tgoop.com/learn_with_John/764
Last Update:
የሠጠው ዝርዝር እስካሁን ድረስ ዓለም የሚጠቀምበት የእስክንድርያ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ እንኳን አዋልድ መጻሕፍትን ቀርቶ የመጽሐፍ ቅዱስንም ቁጥር የወሰነችና ‘ይህ ይውጣ ይህ ይግባ’ የማለት ሥልጣን ያላት የእግዚአብሔር መንግሥት እንደራሴ ናት፡፡ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስታጣራ ያልተቆጣች ቤተ ክርስቲያን ገድላት ድርሳናትንና ተአምራትን ለማረም ልትቸገር አትችልም፡፡
ገድላት ድርሳናትና ተአምራትን ለማረምና ለማቅናት የምትችለው ግን ራስዋ ቤተ ክርስቲያንዋ እንጂ በጋራ በምንቀበላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ከእኛ ጋር መስማማት ባልቻሉ ሰዎች አይደለም፡፡ በልጁ መወለድ ከማይስማማ ሰው ጋር ስለ ልጁ አስተዳደግ መነጋገር እንደማይቻል በአዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊነት ከማያምን ሰው ጋር ስለ አዋልድ መጻሕፍት ይዘት መነጋገርም አይቻልም፡፡
ወንጌል የክርስትና ትምህርት መጽሐፍ ሲሆን ገድላት ደግሞ የወንጌሉ ሥዕላዊ መግለጫዎች /Iconography of the bible/ ተግባራዊ ክርስትና መማሪያዎች ናቸው፡፡ ገድላት ፣ ድርሳናትና ተአምራት ሲነሡ ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሌላ መጽሐፍ አንፈልግም’ ብለው የሚተቹ አካላት መጽሐፍ መሸጫ መደብሮቻቸው ጎራ ብትሉ ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ አይሸጥም’ አይሏችሁም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ የትርጉም መጽሐፎች ፣ ‘የሚስዮናውያን ታሪኮች’ ፣ ‘ሲኦል ደርሶ የመጣው ሰው ምስክርነት’ ፣ ‘የወንጌላዊው እገሌ የአገልግሎት ሕይወት ግለ ታሪክ’ ወዘተ የሚሉ መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው? አዋልድ መጻሕፍት ማለትም ይሄ ነው፡፡ ለእነርሱ ሲሆን ተፈቅዶ ለእኛ ሲሆን ከተከለከለ double standard theory ይሆናል፡፡ እኛ ግን የምናምነውን እስካወቅን ድረስ እምነታችንን አክብረን እንከተላለን እንጂ በሌሎች ሚዛን አናስመዝንም፡፡ ገድላት ድርሳናትና ተአምራት ምንም እንከን ባይኖራቸውም እንኳን የማይቀበሏቸው ሰዎች በይዘታቸው ላይ የሚሠጡት አስተያየት ዋጋ ሊሠጠው አይገባም፡፡
በገድላት ፣ ድርሳናትና ተአምራት ላይ የሚኖሩ የታሪክ ፣ የነገረ ሃይማኖት ፣ የትርጉም ወዘተ ልዩነቶችን ለማረም ያመነ ሰው መሆን ብቻም በቂ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ሆዱ ላይ ድንገት ስለት ቢሰካበት ይሄንን ሰው ለመርዳት ማንኛውም ተራ ሰው የሚመጣለት መፍትሔ የተሰካውን ቢላ እጀታ ይዞ ስለቱን ማውጣት ነው፡፡ ይሄንን ሲያደርግ ግን የሰውዬውን ሆድ እቃ ዘርግፎ ሊገድለው ይችላል፡፡ የቀዶ ሕክምና ባለ ሙያዎች ግን በጥንቃቄ ስለቱን ከሰውዬው አካል ለይተው በማውጣት ሌላው አካል ሳይጎዳ ማዳን ይችላሉ፡፡
በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የሚኖሩ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣትም ማንኛውም አንባቢ አይችልም፡፡ ‘ተረት ነው’ ብሎ ለማጣጣል ምንም እውቀት ስለማይጠይቅ ማንም ሊሠራው ይችላል፡፡ አዋልድ መጻሕፍቱን አጥርቶ ለአገልግሎት ለማዋል ግን አገባብ የሚያውቁ የቅኔ መምህራን ፣ ጥንታዊ ድርሳናትን መመርመርና መመዘን የሚችሉ የሥነ ድርሳናት ባለሙያዎች /ፊሎሎጂስቶች/ ፣ የመጻሕፍት መምህራን ፣ አዋልድ መጻሕፍቱን ከታሪክ አንጻር መተንተን የሚችሉ የታሪክ ምሁራን ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ዳራውን መቃኘት የሚችሉ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ወዘተ ለሺህ ዓመታት የተከማቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጻሕፍት ሀብት ማደራጀትና በጥራት ለትውልዱ በሚመጥን መንገድ የማቅረብ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ በሊቃውንት ጉባኤ እየታዩ ካሉና የብዙ ቀሳጢያን እጅ በየዘመኑ ካረፈባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ተአምረ ማርያም ነው፡፡
