tgoop.com/Ketbeb_mender/3522
Last Update:
♥️♡:。.。 እዮሪካ 。.。:♡♥️
ክፍል 23
✍ደራሲ - አብላካት
እኔም ከእነሱ መሀል እየነጠልኩኝ ማውራት ስለ ማልፈልግ አቤልንም ከዚህ በኋላ እኔን ብሎ እንዳይመጣ ነገርኩት.... ምክንያቱም ሳባን አውቃታለው ማናቸውም እንዲያዋሩኝ አትፈልግም እሱንም ከምታኮርፈው እኔው ብሸሽ ይሻለኛል። ሰዓቴን አመቻችቼ ስራዬንና ትምህርቴን እኩል ማስኬድ ችያለው። ገንዘቡ ያስፈልገኛል ሁሉም የእናቴን እጅ ነው እሚጠብቁት ሰርቶ እንኳን ይሄንን ልቻል እሚል የለም ሁሌም ብር ባስፈለጋት ቁጥር ከእንጀራ አባቴ ጋር መጨቃጨቋ ሰላሜን ይነሳኛል... አባቢ በህይወት እያለ ደልቶን ባንኖር እኔ እና እናቴ ግን የጎደለብን ምንም ነገር አልነበረም ምንም ሰርቶ ቢሆን እኔን ከጓደኞቼ እኩል እናቴንም ከጎረቤቶቿ አያሳንሳትም ነበር። ዛሬ ላይ ግን የየአማን እና የሊድያ የትምህርት ክፍያ ሲደርስ የወር አስቤዛ ሲያልቅባት ማጠፊያው ሁሉ ያጥራታል.....ለአንድ ለራሴ አላንስም ግን ደግሞ እናቴን በዚህ ሁኔታ እራስሽ ተወጪው ልላት አልችልም ፤ ገና ድሮ ለማግባት ስትወስን ትክክለኛው ሰው እንዳልሆነ ደጋግሜ ስነግራት የሷን ኑሮ ይኖሩላት ይመስል ሁሉም ጎረቤት የምን እራስ ወዳድነት ነው... ያንቺ አባት ከሞተ እናትሽ ህይወቷን አትኑር እንዴ እያሉ አፍ አፌን ይሉኝ ነበር....የኔ ፍራቻ ይሄ ነበር ዛሬ እናቴ ያለችበት ሁኔታ ለእሷ አይገባትም። ድሮ አግቢ አግቢ ብለው ገፋፍተው እዚህ መናጢ ላይ የጣሏት ሰዎች ዛሬ አንድ ኪሎ ሽንኩርት አይገዙላትም። ለምንድነው በሰው ህይወት ፈላጭ ቆራጭ እምንሆነው..... እናቴን የተመቀኘኋት ይመስል ሀሳቤን ሲያጣጥሉ ነበር አሁን ግን ብቻዋን ናት ያኔ ምን ነበር ያላችሁት ብዬ ዛሬ ላይ ብጠይቃቸው እርግጠኛ ነኝ መልሳቸው እሚሆነው ለሷ ብለን እንጂ አላስገደድናት ነው እሚሉኝ።
የኔን ህይወት እምኖረው እኔ ነኝ እናት እና አባቴ እንኳን የተሻለ እንዲገጥመኝ መመኘት እና መጥፎ እና ጥሩውን ሊነግሩኝ እንጂ ሊወስኑልኝ አይገባም.....የሰዎችን ሀሳብ አላጣጥልም እቀበላለው ግን ደግሞ ማንም የወሰነልኝን አልኖርም.... ነገ እኔ ብቸገር አብሮኝ እሚቸገር የለም እንዲህ አድርጊ እንዲህ ሁኚ ያለኝ ሁሉ ከንፈር ከመምጠጥ የዘለለ ምንም አያደርግልኝም። ውሳኔያችን ነጋችን ላይ ችግር እንደማይፈጥር ቆም ብለን ማሰብ አለብን ሰው ስላለን ስላበረታታን ብቻ የነሱን ሀሳብ ተቀብለን መተግበር የለብንም ባይ ነኝ። ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ሰውም በል በል ብሎ ከመሀል ያደርስል እንጂ አብሮ አይዘልቅም።
ከክላስ በኋላ ወደ ስራ ሄጄ ስራዬን ስጨርስ ማይለፍ እራት ጋብዞኝ ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍን....ወደ ቤት ሸኝቶኝ ሲመለስ ሊድያን ከሆነ መኪና ስትወርድ አየኋት። ሰውየውን እንደምንም ለማየት ስሞክር በእድሜ ገፋ ያለ ሰው ነው....ሹገር ዳዲ እሚባለው አይነት.... ለተራ ገንዘብ ብሎ እራስን ክብርን እንደ መሸጥ ምን ውርደት አለ ..... አንዳንዴ እንደ እህት ብትቀርበኝ እና ይህ ነገር እንደማይጠቅማት ብነግራት ብዬ እመኛለው.....እራሷን ስታጣ ዝም ብዬ መመልከቴን ሳስብ ክፉ የሆንኩ ይመስለኛል....ምንም ቢሆን የእናቴ ልጅ ናት ክፉዋን ማየት መስማት አልፈልግም። መኪናው ከሄደ በኋላ ወደ ግቢ ልትገባ ስትል እጇን ያስኳት....
"ያምሻል እንዴ አስደነገጥሽኝ እኮ! ምንድነው ?" አለችኝ...
"ማነው ሰውየው ?" አልኳት....
"ማንም አደለም ደሞ ማንስ ቢሆን ምን ያገባሻል!?"
"እሱ እኮ አባትሽ ይሆን ገና ልጅ እኮ ነሽ ለምን እንደ እድሜ አትሆኚም !"
"እራስሽን እንደ ታላቅ እህት ቆጥረሽ እየተቆጣሽኝ ባልሆነ ። ትሰሚኛልሽ የፈለኩትን ከፈለኩት ሰው ጋር መሆን እችላለው ይሄ አንቺን አይመለከትም " አለችኝ.....
"እዮልሽ ሊድያ ከዚህ እምታተርፊው እራስን ማጣት ነው እባክሽን እንደዚህ መሆንሽን አቅም"
"ነገርኩሽ እማይመለከትሽ ነገር ውስጥ ጥልቅ አትበይ። ምነው አንቺ ከዚህ የተሻለ ውሎ እምትውዪ አስመሰልሽው ከማንም ጋር ስትልከሰከሺ አደል እንዴ እምትውይው!" ብላ ንግግሯን ልትቀጥል ስትል ገፍትሬያት ወደ ውስጥ ገባሁኝ።
ይቀጥላል....
ቀጣዩ ክፍል 100❤️ ሲደርስ ይለቀቃል እያነበባችሁ አስተያየታችሁን አድርሱኝ...
ለአስተያየት - @Yetomah_Bot
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
@Ketbeb_Mender
@Ketbeb_Mender
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
BY የብዕር ጠብታ✍📒📖

Share with your friend now:
tgoop.com/Ketbeb_mender/3522