tgoop.com/learn_with_John/508
Last Update:
+ ዕጣንና አለመታዘዝ +
ዕጣን መቅሠፍትን ያርቃል : ደዌን ይገሥጻል::
ሳይንሱ ሳይቀር ድብታን (depression) ያርቃል እስከማለት የደረሱ ጥናታዊ ምስክርነቶችን ይሠጥበታል::
ዕጣንን መቅሠፍት እንዲያርቅ የሚያደርገው ንጥረ ነገሩ ብቻ ሳይሆን በካህናት የሚደረገው ጸሎተ ዕጣን ነው::
በእስራኤላውያን ታሪክ የተፈጸመው ይህ ነው::
"አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው" ኦሪት ዘኍልቍ 16 :47
በዕጣን ምክንያት ብዙ ሺህ ሰው ካለቀበት መቅሠፍት እስራኤላውያን ዳኑ:: ይህ ታሪክ ዕጣን መቅሠፍት እንደሚያርቅ ያሳያል::
በተያያዘ ዜና :-
የብዙ ሰው ሞት ምክንያት የነበረው መቅሠፍት ግን መነሻው ምን ነበር? ስንል የሚከተሉት ነጥቦችን ማስተዋል ይገባናል::
1ኛ የመቅሠፍቱ ዋነኛ መነሻ ቆሬ ዳታንና አቤሮን የተባሉ ሰዎች ለሌዋውያኑ ካህናት ለሙሴና ለአሮን ትእዛዝ አንገዛም ማለታቸውና ክህነትን በማቃለላቸው ነበር
2ኛ ካህን ከመናቅ አልፈው እኛ ከማን እናንሳለን ብለው ያለ ሥልጣናቸው እሳት አንድደው ዕጣን ለማጠን በመሞከራቸው የተነሣ መቅሠፍት ነበር
3ኛ መቅሠፍቱ ከመነሣቱ በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ መቅሠፍቱ እንዳይነካችሁ ፈቀቅ በሉ ብሎ ነበር:: ከዚያ መቅሠፍት ከዳኑት መካከል የሚበዙት ይህን ትእዛዝ ከሙሴ አፍ ሲሰሙ አክብረው መሸሽ የቻሉ ሰዎች ብቻ ነበሩ:: አልሰማ ያሉና ከኑግ ጋር የተገኙ ሰሊጦች ግን አብረው ተወቅጠዋል::
የአሮንን ክህነት የናቁት ግን ዕጣኑን ራሳቸው ይዘው ቢያጥኑም መቅሠፍቱ የጀመረው ከእነርሱና ከቤተሰባቸው ነበር:: ይህ እንግዲህ ቃል በቃል የተጻፈው ነው::
አባቶቻችንን እንስማ! በእኛ ቸልታ ምክንያትም ብዙ ሊቃውንትዋ አረጋውያን የሆኑላትን ቤተ ክርስቲያን አንጉዳት:: ታምመህ ከምትሰቃይና ለሌሎችም ሥቃይ ምክንያት ከምትሆን "ሳትታመም ዳን" "ተፈወስ እምቅድመ ትሕምም":: ተጠንቅቆ ከቤቱ የሚውለውን ሰው አንተ ወጥተህ በሽታ ሸምተህለት ማምጣትህ አያሳዝንም?
"አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል!" መክ 2:16
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መጋቢት ቂርቆስ 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
BY እልመስጦአግያ+++
Share with your friend now:
tgoop.com/learn_with_John/508