tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/8123
Last Update:
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ንግሥት አውዶክስያ እና የሊቁ የሕይወት ፍጻሜ፦
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በጵጵስና ዘመኑ ከሚታወቅባቸው ደማቅ ሥራዎቹ አንዱ ድኃ ሲበደል ፍርድ ሲጎድል እንደ አባቶቹ እንደ ኤልያስና እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ንጉሡንና ንግሥቲቱን ያለ ፍርሀት በጥብዐት ይገሥፅ የነበረ አባት መሆኑ ነበር። በዘመኑም የንጉሡ የአርቃድዮስ ባለቤት ንግሥት አውዶክስያ የአንዲትን መበለት መሬት ሥልጣኗን ተጠቅማ ነጠቀቻት፡፡
ይህቺ መበለት መሬቷን እንድትመልስላት ደጋግማ ብትለምናትም ንግሥቲቱ እሺ ስላላለች መበለቷ ችግሯን ለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነገረችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የድኃዪቱን መሬት እንድትመልስላት ደጋግሞ ቢነግራትም ንግሥት አውዶክስያ ግን በዕንቢተኝነቷ ጸናች። በዚህ ጊዜም ሊቁ ሳይፈራና ሳያፍር ንግሥቲቱ የድኃዪቱን መሬት ካልመለሰች ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበል አወገዛት፡፡
ንግሥት አውዶክስያም በዚህ ጊዜ እጅጉን ተናዳ የቆጵሮሱን ሊቀ ጳጳስ ኤጲፋንዮስንና የእስክንድርያውን ፓትርያርክ ቴዎፍሎስን አስጠርታ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከግዝቷ እንዲፈታት እንቢ ካለ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ዘግታ አብያተ ጣዖታትን በማስከፈት የቀደመውን የስደት ዘመን መልሳ እንደምታመጣው በመንገር ከግዝቷ እንዲያስፈቷት ነገረቻቸው፡፡
እነርሱም ሄደው “ምእመናን ትንሽ ዐረፉ ስንል የቀደመውን የመከራ ዘመን መልሼ አመጣዋለሁ እያለች ነው እባክህ ከግዝቷ ፍታት።" በማለት ተማጸኑት። ሊቁ ግን “የድኃዪቱን መሬት ካልመለሰች አልፈታትም ብሎ በአቋሙ በመጽናቱ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ንግሥት አውዶክስያ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በኑፋቄያቸው ምክንያት አውግዞ የለያቸውን አርዮሳውያን ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስባ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በማይገባ ነገር አውግዞኛልና ፍረዱልኝ አለቻቸው፡፡ እነርሱም በኑፋቄያቸው ምክንያት አውግዟቸው ስለነበር ይጠሉት ነበርና ተሰዶ በግዞት እንዲኖር፣ በዚያም እንዲሞት ፈረዱበት፡፡
ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ሁከት እንዳያነሣ እርሱን በመንፈቀ ሌሊት በፈረስ በሠረገላ አድርጋ ወደ ደሴተ አጥራክያ አጋዘችው፡፡ እርሱም በዚያ በተጋዘበት ሀገር የነበሩትን ሰዎች አስተምሮ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መለሳቸው፡፡ በወቅቱ በሮም ነግሦ የነበረው ንጉሥ አኖሬዎስ እና ሊቀ ጳጳሱ ዮናክንድዮስ ይባላሉ፡፡ ንጉሡና ሊቀ ጳጳሱም የሊቁን ከመንበሩ መሰደድ ሲሰሙ የሮሙ ንጉሥ አኖሬዎስ ወደ ንጉሥ አርቃድዮስ በፍጥነት ከስደቱ መልሰው የሚል መልእክት ላከበት፡፡ ንጉሥ አርቃድዮስም ያለ ንግሥት አውዶክስያ ፈቃድ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ከስደቱ መለሰው፡፡
ነገር ግን ንግሥት አውዶክስያ ሊቁ ከግዞቱ የተመለሰው ያለ ፈቃዷ ነበርና ሌላ ምክንያት ፈልጋ እንደገና በስደት እንዲጋዝ አደረገችው፡፡ እርሱም በመንገድና በእስራት ደክሞ ስለነበር አጥራክያ እንደደረሰ ብዙ ሳይቆይ ግንቦት 12 ቀን በ407 ዓ.ም. በሰላም ዐረፈ፡፡
ከዚህም በኋላ የሮሙ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሱ ዮናክንድዮስ የሊቁን ሁለተኛ መሰደድ ሲስሙ ሊቀ ጳጳሱ ዮናክንድዮስ ከስደቱ ካልመለሽው ሥጋውን ደሙን እንዳትቀበይ ብሎ አወገዛት፡፡ እርሷም ከስደቱ ይመልሱት ዘንድ መልክተኞችን ብትልክም መልክተኞቹ በደረሱ ጊዜ ዐርፎ አገኙት፡፡ እነርሱም አስከሬኑን በድንጋይ ሳጥን ይዘው ከደሴተ አጥራክያ ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር የሊቁ ቅድስና እንዲገለጥ ፈቃዱ ነውና በንግሥቲቱ ላይ ከባድ ደዌ አመጣባት፡፡
ንግሥቲቱም የምትድን መስሏት ለብዙ ባለ መድኃኒቶች ብዙ ገንዘብ ብትከፍልም ከደዌዋ ግን ሊፈውሳት የቻለ ከቶ አልነበረም፡፡ ከብዙ ድካም በኋላም ለክፉ ሠሪ ደግ መካሪ አይታጣምና አንድ ሰው ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መቃብር ሂዳ ብትማጸን ሊቁ እንደሚያማልዳት ነገራት፡፡
እርሷም ወደ መቃብሩ በመሄድ “የአዛኙ የክርስቶስ አገልጋይ ሆይ እዘንልኝ፤ የሩኅሩኁ የእግዚአብሔር አገልጋይ ራራልኝ፤” እያለች ጸለየች፡፡ ከዚህ በኋላም በጻድቁ አማላጅነት በእግዚአብሔር ቸርነት ከደዌዋ ተፈወሰች።
ስመ ሥርጋዌሁ ለቅዱስ ዮሐንስ.....
ይቀጥላል....
BY አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር

Share with your friend now:
tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/8123
