tgoop.com/learn_with_John/771
Last Update:
++ የሰይጣን ነጻ አውጪ +++
ብዙ ጊዜ በsocial mideaም ይሁን በብዙኃን መገናኛ በስፋት የሚታዩና ትልቅ ተደራሽነት የሚኖራቸው ነገሮች በማኅበረሰቡ ዘንድ የተከለከሉ እና ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶች ናቸው። እነዚያን ጉዳዮች በማውገዝም ይሁን "ጉድ እኮ ነው" በሚል አግራሞት ለሌሎች የሚያጋራቸውና አስተያየት የሚሰጥባቸው ተመልካች ቁጥር ጥቂት የማይባል ነው። ይህ ግርግር በራሱ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊል ግን በውስጣችን ያለውን "በተከለከለ ነገር የሚማረክ" ማንነታችንን በደንብ ያሳያል። አይሆንም ተብለን እየተከለከልን በገባንበት ሱስ፣ ወዳጅነት፣ ፍቅር፣ ትዳር የምንሰቃይ ስንቶቻችን እንሆን?
ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ትልቅ እንቅፋት የሚሆንብን ይህ የተከለከለውን የሚያሳድድ ክፉ አመላችን ነው። ፈጣሪያችን "አታድርጉ" ሲለን እኛን ለመጠበቅ ሳይሆን የእኛን ዓለም ለማጥበብ ሲል ያሰረን ያህል ይሰማናል። የተሰጡንን ሕግጋት ካልጣስንም ነጻነታችንን ተግባራዊ ያደረግን አይመስለንም። የተፈቀደልንን አናደርግም፣ ያልተፈቀደልን ያንንም ሳናደርግ አንውልም። እኛ እንዲህ ነን፦ ቀኝ ሲጠብቁን በግራ፣ በግራ ሲያስሱን በቀኝ ብቅ የምንል ጉራማይሌ ነን።
ከሁሉ የሚያስደንቀው ደግሞ በዚህ ጠባያችን "የሰይጣን ነጻ አውጪ" እስከ መሆን መድረሳችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው መድኃኒታችን ክርስቶስ ለዘመናት ባሪያ ያደረገንንና ሲረግጠን የኖረውን ሰይጣን በመስቀሉ ጠርቆ (አስሮ) ከመንገድ አስወግዶልናል።(ቆላ 2፥14) እኛን ከእርሱ ጋር በትንሣኤው ሲያስነሣን ያን ዕቡይ ጠላታችንን ግን እንሳለቅበት ዘንድ ከእግራችን ስር ጥሎልናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰይጣን ጌታ ከተሰቀለባት እለተ አርብ በኋላ በብረት ሳጥን እንደ ታሰረ ውሻ ሆኗል ይለናል። ስለዚህ እንደ ፈቃዱ ሊፈነጭና ማንም ላይ ሊሰለጥን አይችልም ማለት ነው። ነገር ግን ሰው በፍላጎቱ ወደ ታሰረው ሰይጣን በሄደና መዝጊያውን በከፈተለት ጊዜ ለታሠረው ሰይጣን ነጻነት ይሰብካል። በክፋት ጥርሶቹ ነካክሶ ያደማው ዘንድ በገዛ እጁ በራሱ ላይ ያነግሠዋል። በዚህም ሰው የተፈቀደለትን ንግሥና ትቶ የተከለከለውን የዲያብሎስ ባርያነት ኑሮን ይገፋል።
አባ መቃርስ እንዳለው "የሚወደውን ባለጠጋ እግዚአብሔርን ጠልቶ የሚጠላውን ደሃ ሰይጣንን ወድዶ የሚከተል" ሰው ምን ያህል ሞኝ ነው?!
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ
ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ቴሌግራም
https://www.tgoop.com/Dnabel
BY እልመስጦአግያ+++

Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/771