tgoop.com/learn_with_John/770
Last Update:
እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮትም ቅዱስ ጳውሎስ ለጥምቀት ምሳሌ አድርጎ ያነሣውን የግዝረት ሥርዓት ለሕፃናት ጥምቀት ማስረጃ አድርገው አስተምረውበታል፡፡ በአብርሃም ዘመን ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ወገን ለመሆን ምልክት ነበር፡፡ ስለዚህም በአብርሃም ቤት የሚወለዱ ሕፃናት ስምንት ቀን ሲሆናቸው እንዲገረዙ ሕግ ወጥቷል፡፡(ዘፍ 17፡10-14) ሕፃኑም በዚያ የቀናት ዕድሜ ላይ እያለ ይገረዛል እንጂ ቆይ ይደግና ጠይቀነው አይባልም፡፡ ልክ እንደ ግዝረቱ በሐዲስ ኪዳንም ጥምቀት ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ጋር በሕዋስነት የምንቆጠርበት ምሥጢር ነው፡፡ ግዝረት በሕፃንነት ይፈጸም እንደነበር፣ ጥምቀትም በሕፃንነት ይፈጸማል፡፡ እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስም አባባል ‹የጣቶቻቸው ጥፍር ሳይጸና› በጨቅላነት ዕድሜያቸው ይጠመቃሉ፡፡ ይኸው ሊቅ ሌላው የጥምቀት ምሳሌ የሆነውን ባሕር መሻገር በማንሣት ፣ ባሕሩን የተሻገሩት ሕፃናትም ጭምር እንደሆኑ ፣ጥምቀተ ክርስትናም ለሕፃናት ይፈጸማል ሲል ይናገራል (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡
ጥምቀተ ክርስትና ሁል ጊዜ ተጠማቂው ተጠይቆ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረው በኋላ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ ይህም እፍታ ለአዳም የልጅነትን ጸጋ ያገኘበት ጥምቀቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ በያዘው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ከመስጠቱ በፊት እንደ ጠየቀው አይናገርም፡፡ ታዲያ እንዴት የሠላሳ ዓመቱ ጎልማሳ አዳም ያልተጠየቀውን ጥያቄ የአርባን ቀን ልጅ ጠይቁ ይሉናል? ፡፡ እግዚአብሔር አዳምን አልጠየቀውም ማለት አስገደደው ማለት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሕፃናትን በቀጥታ እነርሱን አልጠየቀችም ማለት አስገድዳቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ አዳም የኋላ ኋላ በፈቃዱ ፈጣሪውን ክዶ ልጅነቱን እንዳጣ እንዲሁ የእግዚአብሔርን አባትነት ያልፈለጉትም አድገውም ቢሆን የመካድ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
ሌላው አንዳንድ ጊዜ ከማመን (ከትምህርት) ጥምቀት ሊቀድም የሚችልባቸውም ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ ዓለም ሲልካቸው ‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው› ሲል ያዘዛቸው (ማቴ 28፡19)፡፡ ልብ በሉ በዚህ የጌታችን ትዕዛዝ ውስጥ በቀዳሚነት የተነገረው ‹አስተምሩ› የሚለው ሳይሆን አጥምቁ የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ አድገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚገቡ ካልሆነ በቀር ለሕፃናት ጥምቀት ሊቀድም ይችላል፡፡ ደቀ መዝሙርነት የሚገኘው ከጥምቀት በኋላ ነው፡፡ ሳይጠመቁ ደቀ መዝሙርነት የለም፡፡
በአጠቃላይ ከላይ ያቀረብናቸው ነጥቦች የሕፃናትን ጥምቀት ተገቢነት የሚያሳዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ሲሆኑ በተቃራኒው ግን የሕፃናትን ጥምቀት የሚከለክል ምንም ዓይነት ትምህርት ወይም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ አናገኝም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባሯ ብትመሰገን እንጂ የምትነቀፍ አይደለችም።
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ
ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ቴሌግራም
https://www.tgoop.com/Dnabel
BY እልመስጦአግያ+++

Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/770