tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7664
Last Update:
አባ እልመፍርያንም አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱንም ተመልክቶ ጳጳስዋ ለሞተባት ለአንዲት አገር ጵጵስና ሊሾመው ወደደ። ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም በእሑድ ቀን ሰበሰባቸው አባ አትናስዮስንም አቅርበው እንዲህ አሉት ለዕገሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ልትሆን ዛሬ #መንፈስ_ቅዱስ ጠርቶሃል አሉት። እርሱም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተዉትም አልቅሶ አማላቸው እንደማይተውትም በአወቀ ጊዜ እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስ እንደሆነ ነገራቸው የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጸላቸው።
በዚያን ጊዜ አባ አልመፍርያን ደነገጠ አክሊሉንም ከራሱ ላይ አውልቆ በምድር ላይ ወደቀ ለረጅም ጊዜ እንደ ሞተ ሆነ በተነሣም ጊዜ እንዲህ ብሎ ጮኸ ወንድሞቼ የማደርገውን እስቲ ንገሩኝ ዛሬ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥለኝ ምድርም አፍዋን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና ጌታዬ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስ ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደ ባርያ ሊአገለግል አግባብ ነውን ወዮልኝ ወዮልኝ።
ጳጳሳቱና የተሰበሰቡት ሁሉ በሰሙ ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቀው ሰገዱለት እጆቹንና እግሮቹንም ሳሙ ሊቀ ጳጳሱም ያማሩ የክህነት ልብሶችን ያለብሱት ዘንድ መስቀሎችንና አርዌ ብርቱን ያመጡ ዘንድ በመንበር ላይም ያስቀመጡት ዘንድ አዘዘ።
ከዚያም በኋላ ጳጳሳቱ ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት ሦስት ጊዜ አክዮስ አክዮስ አክዮስ እያሉ ይህም ይገባዋል ማለት ነው ቤተ ክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት ።
ከዚህም በኋላ መቀደሻ ልብስ ለብሶ መሥዋዕቱን አክብሮ ቀድሶ አቈረባቸው እነርሱንም ሀገራቸውንም ባረከ ለዚያችም አገር ምንኛ መጠን የሌለው ደስታ ሆነ ተባለ ።
በማግሥቱም አባ እልመፍርያን ተነሥቶ በቅሎ አስመጣ ለጒዞ የሚያሻውን ሁሉ አዘጋጀ አባ አትናስዮስንም በበቅሎ አስቀምጦ እርሱ በእግሩ ተከተለው ጳጳሳቱና ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉም ከአባ እልመፍርያን ጋር አጅበዉ ወደ አንጾኪያ አገር ወሰዱት አባት አትናስዮስም አባ እልመፍርያንን አንተም በበቅሎ ላይ ተቀመጥና በአንድነት እንሒድ አለው። አባ እልመፍርያንም ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም አንተ በእግርህ ወደ አገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ አገርህ አደርስሃለሁ አለው።
የአንጾኪያ አገር ጳጳሳትም የሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝብ ሁሉ ጋር ሊቀበሉት ወጡ በታላቅም ክብር ተቀብለው ወደሹመቱ መንበር አስገቡት። ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስቀመጡት በዚያችም ቀን ፈጽሞ ደስ አላቸው ተሰናብተውትም ወደ ሀገራቸው በፍቅር አንድነት ተመለሱ። ይህም አባት አትናስዮስ በጎ አኗኗርን ኖረ መንጋውንም በትክክል በእውነት ጠበቀ በጎ ጒዞውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ ።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ አትናቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_እስጢፋኖስ_ካልዕ
በዚችም ቀን በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በአንጾኪያ አገር የሰማዕታት መጀመሪያ ሁኖ ሌላው እስጢፋኖስ በሰማዕትነት አረፈ ።
ይህም የፋሲለደስ ወንድም ለሆነ የኒቆምዮስ ልጅ ነው በወገንም የከበረ ነው አባቱም ከአንጾኪያ ታላላቆች ወገን ሁኖ በወርቅ በብር በወንድ ባሮች በሴት ባሮች እጅግ የበለጸገ ነው ክብር ይግባውና #ክርስቶስንም እጅግ ይፈራዋል ይወደዋልም ለድኆችና ለችግረኞች አብዝቶ ይመጸውታል በሰው ሁሉ ዘንድ ተወዳጅ ነው ።
