tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7800
Last Update:
አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው። እነርሱም ታዛዦች ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ የኢትዮጵያ ንጉሥም መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው እሊህንም ቅዱሳን አባቶች ይቀበሏቸው ዘንድ አሽከሮቹን በቅሎዎችን አስይዞ ላከ በመጡም ጊዜ በታላቅ ደስታ ሰላምታ አቀረበላቸው ከእርሳቸውም ቡራኬን ተቀበለ ታላቅ ክብርንም አከበራቸው ። እነርሱም የሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ አንብቦ ለሊቀ ጳጳሳቱ ቃል ታዛዥ መሆኑን ገለጠላቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ስብከታቸውና ወደ ሕዝባቸው መመለስን በአሰቡ ጊዜ ስለ ቅድስናቸውና ስለ ትምህርታቸው ጣዕም ስለ ወደዳቸው የተከበረው ንጉሥ መመለስን ከለከላቸው በእርሱ ዘንድ እነርሱ እንደ #እግዚአብሔር መላእክት ሁነዋልና ፊታቸውም እንደ ፀሐይ ያበራል።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው #እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ በላዩ ደዌ ላከበት በዚያውም ደዌ በሰላም አረፈ።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከቱም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አቡነ_አላኒቆስ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ አላኒቆስ የትውልድ ቦታቸው ሸዋ አንኮበር ሲሆን አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ነው፡፡ ንጉሡ አባታቸው ‹‹አግባና መንግሥቴን ይዘህ ተቀመጥ›› ቢላቸው እርሳቸው ግን ንግሥናን በመናቅ እምቢ ብለው ሄደው ከ#እመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው ቢለምኗት #እመቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹ክፍልህ ምናኔ ነው፣ የአባትህ መንግሥት ያልፋል የልጄ መንግሥት ግን ዘላለማዊ ነው›› አለቻቸው፡፡ ጻድቁም ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሄደው በዚያው መንኩሰው ገዳሙን እያገለገሉ ተቀመጡ፡፡ ከጸሎታቸው በኋላ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበርና አንድ ቀን እንዲሁ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ መላእክት አውጥተዋቸዋል፡፡ አቡነ አላኒቆስ ወደ አክሱም እንዲሄዱ ታዘው ከሄዱ በኋላ በዚያም የጽላተ ሙሴ የታቦተ ጽዮን አጣኝ ሆነው 40 ዓመት ተቀምጠዋል፡፡ #እመቤታችንም ተገልጣላቸው በዓታቸውን እንዲያጸኑ ከነገረቻቸው በኋላ ከአክሱም ወጣ ብሎ የሚገኘውን ማይበራዝዮ ገዳምን መሠረቱ፡፡ በዚያም እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እያስተማሩ አገልግለዋል፡፡
አንድ ቀን መኰንኑ ወደ ሩቅ ቦታ ሲሄድ ቤተሰባቸውን ለ #ንስሓ አባታቸው አደራ ሰጥተው ሄዱ፡፡ የ #ንስሓ አባታቸውም የአቡነ አላኒቆስ ጓደኛ ነበሩ፡፡ መኰንኑም ከሄዱበት ሲመለሱ ሚስታቸው ከአሽከሯ አርግዛ ጠበቀቻቸው፡፡ ‹‹ከማን አረገዝሽ?›› ብለው ጽኑ ግርፋት ቢገርፏት ዋሽታ ‹‹ያረገዝኩት ከንስሓ አባቴ ነው›› አለች፡፡ መኰንኑም መነኩሴውን እገላለሁ ብሎ ሲነሣ መነኩሴውም ወደ አቡነ አላኒቆስ ሄደው አለቀሱ፡፡ አቡነ አላኒቆስም የመኰንኑን ሚስት ቢጠይቋት ባሏን ፈርታ ‹‹አዎ ከመነኩሴው አባት ነው ያረገዝኩት›› አለች፡፡ እሳቸውም ‹‹የተረገዘው ከዚህ መነኩሴ ከሆነ በሰላም ይወለድ፣ ካልሆነ ግን አይወለድ›› ብለው በቃላቸው አስረውና ገዝተው ሸኟቸው፡፡
በግዝታቸው መሠረት ሴቲቱ ድፍን 22 ዓመት ሙሉ ሳትወልድ በጭንቅና በጣር ኖረች፡፡ በአልጋ ላይ ሆና ተጨንቃ ስትኖር በመጨረሻ ለቤተሰቦቿ ተናግራ ወደ አቡነ አላኒቆስ ዘንድ በቃሬዛ ወሰዷትና ይቅርታ ጠይቃ እውነቱን ተናገረች፡፡ እሳቸውም ‹‹#እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ቢሏት 22 ዓመት ሙሉ ተረግዞ የነበረው ልጅ ትልቅ ሰው ሆኖ ጥርስ አውጥቶ፣ ፂም አብቅሎ በሰላም ተወለደ፡፡ እርሱም ከተወለደ በኋላ አባቱ ማን እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጻድቁ አባታችንም ልጁን አሳድገውት አስተምረው አመንኩሰውታል፡፡ ስሙንም ተወልደ መድኅን አሉት፡፡ በስሙ የተሠሰራ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ጽንብላ ወረዳ ይገኛል፡፡
ጻድቁ አቡነ አላኒቆስ ሌላም የሚታወቁበት አንድ ግብር አላቸው፡፡ የማይበራዝዮ ገዳማቸው አገልጋይ የሆነው መነኩሴ በሬ ጠምዶ ሲያርሱ አንበሳ ከጫካው ወጥቶ አንዱን በሬ በላው፡፡ መነኩሴውም መጥተው ለአቡነ አላኒቆስ ነገሯቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ጸሎቴን እስክጨርስ ድረስ ወደ ጫካው ሂድና አንበሳውን ‹አላኒቆስ ባለህበት ጠብቀኝ እንዳትንቀሳቀስ ብሎሃል› ብለህ ተናገር›› ብለው ለመነኩሴው ነገሯቸው፡፡
መነኩሴውም እንደታዘዙት ወደ ጫካው ሄደው ጮኸው በሉ የተባሉትን ተናገሩ፡፡ አቡነ አላኒቆስም ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ወደ ጫካው ሄደው አንበሳውን የበላውን በሬ አስተፍተውት በሬውን ነፍስ ዘርተውበት ከሞት አስነሥተው ዕለቱን እንዲታረስ አድርገውታል፡፡ አንበሳውንም ገዝተው ወደ ገዳማቸው ወስደው ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱት እንዲያገለግላቸው አድርገውታል፡፡
አቡነ አላኒቆስ አንበሳውን አስረው ያሳድሩበት የነበረው ዛፍና ውኃ ያጠጡበት የነበረው ትልቅ የድንጋይ ገበታ ዛሬም ድረስ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ከ22 ዓመት እርግዝና በኋላ ሴቲቱ ጥርስና ፂም ያለው ልጅ እንድትወልድ ያደረጉበት ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይም ከነቅርጹ በገዳሙ በግልጽ ይታያል፡፡ ጻድቁ ጥቅምት 21 ቀን ዐርፈው በዚያው በማይባራዝዮ ገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡ ጸበላቸው እጅግ ልዩ ነው፣ ያላመነውን ሰው አስፈንጥሮና ገፍትሮ ይጥለዋል እንጂ አያስቀርበውም፡፡
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_21 እና #ከገድላት_አንደበት)
BY አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር
Share with your friend now:
tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7800
