tgoop.com/TIMRAN/3219
Last Update:
ትምራን 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን አከበረች
ሴቶች ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ እና አመራርነት እንዲመጡ የማስቻል ራእይ ሰንቃ በመጋቢት 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ያገኘችው ትምራን 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን በሳፋየር አዲስ ሆቴል ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም አከበረች።
በክብረ በዓሉ ላይ የትምራን መሥራቾች፣ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ ለጋሾች፣ ባለድርሻ አካላት፣ ጥሪ የደረገላቸው እንግዶች እና ባለሞያዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምራን ቦርድ ሰብሳቢ መስከረም ገስጥ፣ እንኳን አደረሳችኹ ያሉ ሲኾን ትምራን ቁጭት እና ቁርጠኝነት የወለዳት ድርጅት ነች ብለዋል። ይኽም ሴቶች የሚገባቸውን የፖለቲካ መድረክ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ አለማግኘታቸው እና ወጥነት ባለው እና በተቀናጀ መልኩ ዕለት ከዕለት የሚሠራ አካል ባለመኖሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የትምራን ምሥረታ ሐሳብን በማመንጨት ረገድ በዋናነት በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ በርካታ ተዋናዮች መኖራቸውንም አመልክተዋል። ቁርጠኝነቱ ይኽንን ትግል ሀገራዊ አድርጎ ለመንቀሳቀስ መደራጀት አስፈላጊ መኾኑ ነው ብለዋል። ትምራን ዕድሜዋ ትንሽ ቢኾንም ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጀምሮ እስከ ሀገራዊ ምክክር ድረስ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ ኬር ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ትምራን በአምስት ዓመታት ውስጥ ባከናወነቻቸው ተግባራት ያሳደረችው በጎ ተፅዕኖ ጥናት ቀርቧል። የዚኽ ጥናት ውጤት በቀጣይ ስልታዊ እቅዷን ለመከለስ እገዛ ማድረጉ ተገልጿል።
ትምራን አቅም ግንባታ እና ቅስቀሳ፣ ጥናት፣ ምርምር እና ኅትመት፣ ውትወታ፣ ትስስር እና አጋርነት እንዲሁም ድጋፍ እና ከለላ የሚሉ አምስት ምሰሶዎችን ይዛ ትንቀሳቀሳለች። #TIMRAN@5
BY TIMRAN (ትምራን)
Share with your friend now:
tgoop.com/TIMRAN/3219