ይህንንም ቅዱስ እስጢፋኖስን በወለዱት ጊዜ በበጎ ተግሣጽ በምክር አሳደጉት በጀመሪያም የዳዊትን መዝሙር ከዚያም የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን የ #መንፈስ_ቅዱስ ዕውቀት በላዩ እስቲመላ ድረስ አስተማሩት ።
ሁለተኛም ሥጋዊ ጥበብ ፈረስ መጋለብን ጦር መወርወርን በፍላፃ መንደፍን በቅዱስ ፋሲለደስ ቤት ሁኖ ከቅዱሳን ፊቅጦርና ገላውዴዎስ ጋር ተማረ ለፋሲለደስ የወንድሙ ልጅ ነውና ስለዚህም የፋሲለደስ ልጅ ይባላል ።
ዘመዶቹም ሁሉ #እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው በሕጉ በትእዛዙ በአምልኮቱ ሁሉ የጸኑ ናቸው ። ከውስጣቸውም ክብር ይግባውና ከ #ክርስቶስ የፍቅር ትኲሳት ልቡን የሚያቀዘቅዝ ወደ ቀኝ ቢሆን ወደ ግራም ፈቀቅ የሚል የለም ።
#ጌታችንም ለእርሱ ያላቸውን የፍቅራቸውን ጽናት በአየ ጊዜ ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀላቸውን መንግሥቱን ሊአወርሳቸው ወደደ ። ከዚህም በኋላ የግብጽ አገር ወደ ሆነ የፍየል ጠባቂ በጦርነት ምክንያት ወደ መለመሉት ስሙ አግሪጳዳ ወደ ሚባል ሰው ሰይጣን መጥቶ አደረበት ወደ አንጾኪያም በደረሰ ጊዜ የመንግሥት ፈረሶች ባልደራስ አደረጉት ።
የአንጾኪያም ንጉሥ በሞተ ጊዜ መንበሩ ከንጉሥ ተራቆተ በአንዲት ዕለትም የንጉሡ ሴት ልጅ በቤቷ ደርብ ስትመላለስ ሲዘፍን አየችው እርሱም ለፈረሶች ክራርና መሰንቆ ሲመታላቸው እንደሚዘፍን ሰው ሁነው ያሽካኩ ነበር ። ስለዚህ ወደደችውና ባል አድርጋ አነገሠችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰየመችው ።
ያን ጊዜ በዘመኑ ለተደረገ ዓመፅና ግፍ ወዮ ምን ዓይነት ዓመፅና ግፍ ነው ። ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ከካደው በኋላ ጣዖታትን አመለከ በ #ክርስቶስም ያመነውን ሁሉ ገደለ እንደ ነጣቂዎች አራዊትም የሰውን ሥጋ የሚበላ ደማቸውንም የሚጠጣ ሆነ ። የተመረጡ የመንግሥት ልጆችን ሁሉ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች በተናቸው ከእነርሱ ውስጥ በችንካሮች ቸንክሮ የገደላቸው አሉ በማረጃ አርዶ የገደላቸው በጦር ወግቶ በእሳትም አቃጥሎ የገደላቸው አሉ አሥሮ አፋቸውንም በልጓም ለጉሞ ወደ ግብጽ አገሮች እስከ ሰደዳቸው ድረስ ልቅሶና ዋይታም በአንጾኪያ አገር እስከመላ ድረስም ባል ስለ ሚስቱ ሚስትም ስለ ባልዋ እናትና አባት ስለ ልጆቻቸው ልጆችም ስለ ወላጆቻቸው ሰዎችም ሁሉ ስለ ወገኖቻቸው የቅዱሳን ሰማዕታትም ሥጋቸው በሀገሩ ጥጋጥግ የወደቀ ሆነ ። ለጠባቂዎች ገንዘብ ሰጥተው በሥውር ወስደው ከሚቀብሩአቸው በቀር ቀባሪ የላቸውም ።
ይህም ቅዱስ እስጢፋኖስ የምስክርነት አክሊልን ይሰጠው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ሲጸልይ ኖረ ።
የመጀመሪያዪቱ ቀን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በግዛቱ ውስጥ ላሉ አገሮች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ የጣዖት ቤቶች እንዲከፈቱና እንዲአመልኳቸው እነርሱ በጦርነት ውስጥ ድል አድራጊነትን ይሰጡናልና ይህንንም ትእዛዝ የሚቃወምና እምቢ የሚል ቢኖር ንብረቱ ይወረስ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ይሠቃይ ርኅራኄ በሌለው አሟሟት እስኪሞት ብሎ የሚያዝ የአዋጅ ደብዳቤ ጻፈ ።
የመንግሥቱን ታላላቆች ሁሉ ሕዝቡንም ታላቁንም ታናሹንም ሰበሰባቸው ። ይቺ የረከሰች ደብዳቤም በተሰበሰቡት ፊት ትነበብ ዘንድ አዘዘ ቅዱስ እስጢፋኖስም በሰማ ጊዜ ስለ ቀናች ሃይማኖት በ #ክርስቶስ ፍቅር እሳትነት ልቡ ነደደ ።
ዲዮቅልጥያኖስንም ተመለከተው እንደ ኢምንትም አደረገው። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ አጵሎንን ያመልኩ ዘንድ የምታዝ ይቺን የረከሰች ደብዳቤ በመጻፍህ የምታሳየው ይህ ዓመፅ ምንድን ነው ይህንንም ሁሉ ያጠፋው ዘንድ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አለ ይህንንም ብሎ ይችን የረከሰች ጽሑፍ በያዘ ወታደር ላይ ተወርውሮ ነጠቀውና ቀደዳት በጣጥሶም ጣላት ።
BY አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር
Share with your friend now:
tgoop.com/amennnnnnnnnnnnnnnnnnnn/7664
