tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7903
Last Update:
የሄሮድያዳም ልጅ የመጥምቁን ራስ ወስዳ ለእናቷ ልትሰጣት ስትል ዐይኖቹ እንደፀሐይ ሲያበሩ ብታየው "ንጉሡን አትፈራውምን?" በማለት ተቆጣች፡፡ በመቀጠልም "እነዚህን ዐይኖቹን በወስፌ እያወጣሁ እጥላቸዋለሁ፣ ምላሱንም ደግመኛ እንዳይገሥጽ ቆርጨ እጥላቸዋለሁ" በማለት ፊቱን በጥፊ ለመምታት እጇን ስታነሣ ያንጊዜ የዮሐንስ ራስ ክንፍ አውጥታ በረረች፡፡ በአየር ላይ ሳለችም ዳግመኛ "የተረገምሽ ሄሮድያዳ የባልሽን ወንድም ሄሮድስን ማግባት አይገባሽም፣ ቀድሞ የምዘልፍሽ አሁንም የምዘልፍሽ እኔ ነኝ" እያለች የዮሐንስ ራስ የቤቱን ጣሪያ ሰንጥቃ እንደንሥር በአየር በራ ሄደች፡፡
ከዚህም በኋላ ለጥፊ የዘረጋቻቸው የሄሮድያዳ እጆቿ ከትከሻዋ እየተቆረጡ መሬት ላይ ወደቁ፤ እውነቷንም መሬት አፏን ከፍታ ዋጠቻት፡፡ ዘፋኟ ልጇም አብዳ የቤተ መንግሥቱን ዕቃ ሁሉ መሰባበር ጀመረች፡፡ የንጉሡ አንዱ ጭፍራም የሄሮድያዳን በእሳት እንደተለበለበ የግንድ እሳት የመሰለና የተቆረጠ እጇን አምጥቶ ለሄድሮስ ሰጠውና የሆነውን ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገሩ እውነት መሆኑን ሄዶ ባየ ጊዜ በሀፍረት እጅግ ተሸማቀቀ፡፡ ዘፍና በማስደሰት የዮሐንስን ራስ እንዲያስቆርጠው ያደረገችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅም አብዳ በቤተ መንግሥቱ ስትለፈልፍ አገኛት፡፡ ሄሮድስም መኳንንቶቹን "በቤተ መንግሥቴ የተደረገውን ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ" ብሎ አማላቸው ነገር ግን ያበደችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅ ራሷ ሄዳ ሄሮድስን "የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት ፈጽሞ አይገባህም" እያለች በመኳንንቶቹ ፊት ገሠጸችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ቃል ከእርሷ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደና "ቀደሞ ያልሆነ ሥራ ታሠራ በኋላ ደግሞ ምሥጢር ታወጣ ንሣ በሰይፍ ቁረጣት" ብሎ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡፡ ሥጋዋንም ዓሣ አንበሪ ተቀብሎ ዋጣት፡፡ ሄሮድም የወንደሙን ሚስት ሲያገባ አስቀድሞ አግብቷት የነበረችውን ሚስቱን በግፍ አባሯት ነበር፡፡ እርሷም ይህንን ሄሮድስ ያደረሰባትን ግፍ ለአባቷ አርጣ ብትነግረው አባቷ ብዙ ጦር ሰብስቦ መጥቶ ምድረ ገሊላን በኃይል አፈራረሳት፡፡ የበላዩ ንጉሥ ቄሳርም የገሊላን መፍረስና መውድም ሲሰማ ምክንያቱን ቢጠይቅ ሄሮደስ ባደረገው ግፍ ምክንያት መሆኑን ነገሩት፡፡ ቄሳርም ሄሮድስን ከሥልጣኑ ሽሮ አጋዘውና በወህኒ ጣለው፡፡ ሄሮድስም በወህኒ ቤት ሳለ አብዶ ራሱን ስቶ የገዛ አካሉን እየነጨ እየበላ ቷ ብሎ ፈንድቶ ተልቶ ሸቶ እጅግ ክፉ አሟሟት ሞተ።
ከዚህም በኋላ #ጌታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ መለስ ብሎ እንዲህ በማለት ሥልጣን ሰጣት፡- "እነሆ መንፈስሽን በራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ በሰማይም የምትበሪበት እንደ ንሥር ክንፍ ሰጥቼሻለሁና እንደንስር በሰማይ እየበረርሽ በዓለም ሁሉ እየዞርሽ የሄሮድስንና የሄሮድያዳን ኃጢአት ግለጭባቸው፤ እስከ 15 ዓመት ድረስ ገቢረ ተአምራት የምታደርጊበት ኃይሌን መንፈሴን በእራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ" አላት፡፡ ዳግመኛም #ጌታችን ዮሐንስን "እኔም ከ3 ዓመት በኋላ ለአዳም የሰጠሁትን ተስፋ ፈጽሜ በሞቴ ወደ ሲኦል ወርጄ ነፍሳትን ከዲያብሎስ እጅ ማርኬ በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ተነሥቼ ወደ ባሕርይ ክብሬ ተመልሼ ወደ ሰማይ አርጌ ባባቴ ቀኝ በተቀመጥኩኝ ጊዜ ከ15 ዓመት በኋላ ርጉም ሄሮድስ ካስፈጃቸው ከትንንሾቹ ሕፃናት ጋራ ትሆን ዘንድ በአባቴ ፈቃድ እራስህን ተሸክመው ወደ አባትህ ወደ ዘካርያስ ያመጧት ዘንድ እኔ መላእክትን አዛቸዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ነፍስህን በእኔ ቀኝ ባባትህ በዘካርያስ አጠገብ አኑሬያታለሁ መንፈስህንም እስከ 15 ዓመት በእራስህ ውስጥ እንድትኖር አዝዣታለሁ፣ ሥጋህም ከነቢዩ ከኤልሳዕ ጋር እንዲቀመጥ አድርጌያለሁ" አለው፡፡
