tgoop.com/ethzema/4687
Last Update:
#ኢዜማ_ምን_ያስፈልገዋል ?
👉 #የምርጫ_ቅስቀሳ_ሰዓት
#ኢዜማን_በልኩ !!
ኢዜማ በአማራጭ ኃይልነት ጠንካራ ቁመና ያለው ፓርቲ ሆኖ እንዲወጣ አሁን ላይ “ምን ያስፈልገዋል?” ካልን ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው የአዲሱ ትውልድ አካል የኾነ፣ ዘመኑን የሚዋጅ ቆራጥ እና ትጉህ አመራር ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን።
አሁን የኢዜማ አዲሱ ትውልድ ኃላፊነትን የሚረከብበት ጊዜ ነው። ይህ ደግሞ ላለፉት 50 ዓመት ደጋግመን በሞከርነው እና ተፈትኖ በወደቀ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ ተዘፍቆ ሊሳካ የሚችል አይደለም። አሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአዲስ መንፈስ አዲስ ትግል ይፈልጋል። አዲሱ የፖለቲካ ትግል የአዲሱ ትውልድ ኃላፊነት እና መብትም ጭምር ነው። በተለመደው መንገድ ባረጀ አስተሳሰብ ሄደን የተለየ ቦታ መድረስ ካለመቻላችንም በላይ የምንመኘውን ውጤት አናመጣም።
ይህ የኢዜማ አዲሱ ትውልድ ድምፅ ነው። ይህ ድምፅ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የተዘጋጀ፣ ፖለቲካን ተስፋ አስቆራጭ በኾነ ዝግታ አልያም በስሜት እየቸኮለም የማይጋልብ “ኢዜማን በልኩ!” ብሎ የተነሳ ቁርጠኛ አመራር ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ሀገራችን የነበረችበትን አስጊ የጸጥታ ሁኔታ እና የመበተን ስጋት በቅጡ በመረዳት ኢዜማ በእርጋታ እና በስክነት ሲሠራ እንደቆየ የሚታወቅ ነው። አሁን ላይ በሀገራችን ያሉትን ተለዋዋጭ ክስተቶች በጥልቀት በመገንዘብ እና በተለይም ሀገራዊ ምክክሩን እና 7 ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ከግምት በማስገባት በተግባር ኢዜማ በልኩ፣ በራሱ መንገድ፣ የራሱን ጉዞ ለማድረግ ተነስቷል።
ይህ ጉዞ ከኹሉም የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግን ሀቀኛ ትብብር የሚፈልግ እንደኾነ አያጠያይቅም። እኛ እንደምናስበው ኢዜማ በዚህ ሰዓት ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት እና ተልዕኮውን መሸከም እና መፈጸም የሚችል ቆራጥ ድርጅታዊ አመራር ያስፈልገዋል። ይህ አመራር የጠራ አረዳድ ያለው፣ እርስ በእርስ የማይጓተት፣ ስለ ዓለምአቀፍ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ እንዲሁም ውስጣዊ ድርጅታዊ ሁኔታዎች በቂ ግንዛቤ ያለው መኾን አለበት። ኢዜማ የጋራ ግብና ዓላማ ሰንቆ የሚሠራ፣ ኹሌም ለመማር ዝግጁ የኾነ፣ ዘመኑን የሚዋጅ እውነተኛ የአዲሱ ትውልድ አመራር ለመኾን ቆርጦ የተነሳ አመራር ያስፈልገዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም እኛ አራታችን (ሊቀመንበር፣ ም ሊቀመንበር፣ ዋና ጸሐፊ እና ፋይናንስ) ተግባብተን ለመመረጥ እየሠራን እንገኛለን።
👉 ሙሉውን ሰነድ ለማንበብ ከታች የተያያዘውን ማሥፈንጠሪያ ይጫኑ 👇
https://drive.google.com/file/d/1prqfUjj2PzXojUVGNCVYyviZ5Qb-lS6Y/view?usp=drivesdk
BY የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
Share with your friend now:
tgoop.com/ethzema/4687