ከሁሉም በፊት ተአምረ ማርያምን በተመለከተ የሚሠራውን ሥራ ታላቅነት ለመረዳት የተአምረ ማርያምን ግዝፈት በማሳየት ልጀምር፡፡
ብዙ ሰው ተአምረ ማርያም ሲባል ስለ አንድ መጽሐፍ ብቻ እየተነገረ ስለሚመስለው በተአምረ ማርያም ላይ የሚነሡ ጥያቄዎች ስለ አንድ መጽሐፍ ብቻ የሚነገሩ ሊመስለው ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራትና ገዳማት የሚገኙ የተአምረ ማርያም የብራና ቅጂዎችና የታተሙ መጻሕፍትን አንድ ጊዜ ገልጠን በጋራ እናንብብ ቢባል ሁሉም መጻሕፍት በገፅ ብዛት ፣ በያዙት ተአምራት ቁጥር ፣ በተአምራቱ ቅደም ተከተል ፣ በተአምራቱ ውስጥ ባሉ ታሪኮች ዝርዝር ሁኔታ ብዙ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ስለዚህ ‘ተአምረ ማርያም ላይ እንዲህ ይላል ወይ?’ ለሚል ጥያቄ የአዋቂ ሰው መልስ የሚሆነው ‘የትኛው ቅጂ ላይ?’ የሚል ጥያቄ ነው፡፡
+ የተአምረ ማርያም የትመጣ (Origin) +
ወላዲተ አምላክን የሚመለከቱ መጻሕፍት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መነበብ የጀመሩት ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መሆኑ የታመነ ነው፡፡ በ300 ዓ.ም. በግብፅ በዐረቢኛ ተጽፎ በ600 ዓ.ም. ወደ ግእዝ የተተረጎመው ‘መጽሐፈ ስደታ ለማርያም’ ወይንም ‘ነገረ ማርያም’ ከተአምረ ማርያም በፊት ከተተረጎሙ የነገረ ማርያም መጻሕፍት መካከል ተጠቃሹ ነው፡፡ የPEMM researcher የሆኑት መሐሪ ወርቁ በ2022 ባጠኑት ጥናት እንደገለጹት ይህ የነገረ ማርያም መጽሐፍ Early Christian Infancy Gospelን በምንጭነት የተጠቀመ ሲሆን የግእዙ ትርጉም ከዐረቢኛው ይልቅ ድንግል ማርያምን በታሪኩ ማእከልነት የሚያስቀምጥ ነው፡፡ የመጽሐፈ ስደታ ለማርያም ሁለት ቅጂዎች በBritish Library የሚገኙ ሲሆን አንደኛው ለአፄ በካፋ እናት ለማርያማዊት (1720 ዓ.ም.) የተሠጠ ሌላኛው ለአፄ ኢያሱ ካልዕ (1730 ዓ.ም.) የተጻፈ ነው፡፡
ተአምረ ማርያም ራሱን ችሎ በመጽሐፍ ደረጃ መጻፍ የጀመረው ግን ከ13ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ያጠኑ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ ተአምረ ማርያም ከ13ኛው እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የቆየ መጽሐፍ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ዘመናት ቀስ በቀስ እየጨመረ እያደገ የመጣ አንድ ትልቅ የመጽሐፍ ዋርካ እንጂ እንደ አንድ መጽሐፍ ተጽፎ ተጠናቅቆ ሲወርድ ሲወራረድ እስከ ዛሬ የደረሰ አይደለም፡፡ በየስፍራው ያሉት የተአምረ ማርያም ቅጂዎች ሲመሳከሩ ትንሹ 3 ተአምራትን ብቻ የያዘ ሲሆን ትልቁ እስከ 390 ተአምራትን የያዘ ነው፡፡ በአጠቃላይ በተለያዩ መጻሕፍት ተበታትነው ያሉት ደግሞ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ተአምራትን ይሆናሉ፡፡ Princeton Ethiopian Eritrian and Egyptian Miracles of Mary (PEMM) በ2018 ይፋ ባደረገው ጥናት በየገዳማቱ ያሉት የተአምረ ማርያም የብራና ቅጂዎችም ከ560 እስከ 643 ይደርሳሉ፡፡
በ1300 ዓ.ም. ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከዐረቢኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመው የመጀመሪያው የተአምረ ማርያም ቅጂ ስምንት ተአምራትን ብቻ የያዘ ነበር፡፡ ከዚያም በ1400 በአፄ ዳዊት ዘመን የተጻፈው የተአምረ ማርያም ቅጂ ደግሞ ከዐረቢኛ የተተረጎሙ 75 ተአምራትን የያዘ ሲሆን በወርቅ ቀለም ያጌጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሥዕላት ያሉበትና ንጉሡም ከድንግል ማርያም እግር ሥር ሲወድቁ የተሣለበት ነበረ፡፡ (EMML 9002) [ይህ ቅጂ በግሸን ማርያም ዕቃ ቤት ይገኛል /1967 Diana Spencer] ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ በ1525 ዓ.ም. የተጻፈው ተአምረ ማርያም ደግሞ 350 ተአምራትን የያዘ ነበር፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሌላ ቅጂ ደግሞ 33 ተአምራትን ብቻ የያዘ ሲሆን ‘አኮኑ ብእሲ’ የሚል ርእስ ያላቸው አርኬዎች የተካተቱበት ነው፡፡
BY እልመስጦአግያ+++
Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/764