ከዚህም በኋላ #ጌታችን እንዳዘዛት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ እንደንስር በአየር ላይ እየበረረች የምታስተምር ሆነች፡፡ በምሥራቅ በኩል ሄዳ በዐረብ አገር ውስጥ በሰማይ ላይ ስታስተምር በዚህች ዕለት ጥቅምት 30 ቀን በግልጽ ታየች፡፡ ነጋዴዎች ድምጹዋን ሰምተውና አይተዋት እጅግ ተደስተው ገንዘባቸው ሁሉ ጥለው የቅዱስ ዮሐንስን እራስ ለመያዝ ሰውነታቸውን ብዙ አደከሙ፡፡ ነገር ግን ለመያዝ አልተቻላቸውም፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰማይ "የምትያዝበት ጊዜ ስላልደረሰ ሰውነታችሁን አታድክሙ" የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣላቸው፡፡ መፈለጋቸውንም ተው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስም እራስ 15 ዓመት ስታስተምር ኖራ ሚያዝያ 15 ቀን በዐረብ ሀገር ዐረፈች፡፡ የታዘዙ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ከቅዱስ ዮሐንስ እራስ ከተባረኩ በኋላ በታላቅ ዝማሬ እያመሰገኑ የቅዱስ ዮሐንስን አንገት ወስደው በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ቀበሯት፡፡ ቅድስትን ነፍሱንም እያመሰገኑ ወደ ሰማይ አሳረጓት፡፡ በዚያም በ #ሥሉስ_ቅዱስ ዙፋን ፊት ወድቃ ከሰገደች በኋላ አባቷ ዘካርያስንና እናቷ ኤልሳቤጥን እጅ ነሳቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በ3ኛው ሰማይ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ #ጌታችን ሦስቱን ሰማየ ሰማያት ርስት ጉልት አድርጎ ሰጥቶታልና፡፡
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_አባት_ባሕታዊ_አብርሃም
በዚህች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር በገድል የተጸመደ ቅዱስ አባት ባሕታዊ አብርሃም አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ #እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያመልኩ ናቸው በዚህም ዓለም ገንዘብ እጅግ ባለጸጎች ነበሩ።
ይህም ቅዱስ በአደገ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ሊለብስ ሽቶ በላዕላይ ግብጽ ወደሚገኝ ወደ ሀገረ አክሚም በመርከብ ተጭኖ ሔደ ወደ አባ ጳኵሚስም ደረሰ እርሱም የምንኲስና ልብስን አለበሰው በገድልም በመጸመድ ሥጋውን አደከመ በአባ ጳኵሚስም ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ሃያ ሦስት ዓመት ያህል በማገልገል ኖረ።
ከዚህም በኋላ በዋሻ ውስጥ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንዲአሰናብተው አባ ጳኵሚስን ለመነው እርሱም ፈቀደለት ዓሣ የሚያሠግሩበትን መረብ የሚሠራ ሆነ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አንድ ሰውን አመጣለት ያም ሰው መረቡን ሽጦ ምግቡን አተር ይገዛለታል የተረፈውንም ለድኆች ይሰጣል የምግቡም መጠን ሁልጊዜ ማታ ማታ አንዲት እፍኝ ከጨው ጋር በውኃ የራሰ አተር ነው።
እንዲህም እየተጋደለ በዚያች ዋሻ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ ልብሱም ከገዳም ሲወጣ የለበሰው ከዘመን ርዝመት የተነሣ አርጅቶ ተበጣጠሰ ሥጋውንም በጨርቅ የሚሸፍን ሆነ። በየሁለት ዓመትም ወደ መነኰሳቱ ገዳም በመውጣት ሥጋውንና ደሙን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ይመለስ ነበር። በዚያችም ዋሻ መኖር በጀመረባት ዓመት ሰይጣናት ወደ ርሱ በመምጣት ምትሐት እየሠሩ ተፈታተኑት እርሱ ግን ውሻን እንደሚአበር ሰው አበረራቸው።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ያን ሕዝባዊ ሰው ልኮ የአባ ጳኵሚስን ረድእ አባ ቴዎድሮስን አስጠራው በመጣም ጊዜ ሰግዶ ሰላምታ ሰጠው እንዲጸልይለትና በጸሎቱም እንዲአስበው ለመነው። ከዚህም በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ በዚያንም ጊዜ አባ አብርሃም በርከክ ብሎ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ አባ ቴዎድሮስም ወደ መነኰሳቱ ላከ እነርሱም መጥተው ከሥጋው በረከትን ተቀበሉ ሥጋውንም ወሰደው ከቅዱሳን ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት።
ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምትና_30_ሚያዝያ
#ከገድላት_አንደበት)
BY አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር
Share with your friend now:
tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7903
