Telegram Web
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ አርሳኒ +"+

=>ቅድስት ሃይማኖት እዚህ ዛሬ እኛ ጋር የደረሰችው
በበርካታ ሰማዕታትና ጻድቃን ደም ነው:: ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን
ግድግዳዎቿ እንጨትና ድንጋይ እንዳይመስሏችሁ:: አጽመ
ቅዱሳን ነው እንጂ::

+ቅዱሳን ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስን እንደ እኔ እና እንደ
ዘመኑ ትውልድ በከንፈራቸው የሚሸነግሉ አልነበሩም::
እነርሱ
በፍጹም ልባቸው ስለ ፍቅሩ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ
እንጂ:: በቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ቀደምት ቅዱሳን
አንዱ ደግም
ቅዱስ አርሳንዮስ ነው::

+ቅዱሱ የተወለደው በ345 ዓ/ም ሮም ውስጥ ነው::
በወጣትነቱ ይሕ ቀረህ የማይሉት የጥበብና የፍልስፍና
ሰው ነበር::
በተለይ በትልቁ የሮም ቄሳር ቴዎዶስዮስ ዘመን በቤተ
መንግስት አካባቢ የተከበረና የንጉሡ ልጆች መምሕር
ነበር::
አኖሬዎስና አርቃዴዎስን ቀጥቶ ያሳደጋቸውም እርሱ ነበር::

+በድንግልና እስከ 40 ዓመቱ ድረስ ሮም ውስጥ ቆየ::
ከዚህ በኋላ ግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ሲያስብ መልዐኩ
በሕልም ወደ
ግብፅ ሒድ አለው:: በመጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ቀጥሎ
ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ መነኮሰ:: በቆይታ ግን
ብሕትውና ምርጫው
ሆነ::

+ቅዱስ አርሳኒ በእነዚሕ ነገሮቹ ይታወቃል:-

1.በምንም ምክንያት ከማንም ጋር አያወራም:: (ለ60
ዓመታት በአርምሞ ኑሯል)

2.በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ተጠግቶ እንባውን ሲያፈስ
የርሱን አካል አርሶ በመሬት ላይ ሲፈስ ይታይ ነበር::
ከእንባው ብዛት
ቅንድቦቹ ተላልጠው አልቀው ነበር::

3.በርካታ ድርሳናትን ደርሷል:: ብዙዎቹ ዛሬም ግብጽ
ውስጥ አሉ::

4.ሸንጎበቱን ወደ ደረቱ አዘንብሎ ስለሚቆም ማንንም ቀና
ብሎ አያይም ነበር::

5.ለጸሎት አመሻሽ 11:00 አካባቢ ላይ ይቆምና ጸሎቱን
የሚጨርስ ፀሐይ ግንባሩን ስትመታው ነው::

6.ሁል ጊዜ ራሱን "አንተ ሰነፍ (ሐካይ) እያለ ይገስጽ
ነበር::

7.በገዳማውያን ታሪክ የርሱን ያሕል በቁመቱ ረዥም
አልተገኘም ይባላል:: የራሱ ጸጉር በጀርባው የወረደ ሲሆን
ጽሕሙን
በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ነጭና እስከ መታጠቂያው
የወረደ ነበር::

+እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው::

+ቅዱስ አርሳንዮስ አካሉ በተጋድሎ ደቆ: ለ60 ዓመታት
በግሩም መንፈሳዊነት ኑሮ በ100 ዓመቱ በዚሕች ዕለት
ዐርፏል::

❖አምላካችን እግዚአብሔር ከታላቁ የቅድስና ሰው አርሳኒ
በረከት አይለየን::

=>ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አርሳንዮስ - አርሳኒ (ጠቢብ ገዳማዊ)

ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5.13ቱ ግኁሳን አባቶች
6.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል:: ደግሞ
ተገርቷል:: ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው
አይችልም:: የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት
ነው:: በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን:: በእርሱም እንደ
እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን::
ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ:: ወንድሞቼ ሆይ
ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም:: (ያዕ. 3:7-11)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኩዋን የመነኮሳት አባት ለተባለው "ቅዱስ ዻኩሚስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱስ ዻኩሚስ (አባ ባኹም) "*+

=>ዛሬን አያድርገውና ምንኩስና ማለት መላእክትን መስሎ የሚኖርበት ሕይወት ነበር:: ምንኩስና በእግዚአብሔር ፈቃድ በአባ እንጦንስ ቢመሠረትም ሕይወቱን በማስፋፋት ደረጃ የቅዱስ ዻኩሚስን ያሕል የደከመና የተሳካለት ግን የለም::

+ቅዱሱ በትውልዱ ግብፃዊ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ከቀደመ ሕይወቱ ጋር በተያያዘ የሚተረክ ነገር በመጽሐፈ ገድሉ ላይ አለ:: ዻኩሚስ ወደ ምንኩስናው ዓለም የመጣ በታላቁ አባ ዸላሞን አማካኝነት ነው:: ለተወሰነ ጊዜም መንፈሳዊ አባቱን እየረዳ ሕይወተ መነኮሳትን አጥንቷል::

