tgoop.com/gitim_menfesawi/3015
Last Update:
አንድ ሰው መፍትሔ የሌለው የሚመስል መከራ ሊገጥመው ይችላል። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ድምፅ መከራው የገጠመው ጥቂት ኃጢአቶችን ስለ ፈጸመ መሆኑን ከማስጠንቀቂያ ጋር ይነግረዋል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቃሉ ንስሓ ከገባህ መከራው ፍጻሜ ያገኛል እያለ ውስጡን ሲመክረው ይሰማል። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ንስሓው ሲል ለሰውየው ይራራለታል።
የእግዚአብሔር ድምፅ አንድ ሰው ሲታመም ወይም እርሱ የሚወደው ሌላ ሰው ሲታመም ሊመጣ ይችላል። በዚህ ጊዜ እንዲጸልይ ወይም ስእለት እንዲሳል የሚመክረውን ድምፅ ከውስጡ ይሰማል ይህ ድምፅ የእግዚአብሔር ድምፅ ነው።
የዮሴፍ ወድሞች እህል ሊገዙ ወደ ግብጽ ከወረዱ በኋላ በዚያ ችግር ሲገጥማቸው እርስ በእርሳቸው እንዲህ በማለት ተነጋግረው ነበር፦ "በእውነት ወድማችንን በድለናል እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውና ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን።"/ዘፍ 42፥21/ ከዚህ በኋላ ለዮሴፍ እንዲህ ብለውታል፦ "ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ"/ዘፍ 44፥16/ ኃጢአታቸውን እንዲያስታውሱ ኋላም እንዲገሰጹ ያደረጋቸው የእግዚአብሔር ድምፅ ነው።
ነቢዩ ዳዊት የጌራ ልጅ በሆነው በሳሚ ሲሰደብ የእግዚአብሔር ድምፅ ውስጡ ስላለፈ ኃጢአቱ እየወቀሰው መሆኑን አዳምጧል። ስለሆነም በዙሪያው ለነበሩ ሰዎች "እግዚአብሔር ዳዊትን ስደበው ብሎታልና ይርገመኝ።" /2ኛ ሳሙ.16፥10/ በማለት በግልጽ ተናግሯል።
ረሀብና የመሬት መንቀጥቀጥ በዓለም ሲደርስ የእግዚአብሔር ድምፅ በመላው ዓለም ውስጥ ይሰማል። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ድምፅ የሚናገረን "ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።" /ሚል 3፥7/ እያለ ነው። ይህ ድምፅ በረሀቡ ወይም በመሬት መንቀጥቀጡ ጉዳት ለደረሰባቸው ሀገሮች የሚሆን የእርዳታ ጥሪ ለማሰማት ወይም ሌሎቹ ከእነርሱ ትምህርት በመውሰድ ንስሓ እንዲገቡ ለማድረግ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኝት ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው።
ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ስትገቡ ከውስጣችሁ ያለውን የእግዚአብሔር ድምፅ አድምጡት እርሱ ለእናንተ ሊነግራችሁ የሚወደው ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁና።
#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
@gitim_menfesawi
BY ከራድዮን
Share with your friend now:
tgoop.com/gitim_menfesawi/3015