tgoop.com/learn_with_John/863
Last Update:
https://youtu.be/4s9LW4mhUqQ?si=EzwAsMh6cRJFCZHK
(መምህር ኢዮብ ይመኑ)
-እጠብቅሀለሁ-
እጠብቅሀለሁ በመጠቂያዬ፤
ትመጣለህና ሳትረሳ ጌታዬ።
ቀናት ቢያሰለቹ፥ ቢቆጠር ዘመናት፤
አምንሀለሁ ነፍሴን፥ እንደማትተዋት።
በምንም በየትም። በሁሉም ሁኔታ፤
እጠብቅሀለሁ፥ በእድሜ ጀምበር ማታ።
፡
አማርሬህ፥ አኩርፌህም፥ አምቼህም፥ እኔ አውቃለሁ፤
ትግስትህን ሳልታገስ፥ ብዙ ነገር ብዬሀለሁ፤
ለዘመኔ እሾህ ሆኜ፥ ከቤትህም ጠፍቻለሁ፤
አትድረስብኝ አልደርስም፥ ብዬ በስምህ ምዬ አውቃለሁ።
ማታ እግሮቼን አጥበህ፥ በትህትና ለመከርከኝ፤
አላውቀውም፥ ማነው እሱ፥ ብዬ ባፌ መሰከርኩኝ።
ስታበራ ብቻ ሳይሆን፥ ጌቴሴማኒ ፀዳል ስትሆን፤
ቀያፋም ቤት መጥቻለሁ፥ ስትገረፍ ጅራፍ ልሆን።
፡
ለካ እኔ ፈጠንኩ እንጂ፥ አንተ እኮ አልዘገየህም፤
በሰዓትህ ትመጣለህ፥ ቆየህ ምነው? አልልህም።
እንደ ዕንባቆም እጮሀለሁ፥ አምላኬ ሆይ እልሀለሁ፤
ስትሰጠኝ ብቻ ሳይሆን፥ ብትከለክለኝም እጠብቅሀለሁ።
ፀጋህን ከኔ ውሰድልኝ፥ እኔ አንተን ከማጣህ፤
እንደዘኪዎስ ከዛፍ ልውጣ፥ ቤቴ ግባ አይቼህ።
በዝምታ ልቤን ክፈት፥ ግባ ማነው? ሳልልህ፤
አንተ ብቻ ናልኝ እንጂ፥ ከቤቴ ጋር ላምልክህ።
፡
ደሞ እንዲህም ብዬሀለሁ፥ መቼ ጠይቄው መች መለሰ፤
ምነው ልቦናን ነሳኝ፥ እኔን ከሰው አሳነሰ።
ለምንድነው ያዋረደኝ፥ ዝም የሚለው እንዲህ ስሆን፤
ለካ አንተ የምትመጣው፥ እንደ አልዓዛር አፈር ስሆን፤
ለካ ህመም አይደለም፥ ሞትም አይደል የሚያቆምህ፤
በአራት ቀኔ ሳትፀየፍ፥ መቃብሬን ትከፍታለህ።
ለካ መሽቶም ትመጣለህ፥ እድሜ ዘመን አይገታህም፤
የጠበቀህ እርፍ ይላል፥ ላንተ ምንም አይሳንህም።
:
እንደ ዮሴፍ ብጠላ፥ በወንድሞቼ ብከዳ፤
በሰላሳ ዲናር ብሸጥ፥ ብንከራተት ምድረበዳ።
የአባቴ አይንም ቢፈስ፥ ቢናፍቀው የልጅ መልኬን፤
የሀሰት ፍርድ ቢፈርዱብኝ፥ ብወረወር እድሜ ልኬን።
ፍርድ አጣመው ቢያንገላቱ፥ ፍርዱም ቢሆን እድሜ ይፍታ፤
ማንም ዳግም አያስረኝም፥ አንተ መተህ ስትፈታ።
አንተ ምን ይሳንሀል፥ በወህኒው በኩል በር አለህ።
በጲጢፋራ መንበር፥ ልታነግሰኝ ትመጣለህ
፡
ታማኝ ነህ ለጠበቀህ፥ ማህጸንን ትፈታለህ፤
ሲስቁብኝ ልትባርከኝ፥ በመቅደስህ ትመጣለህ።
መካን ብባል የተጣለች፥ ስሜም እንኳ በቅሎ ቢሆን፤
መቶ ፍሬ ይገኝብኝ፥ አብዛኝና ለዘር ልሁን።
የሀናን ለቅሶ የሰማህ፥ የኤልሳቤትን እንባ ያበስክ፤
ልጅ የጠየቀችህን፥ በልጆች የምትባርክ፤
ዛሬ አለሁ ያንተ ሀና፥ ዛሬም አለሁ ያንተ ኤልሳቤት፤
እንደ ዮሀንስ ባርከህ ስጠኝ፥ ባንተ ጊዜ በለኝ አቤት።
:
መሮኛል ስልህ ወደላይ፥ የበታቼን ሳላየው፤
አንተ ባልቆረትከው ቀን፥ የራሴን ሞት የተመኘው።
ምነው መታገስ ከበደኝ፥ ነገን ዛሬ ደመደምኩት፤
ምነው ተስፋ ቆረጥኩ፥ ዛሬን አሁን ቀበርኩት።
እንደ ሙሴ በእድሜ ማታ፥ ከከንዓን ሩቅ ብሆን፤
የልፋቴን ሳልቀበል፥ ዕጣ ፈንታ ሞትን ቢሆን፤
በታቦርም ትመጣለህ፥ ቃልኪዳንህ አይታጠፍም
ካንተ ይሰጠዋል እንጂ፥ ሰው በራሱ አያተርፍም
:
ከእሳት በፊት ትደርሳለህ፤
ወይስ ነዶ ትመጣለህ፤
ስወገር ትደርሳለህ፤
ወይስ ፍርዱን ትሽራለህ፤
ስትታመም ትመጣለህ፤
ወይስ ስሞት ታስነሳለህ።
አልወተውትህም እታገስሀለሁ፤
በሁሉም ሁኔታ እጠብቅሀለሁ።
++++
የተናቀን የተረሳን፥ አንተ ስታስታውሰው፤
የጠሉኝ ቢሰበሰቡ፥ ቢሉኝ እንዳንተ እናንግሰው።
ቋጠሮዬን ስትፈታ፥ ከቀበሮ ደስታ ጠብቀኝ፤
ጽድቅህን እኔ እሻለሁ፥ መንግስትን አትንፈገኝ።
+++
( መምህር ኢዮብ ይመኑ)
ግጥም ደራሲ©ታዜና
™ #መንፈሳዊ_ግጥሞች
www.tgoop.com/Menfesawigetmoch
BY እልመስጦአግያ+++

Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/863