tgoop.com/ethzema/4651
Last Update:
የሕግ የበላይነት ተከብሮ አባላቸን በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን!!!
የኢዜማ አባል የሆኑት ሲኒየር ፋርማሲስት ኃይለማርያም ብርሃኑ የድሪም ኬር አጠቃላይ ሆስፒታል የፉርማሲ ክፍል ኃላፊ፣ የኢዜማ የባህርዳር ከተማ የስራ አስፈፃሚ፣ በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የስራ አስፈፃሚ፣ ፓርቲውን በመወከል የ2013 ዓ.ም የክልሉ ምክርቤት እጩ ተወዳዳሪ እንዲሁም በአማራ ክልል በነበረው ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ በሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ያሉ ቆራጥ፣ ሀገር እና ወገንን ቀን ከሌት በማገልገል የሚተጉ ዜጋ ናቸው።
አባላችን ሚያዚያ 21/2017 ዓ.ም ምሽት በ2፡00 ሰዓት በፓሊሶች ከቤታቸው ተወስደው በባህርዳር ከተማ 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለምንም ክስ የታሰሩ ሲሆን ፤ በግንቦት 4 ቀን አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ተመስርቶ ግንቦት 12/2017 ዓ.ም የባህርዳር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ከነበሩበት ቦታ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደው የት እንዳሉ ማወቅ አልተቻለም፡፡
መንግስት አንድን ዜጋ ከሕግ በላይ ሆኖ አስሮ ማንገላታቱ ሳያንስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለማክበር ሲጨመርበት ተስፋ አስቆራጭ ነው! በመሆኑም የሕግ የበላይነት ተከብሮ አባላቸን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በአፅንኦት እንጠይቃለን!!!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ግንቦት 13/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
BY የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
Share with your friend now:
tgoop.com/ethzema/4651