tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7666
Last Update:
አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ስብከተ ወንጌልን በመላ ሀገራችን በማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የሐዋርያት አምሳል›› ተብለዋል፡፡ የገዳሙ አበምኔት ሲያርፉ መነኮሳቱ በፈቃደ #እግዚአብሔር አቡነ መዝገበ #ሥላሴን ይዘው በግድ አበምኔትነት ሾሟቸው፡፡ እሳቸውም ከተሾሙ በኋላ በመላ ሀገራችን ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል፣ ሙታንን አንሥተዋል፡፡ በዓታቸውንም በማጽናት በጸሎት ተወስነው የዐይኖቻቸው ቅንድቦች እስኪላጡ ድረስ ጉንጮቻቸውም እስኪቀሉ ድረስ በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ 40 ቀንና 40 ሌሊትም ይጾማሉ፡፡ ስግደታቸውም በቀንና በሌሊት ያለ እረፍት እንደመንኮራኩር ፈጣን ሆነ፡፡ ወዛቸውና ዕንባቸው አንድ ላይ ተቀላቅሎ እንደጅረት እስኪፈስ ድረስ በጭንቅ ተጋድሎ እንደኖሩ ገድላቸው ይናገራል፡፡ #እመቤታችንም ብዙ ጊዜ እየተገለጠችላቸው ከህመማቸው እየፈወሰች ታበረታቸው ነበር፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ራእይ ተመለከቱ፡፡ እነሆም ውበታቸው የሚያስገርም፣ መልካቸውም የሚያስደንቅ፣ የምስጋና ነፀብራቅ የከበባቸው፣ የራሳቸው ፀጉር ነጭ የሆነ ሦስት ወፎችን ተመለከቱ፡፡ አባታችንም አንድ ጊዜ ሦስት ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሲሆኑ ተመልክተው ፈጽሞ አደነቁ፡፡ እንዲህ እያደነቁ ሳለ #እግዚአብሔር በቃሉ ጠርቶ ካነጋገራቸው በኋላ ብዙ ምሥጢራትን ነገራቸው፡፡ ለመረጣቸው ቅዱሳን እንዲህ መገለጥ ለ #እግዚአብሔር ልማዱ ነውና ለአባታችን ለአዳም፣ ለሄኖክ፣ ለኖኅ፣ ለአብርሃም በልዩ ልዩ ህብር ተገልጧል፡፡ ኦ.ዘፍ 3፡10፣ 5፡24፣ 6፡13፣ 18፡1 ፡፡ ለሕዝቅኤልም በኮበር ወንዝ፣ ለዳንኤል በሱሳ ግንብ፣ ለኢሳይያስ ሱራፌል እያመሰገኑት ተገልጦላቸዋል፡፡ ሕዝ 1፡1፣ ዳን 8፡1-3፣ ኢሳ 6፡1-3፡፡
አቡነ መዝገበ #ሥላሴ በዘመን ደረጃ በኋለኛው ዘመን የተነሡ አባት ይሁኑ እንጂ በሰጡት ሐዋርያዊ አገልግሎትና ገንዘብ ባደረጉት የተጋድሎ ጽናት የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያትን መስለዋቸዋል፡፡ የታዘዘ መልአክ ወደ መንግሥተ ሰማያት ነጥቆ ወስዶ ማደሪያቸውን አሳይቷቸው መልሶ ወደ ምድር ካመጣቸው በኋላ የዕረፍታቸው ጊዜ እንደደረሰ ነገራቸው፡፡ ‹‹በሰኔ ወር ታርፋለህ›› ቢላቸው ‹‹በሰኔማ ልጆቼ ተዝካሬን ማድረግ አይችሉም›› አሉት፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ዕረፍትህ በሐምሌ ይሁን›› ቢላቸው ጻድቁ አሁንም ‹‹አይሆንም›› ብለው ተከራከሩ፡፡ በነሐሴም እንደዚያው ሆነ፡፡ መልአኩም መስከረምን አሳልፎ በጥቅምት እንደሚያርፉ ነግሯቸው ዐረገ፡፡ ከዚህም በኋላ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና #ጌታችን ቅድስት እናቱን፣ መላእክትን፣ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ‹‹አንተ የዓሥራ አንደኛው ሰዓት ቅጥረኛ ወዳጄ ሆይ! (ከቅዱሳን ሁሉ በኋላ የተነሣህ-ማቴ 20፡1-5) የምስራች እነግርህ ዘንድ የድካምህም ዋጋ እሰጥህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ እነሆ ከጠዋት ጀምሮ ከደከሙት ጋር አንድ አድርጌሃለሁ፡፡ ከአንተም ጋር ቃልኪዳን ገብቻለሁ፣ ስምህን በእምነት የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህም የታመነ እስከ ሰማንያ ሺህ ስድስት መቶ (80,600) ነፍሳት ዓሥራት ይሁኑህ…›› በማለት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡ በዚያን ጊዜም አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ፊታቸው እንደፀሐይ አበራና ጥቅምት 9 ቀን ከሌሊቱ በ6 ሰዓት እንደመልካም እንቅልፍ ዐረፉ፡፡ መላ ዘመናቸው 115 ሲሆን የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት #ማርያም ገዳም አበምኔት ሆነው ከመሾማቸው በፊት 62 ዓመት፣ ከተሾሙበት ጊዜ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ 53 ዓመት ነው፡፡ መካነ መቃብራቸው እዚያው የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት #ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡
በጉንዳጉንዶና አዲግራት በሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ በስማቸው የፈለቁ ብዙ ፈዋሽ ጠበሎች አሉ፡፡ አዲግራት የሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ ያለው ጠበል የትኛውንም በሽታ በአስቸኳይ ፈውስ በመስጠት ይታወቃል፡፡ ተጠማቂው ሰው የማይድንም ከሆነ ቶሎ ይሞታል እንጂ ከ7 ቀን በላይ አይቆይም፡፡ ጻድቁ ብዙ የተጋደሉበት ይህ ገዳም በግራኝ አህመድ ዘመን 44 ጽላቶች ተሰውረውበታል፡፡ ዮዲት ጉዲትም ልታገኘው ያልቻለችው ታላቅ ገዳም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከሃዲያን አሕዛብ ጦረኞች ወደ ገዳሙ ሲወጡ በተአምራት ወደ ፅድ ዛፍነት ተለውጠዋል፡፡ ፅዶቹ አሁንም ድረስ በገዳሙ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ፅዶቹን በእሳት አቃጥለው ከሰል ቢያደርጓቸው ደም ሆነው ይፈሳሉ እንጂ ፈጽሞ ከሰል መሆን አይችሉም።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_9 #ከገድላት_አንደበት)
BY አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር
Share with your friend now:
tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7666