+በመንፈሳዊ ሕይወቱና በተጋድሎ እየበረታና እየደረጀ ሲሔድ ከአባ ዸላሞን ተለይቶ : ማሕበር መስርቶ ለመኖር አምላኩን ጠይቆ ፈቃድ በማግኘቱ በሕግ የሚመራ የመጀመሪያውን ገዳም መሥርቷል::

+ቅዱስ ዻኩሚስ ጸሎቱ አጋንንትን ከአካባቢው አያስቀርባቸውም ነበር:: አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ ጾሟል:: ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር ይሰግዳል:: እንባውና ላበቱ ከፊቱ እየወረደ አካባቢው ጭቃ ይሆን ነበር:: ጌታችንም መስቀል ተሸክሞ ይታየው ነበር::

+ስለ ክብሩም መላእክት ወደ ሰማይ ወስደው ገነትና ሲዖልን አሳይተውታል:: አባታችን ቅዱስ ዻኩሚስ ከርሕራሔው የተነሳ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲያገኝ በቀጥታ ከመፈወስ ይልቅ ደዌውን : ርኩሳን መናፍስቱንም ወደ እርሱ እንዲገለበጡ ያዛቸው ነበር::

+ከዚያም በጾም : በጸሎትና በስግደት ያዳክማቸዋል:: ያኔ በግዳቸው እየጮሁ ሲወጡ ደጉ አባት "ምነው ትንሽ ቆዩ እንጂ" ይላቸዋል::

+አጋንንቱም እያደነቁ "ከገነት ካስወጣነው ከአዳም በቀር እንዲህ ዓይነት ፍጡርስ ዓይተን አናውቅም" ብለው እንደ ጢስ በነዋል:: አጋንንት ስለሚፈሩት "አርበኛው መነኩሴ" ይሉታል::

የቅዱስ ዻኩሚስ ፍሬዎች

1.በግብፅ በርካታ ገዳማትን አቁዋቁሟል::

2.ለሁሉም ገዳማት አበ ምኔቶችን ሹሞ እየዞረ ይጠብቃቸው ነበር::

3.የመጀመሪያውን ሥርዓተ መነኮሳት አዘጋጅቷል::

4.መነኮሳት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሹመት እንዳይሾሙ ከልክሏል::

5.መነኮሳት ከገዳማቸው በፍፁም እንዳይወጡ ከልክሏል::

6.ከግብፅ ውጪ ምንኩስናን ያስፋፉ አባቶችን አስተምሮ አመንኩሷል:: (ለምሳሌ በኢትዮዽያ ምንኩስናን ያስፋፉት አቡነ አረጋዊ የዚህ አባት ደቀ መዝሙር ናቸው)

+ከዚሕም ባለፈ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል:: ቅዱስ ዻኩሚስ ጫማ ሳይጫማ: እሾህን ሳይሰቀቅ ይረግጥም ነበር:: የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እጥፍ ሆኖ የበዛለት ቅዱሱ መነኮስ ወደ ወደደው እግዚአብሔር በዚህች ቀን ሔዷል::

=>የጻድቁ መነኮስ ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን::

=>ግንቦት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዻኩሚስ (አበ መነኮሳት ሣልሳዊ)
2.አባ ሲማኮስ ሰማዕት

ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት 
  
ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም:: በእናት ማሕጸን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ:: ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ:: ስለ መንግስተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ:: ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው::  (ማቴ. 19:11)
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ግንቦት 1 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+"+ ቅዱስ ናትናኤል +"+

+በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት
መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ
ሐዋርያ ነው::

+ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ
ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን
ይታወቃል ቢሉ
እርሱ ሕጻን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ
እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ
በቅርጫት ውስጥ
አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው
ነበር::

+ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል::
በባልንጀሮቹ
ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ
ስላደገ): አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::
ምሑረ ኦሪት
ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር::

+በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል
የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ
የጠራበት አንዱ
ምክንያትም ይሔው ነው::

+ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ
ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ" እያለም
ይተክዝ
ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን
አውቆ በፊልዾስ አማካኝነት ጠርቶታል::

+ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን
ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት
ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል
አመስግኖታል::

+ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር
ምስጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ
ቅዱስም ሰክሮ ብዙ
አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ
ክርስቶስ) መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

+የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ
ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም 2ኛ
ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ
አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል::
በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል::
በገድለ
ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው
በ150 ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች
በመጨረሻ
ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::

❖እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን
ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን::
ከበረከቱም አይለየን::

=>ግንቦት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ (ቀናተኛው ስምዖን)
2.ቅዱስ ሚናስ ባሕታዊ
3.ቅዱስ ቀርጢኖስ ሰማዕት
4."400" ቅዱሳን ሰማዕታት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና
 
ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልዾስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ' አለው::  (ዮሐ. 1:48-51)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/05/22 17:51:28
Back to Top
HTML Embed Code:


Fatal error: Uncaught Error: Call to undefined function pop() in /var/www/tgoop/chat.php:243 Stack trace: #0 /var/www/tgoop/route.php(43): include_once() #1 {main} thrown in /var/www/tgoop/chat.php on line 243