባከቡን ከሰይጣን ወጥመድ የሚያድኑን ናቸው። የቅዱሱ መልአክ ተራዳኢነት አይለየን!!!
BY ፍኖተ ሕይወት
Share with your friend now:
tgoop.com/nshachannel/1034