Telegram Web
††† እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እሌኒ ንግሥት †††

††† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ330ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

††† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

††† ግንቦት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት እሌኒ ንግሥት
2.ቅዱስ ስልዋኖስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን::
(ሮሜ. ፲፮፥፲፱)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
††† እንኳን ለቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ †††

††† አናንያ : አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕጻናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም : በጸጋም : በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው::

ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል::

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኳ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ : ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር 60 ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ "ስገዱ" ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ 49 ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::

ከዚያች ቀን በኋላ አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው : በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል::

ቅዱሳን አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት 10 ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ነው::

††† አምላካቸው ከእሳት ባወጣቸው ቀንም:-
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ::
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: (በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል:: )

ድርሰታቸው 2 ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ600 ዓመት በኋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና 33 አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ33 ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል::

ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በኋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ400 ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ::

ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት::

ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::"

"ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ : ቄርሎስ : ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ::

እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል::

በረከታቸው ይደርብን::

ግንቦት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ሠለስቱ ደቂቅ ቅዱሳን (አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል)
2.ቅዱስ አብርሃም ጸራቢ (ሰማዕት)
3.አባ ሚካኤል ገዳማዊ
4.አባ ይስሐቅ ግብጻዊ

ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
4.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
6.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
ናቡከደነፆርም መልሶ:- መልአኩን የላከ : ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን : የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን : በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ::
(ዳን. 3:28)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ †††

††† ቅዱስ ያሬድ:- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን : ክብራችን : ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን?
*አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም)::
*ልቡናው የቅድስና ማሕደር::
*ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው::
*እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ!

ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት:- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ : ሙሉ አካሏ ነው::"

††† የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ †††

††† ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ505 ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር (ትምሕርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ::

ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ::

ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና::

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ : ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ:: ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው::

ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ:: በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር::

ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት : ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር : ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::

ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ : ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ::

††† ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት:-
1. አምስት ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል::
2. በጣና ቂርቆስ : በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል::
3.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል::

††† በ576 (571) ዓ/ም በተወለደ በ71 ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል::

††† አባቶቻችን:-
*ጥዑመ ልሳን
*ንሕብ
*ሊቀ ሊቃውንት
*የሱራፌል አምሳያ
*የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
*ካህነ ስብሐት
*መዘምር ዘበድርሳን
*ማኅሌታይ
*ልዑለ ስብከት
እያሉ ይጠሩታል::

††† የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን::

††† ግንቦት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ
2.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
3.ቅዱሳን ክርስቲናና ይስሐቅ (የቅዱስ ያሬድ ወላጆች)
4.ቅድስት ታውክልያ እናታችን (ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች)
5.ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት
6.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
7.ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት
8.አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ
9.አባ አሴር ሰማዕት (ኢትዮዽያዊ)
10.አባ በኪሞስ ጻድቅ
 
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ::
(2ቆሮ. 12:2-5)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምስለ ፍቁር ወልዳ pinned «https://youtu.be/6DLDfIIOrj4?si=oZfbs5ZH0QgNZT_I»
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ °+

=>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ
ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ?
ምንስ
እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ
ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ
አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን
እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

<< ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? >>

+ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ
ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ::
እነርሱ
ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው::
ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ
አደገ:: ገና
በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና)
ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም
አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ
ትምሕርት ይህ
ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2
ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ
ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

+ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና
እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ
መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ
ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ
ሲኖር
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ
ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ::
ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን
ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

+ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ
ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ
ራዕየ
ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ
ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው
ሳይታክት:
ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና
ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ
አንክሮ
ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና
ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

+ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ
በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው
ወደውታልና
የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ
ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል
የለም::
ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር::

+ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት
ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ
መካከል "
አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ
የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ
10 ዓመት
አቁሞታል::

+ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ
ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም
ይሔው
ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት
ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ
አወገዛት::
እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ
አጋዘችው::

+በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/
ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት
እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና
ለቅሶ ተደረገ::

+አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ
(ግብዣ አዘጋጀ):: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ
ታጥቆ ሲጸልይ
ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ
ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) በግርማ ሲወርዱ
ተመለከተ::

+ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ:
ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን
እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ
እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ"
አላቸው::
ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::

+በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ:
መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ
በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ
ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም::
ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ"
ብሎ በጉባኤ
መካከል ጠየቀው::

+"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ
ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ
አላወቃትም'
ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ
ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::

+"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ
የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ
ይቀያየራል::
እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ
መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::

+'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ
ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ
መልክ
ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::

+አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ
ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም
ሰምተው ሁሉም
ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ
ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች::

+ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ
አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ!
እሰግድ
ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም
የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን
ምስጋናም
ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ
ወጥተዋል::

+ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን:
ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት
የተነሳ ታላቅ
ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን
ባርኳል::

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
*ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
*አፈ በረከት
*አፈ መዐር (ማር)
*አፈ ሶከር (ስኳር)
*አፈ አፈው (ሽቱ)
*ልሳነ ወርቅ
*የዓለም ሁሉ መምሕር
*ርዕሰ ሊቃውንት
*ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
*ሐዲስ ዳንኤል
*ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
*መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
*ጥዑመ ቃል - - -

+እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ
ይክፈለን::

+ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56
ዓመታት
በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት
ተፈጽመዋል::

+እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ
በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት
ቃል ኪዳን
ተቀብላለች::

❖ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር
ያድለን::
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር)
2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን
የተቀበለችበት)
4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን 
❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት 
2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ
3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
6፡ ቅዱስ ላሊበላ
7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ

እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር
አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች
አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት
ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን
አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት
ይብራ::  (ማቴ 5:13-16)
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር)
2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው)
3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን
የተቀበለችበት)
4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ)
8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት)
9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን 
❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት 
2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ
3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
6፡ ቅዱስ ላሊበላ
7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ

እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር
አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች
አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት
ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን
አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት
ይብራ::  (ማቴ 5:13-16)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/06/15 21:34:46
Back to Top
HTML Embed Code: