tgoop.com/learn_with_John/688
Last Update:
እናቱ እናቴ - ልደትሽ ልደቴ !
+ + +
ለእናትነት ክብር - እርሱ ከመረጠሽ
በዮሐንስ በኩል - ለእኔ ከተሰጠሽ
እኔም እርሱን ጌታ - ብዬ ከተቀበልሁ
ማዳኑን አምኜ - በሕጉ ስር ከዋልሁ
እናቱን እናቴ - ብየ ለመቀበል...
ጥያቄ ልደርድር? ለምን? እንዴት? ልበል?
+ + +
ልጅሽ በምድር ላይ - ሥጋሽን በመልበስ
አዳምን ሊያድነው - ለእኛም ጽድቅን ሊያወርስ
የረገጠው መሬት - የቆመበት ቦታ
ከቤተልሄም ዋሻ - እስከ ጎለጎታ
ቅዱስ ከተባለ - ውሎ ያደረበት
ልዩ ክብር ካለው - የተሰቀለበት...
አንችማ እናቱ - ማህፀን ዓለሙ
የሰውነት ልኩ - ሥጋውና ደሙ
እንዴት አትከብሪ!? እንዴት አትቀደሽ!?
እንዴት አትወደጅ!? እንዴት አትወደሽ!?
+ + +
እንኳንስ ለእኔና...
ለእርሱም ለጌታችን - ፈጣሪ ለሆነ
እናቱ መባልሽ - ይህ እውነት ከሆነ
እናቴ መሆንሽ - እንዴት አልታመነ???
+ + +
በሥጋ ያይደለ - በረቀቀ መንፈስ
እናቴ ሆነሽኝ - ያንችን ክብር ብወርስ
ይሄንን መታደል - እንዴት እገፋለሁ?
እናቱ እናቴ ነሽ! - ተቀብየሻለሁ!!!
+ + +
ፈጣሪን ልትወልጅው - አምላክን ልታ’ዥው
ሰማይና ምድር የማይወስኑትን - በእቅፍሽ ልትይዥው
ከድንግልና ጡት - ወተት ልታጠቢው
የዓለሙን መጋቢ...
ከደኃ ማጀትሽ - ሲራብ ልትመግቢው
እናት አባትሽን - ከእስር ልታስፈቺ
የክፋትን አባት - በፍቅር ልትረቺ
ከሀና ከኢያቄም - የተወለድሽ አንቺ
እናትና ድንግል - ንግሥትና አገልጋይ
ሰማየ ሰማያት - ጽርሐ አርያም ሆይ!
የአንቺ ግሩም ልደት - ለእኔም ነው ልደቴ
የጥምቀት መሥራቹ - ልጅሽ ነው አባቴ
ዳግም የተወለድሁ - ከውኃና መንፈስ
ባንቺ መወለድ ነው - የአዳም ተስፋው ሲደርስ
ሕይወት የሆነልን - የልጅሽ ሥጋና ደም
ከአንቺው ነው የነሳው - ከላይ አልወረደም
ዝም ማለት ያልቻልኩት - ለዚህ ነው ድፍረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እና ነሽ - ልደትሽ ልደቴ
+ + +
+
ቅድስተ ቅዱሳን - ንጽሒተ ንጹሐን
ማሕጸኑ ለጽድቅ - እናቱ ለብርሃን
ሰማየ ሰማያት - ታናሽ ብላቴና
ከእያቄም ወሀና - ተወለደሻልና
ዓለም ብርሃን አየ - ውስጥሽ ባለው ፀሐይ
አዳም ቀና አለ - ተስፋ ብርሃኑን ሊያይ
ፍጥረታት በሙሉ - ከሰማይ ከምድር
በደስታ ተመሉ - ልደትሽ ሲነገር
ተወለደሻልና - የፀሐይ እናቱ
ጽርሃሐ-አርያም ሆንሽ - ብላቴናይቱ !
+ + +
+
(፡›አበው ስለክብርሽ - ቃላት አጠራቸው
ስለ ደም ግባትሽ - ምሳሌ ጠፋቸው
እኔ ግን ደፋሩ - እዘባርቃለሁ
ባልበሰለ ብዕር - ቃላት እመርጣለሁ
በተንሸዋረረ ዓይን - ክብርሽን አያለሁ
ምልጃሽን እያሰብሁ - በተስፋ እኖራለሁ‹፡)
+ + +
የብርሃን እናቱ - የፀሐይ ምሥራቁ
የአዳም ሙሉ ተስፋ - የሰይጣን መብረቁ
ስለ አንቺ መወለድ - ዓለም ተፈጠረ
ስለ አንቺ መወለድ - የሰው ልጅ ከበረ
አዳምና ዘሩ - በኃጢአት ቢረክሱ
በአንቺ መወለድ - ግን በክብር ነገሡ
በአንቺ ልዩ ልደት - አዳም አምላክ ሆነ
በአንቺ ልዩ ልደት - ክብራችን ገነነ
በአንቺ ልዩ ልደት - ዲያብሎስ ታሰረ
በአንቺ ልዩ ልደት - ባሪያ መሆን ቀረ
እኔም ደፋር ሆንኩኝ - ፍርሃት ተሰወረ
ባዶው አዕምሮዬ - ክብርሽን ነገረ፡፡
+ + +
ሰማይና ምድር - ልደትሽን ሲያከብሩ
ሊቃውንት ሲቀኙ - መላእክት ሲዘምሩ
ክብርሽን ተማምነው - በምልጃሽ ያደሩ
በምህረት ቃል ኪዳን - ለክብር ሲጠሩ
እንደልጅነቴ ለእኔም - እንዲደርሰኝ
እንባሽን አስታውሶ - ልጅሽ እንዲምረኝ
ዝም ማለት ያልቻልኩት - ለዚህ ነው ድፍረቴ
የአንቺ መወለድ ነው - የጽድቅ መሠረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እናቴ ነሽ - ልደትሽ ልደቴ፡፡
ተጻፈ በተክለ ስላሴ
10-6-2020
BY እልመስጦአግያ+++
Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/688