tgoop.com/kegedlatandebet/1130
Last Update:
ረድኤት በረከቱ ይደርብንና በዚኽች ዕለት ጥር 15 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓሉ ታስቦ የሚውለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ በዐፀደ ነፍስ ተገልጦ ለንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ ያደረገለት ታላቅ ተአምር ይኽ ነው፡- ‹‹በቅድስት ሀገር በሮሐ ከአምላኩ ዘንድ የክህነትን ሥልጣን የተቀበለ የዓለምን ተድላ ደስታ ንቆ መንግሥቱን ከተወ በኋላ በገዳም ሲኖር ለ40 ዓመት ያህል በበዓላትና በየሰንበቱ ከሰማይ ኅብስትና ወይን የወረደለት አንድ ጻድቅና ካህን ነበር፡፡ የጽድቁም ምልክት እስካሁን ክቡር ሥጋው ካረፈበት ሥፍራ አለ፡፡ በመንግሥቱ ሳለ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንፈስ ቅዱስ ባመለከተው ቦታ በባሕር ላይ ቤተ ክርስቲያን ሊያንጽ ተነሣ፡፡ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስን የቤተ ክርስቲያኑን መሠረት ለማሳመር ሁሉ እያንዳንዱ ደንጊያና ሸክላ እንጨትም እንዲሸከም ትእዛዙን ይነግር ዘንድ በግዛቱ ዓዋጅ ነጋሪ አዞረ፡፡ ንጉሡም ከባሕር ዳርቻ ቆሞ አገልጋዩ በባሕሩ ላይ ለቤተክርስቲያኑ መሠረት ርብራብ ሊያደርግ ከባሕሩ ገባ፡፡ ይህንንም ሲያደርግ የባሕር ጋኔን ወጥቶ መታው፣ ፈጥኖም ሞተ፡፡ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ የሰይጣንን መተነኳኮል አይቶ አብዝቶ አዘነ፡፡ በዚህ ጋኔን ስለሞተ አገልጋዩ ስለ ቤተክርስቲያንም መታነጽ የሚያደርገውን ሲያስብ ስለጽድቅ የተጋደለ ማር ቂርቆስ ድንገት በታላቅ ክብር ተገልጦ ‹የተቀባህ ንጉሥ የከበርህም ካህን ሆይ! በአምላኬ ሥልጣን የሞተ አገልጋይህን እኔ አስነሣልሃለሁ፣ ጋኔኑንም እበቀለዋለሁ፣ አንተም ኃይል በተደረገልህ ሥፍራ በምትሠራት መቅደስ ውስጥ በስሜ የተሠየመ ታቦት ታኖራለህ› አለው፡፡
ንጉሡም ‹የክርስቶስ ሰማዕት ሆይ! እንዳልኸው አደርጋለሁ› ብለ መለሰ፡፡ ያን ጊዜም ማር ቂርቆስ እጁን ዘርግቶ የጋኔኑን የራስ ጠጉር ይዞ ከባሕር ውስጥ አወጣው፡፡ ቁመቱ ፈጽሞ ረጅም፣ ሁለንተናውም በእሳት እንዳቃጠሉት የእንጨት ግንድ ጥቁር ነበር፡፡ ከቅድስት ሀገር ከሮሐ ወደ ጎጃም ምዕራባዊ ክፍል እንደ ድንጊያ ወረወረው፣ በዚያም ሞተ፤ የሞተው የንጉሡ አገልጋይ ግን ከሞት ተነሣ፡፡ ንጉሡም ፈጽሞ ደስ ተሰኘ፡፡ አምስት ጊዜ ከሩቅ የዞጴ እንጨት እየተሸከመ ያችን መቅደስ ሠራት፡፡ ከአገልጋየቹም ጋር ሲሠራ ይውል ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም የመቅደስ ሥራዋን እያመለከተው ከእርሱ ጋር ነበረ፡፡ የመቅደስ መታነጽም ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ በከበረ ሕፃን ቂርቆስ ስም የተሠየመ ታቦት በውስጧ አኖረ፡፡ ኅብራቸው ባማረ የከበሩ ጌጦችና ልብሶችም አስጌጣት፡፡ በውስጧም በጥቅምት 19 ቀን ቀደሰ፡፡››
(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ገጽ 98-100)
ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ሆይ! በነቢዩ ኤልያስ ሠረገላ ተሰውሮ ላለ ቅዱስ ሥጋህ ሰላም እላለኹ!
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ በዚኽች ምድር ላይ በሥጋው መከራን በሚቀበልበት ወቅት ማኅበርተኞቹ የተባሉ ዓሥራ አንድ ሺህ አራት ሰዎችን በተአምራቱና በትምህርቱ አሳምኖ ለክርስቶስ መንግሥት ያበቃ ታላቅ ሐዋርያም ጭምር ነው!!! የከበረች በረከቱ ትደርብን በጸሎቱ ይማረን!
BY ከገድላት ኣንደበት ke gedlat andebet
Share with your friend now:
tgoop.com/kegedlatandebet/1130