tgoop.com/nshachannel/1012
Last Update:
[ ነገረ መንፈስቅዱስ ]
መንፈስ ቅዱስ በሁሉ ቦታ ያለ ነው፡፡ታድያ ለሐዋርያት ወረደ ማለት ምን ማለት ነው? ወረደ የሚለው በአካል በሁሉ ቦታ ላለ አይነገርምና፡፡ ወረደ ማለት ጸጋውን ሰጠ ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ይህ ጸጋም ከአብ እና ከወልድ ተለይቶ የመንፈስ ቅዱስ ብቻ የሆነ የተለየ አካላዊ ግብር አይደለም፡፡ የሦስቱም ባሕርያዊ ግብር (ሥልጣናዊ) ግብር ነው እንጂ፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ጸጋ ዘአብ ያለውን ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በቅዳሴ ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ብለውታል፡፡ ባሕርያዊ ግብር ስለሆነ ሦስቱም ይጠሩበታልና፡፡
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወረደ ማለት ጸጋ ለሰው ተሰጠ ማለት ነው፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መንፈስ ቅዱስ ይለዋልና፡፡ ይህን ጸጋ ደግሞ ቤተክርስቲያን ተቀብላ እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሱ ሰዎች ስታድል ትኖራለች በዚህም ምክንያት የጸጋው ግምጃ ቤት ትባላለች፡፡ በነገራችን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከምጽአት በኋላም እየተሰጠ ለዘለዓለም ይኖራል እንጂ አያልቅም፡፡ ይህንንም የመጻሕፍተ መነኮሳት መተርጉማን ተወስኮ ዘነሳእያን ይሉታል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ ላደረጉ ሰዎች እየተጨመረ የሚኖር ጸጋ ማለት ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በዕለተ ጰራቅሊጦስ ተወለደች መባሉ ሙሉ ጸጋን አግኝታ ጸጋን የምትሰጥ ሆነች ለማለት ነው፡፡ ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ካገኙ በኋላ ፈሪ የነበሩት የማይፈሩ ሆኑ፡፡ እስከሞት ድረስ እውነትን እየመሰከሩ የሐሰትን ሐሰትነቱን እየገለጡ ኖሩ፡፡ ሃይማኖት የራስን እውነት መናገር ብቻ አይደለም፡፡ የሌላውንም ስህተት ሳይፈሩ ስሕተትነቱን መናገር ነው፡፡ ቅዱሳን ሊቃውንት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ የሚታወቁትም በዚህ ነው፡፡ እዉነትን በአደባባይ ይሰብካሉ፡፡ ውሸትን ደግሞ በአደባባይ ያጋልጣሉ፡፡
ሃይማኖተኝነት ይህ ነው፡፡ የአንተን እውነት ብቻ እየተናገርክ በሁሉ ዘንድ መወደድ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ውሸት በመናገር በብዙዎች ዘንድ መጠላትም አለበት፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ ግዞት የተፈረደበት የንግሥቲቱን ክፉ ስራ በማጋለጡ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ሲወርድ ጥቡዓን ሆኑ ማለት ይህ፡፡ ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ የውሸትን ውሸትነት የእውነትን እውነትነት በአደባባይ ገለጡ ማለት ነው፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው ብዙው ሰው ይጠላቸው ይሰድባቸው ነበር፡፡ ያ ብቻ አይደለም ይገድሏቸውም ነበር፡፡
ጰራቅሊጦስ፡
ጰራቅሊጦስ ማለት ናዛዚ የሚያረጋጋ ማለት ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት መጽንዒ የሚያጸና ማለት ነው። ጰራቅሊጦስ ማለት መንጽሒ ከኃጢአት የሚያነጻ ማለት ነው።
ጰራቅሊጦስ ማለት ከሣቲ ምስጢር ገላጭ ማለት ነው።
እስመ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ዘተሰውጠ ላእለ ሐዋርያት። በመንፈስ ቅዱስ በነገረ ኩሉ በሐውርት።
እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም አደረሳችሁ!
በሐዋርያት ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ ይደርብን!!!
BY ፍኖተ ሕይወት
Share with your friend now:
tgoop.com/nshachannel/1012