tgoop.com/Ketbeb_mender/3513
Last Update:
♥️♡:。.。 እዮሪካ 。.。:♡♥️
ክፍል 20
✍ደራሲ - አብላካት
ወዴት እንደ ምሄድ አላውቅም.....ጆሮዬ ላይ የነ ሳባ አወራር የእናቴ ጥፊ የነ ሊዲያ አጥንት እሚሰብር ንግግር ያቃጭልብኝ ጀመር....ብቻ ዝም ብዬ መሮጤን ቀጠልኩ ፤ የት እንደሆነ እማላውቀው ቦታ ላይ ስደርስ ቆምኩኝ ደከመኝ! ታከተኝ! አቃተኝ! እረፍት እና ተስፋ በሌለው ህይወት ውስጥ መኖር ይደክማል። ደስታ ምን እንደሆነ ሳላውቀው ቀን በቀን ሀዘንን ማስተናገድ ታከተኝ ፤ ላይሞላ የጎደለን ዓለም ለመሙላት መሞከር ዘበት ነው። አባቴ ናፈቀኝ እምባዬን ማየት እሚያመው አባብዬ አለመኖሩ ለዚህ ሁሉ እንደዳረገኝ ሳስብ አምላኬን ወቀስኩት አማረርኩት.....እሱ ቢኖር እኮ ማንም ቀና ብሎ አያየኝም... እሱ ባይሞት እኮ ይሄን ሁሉ አላሳልፍም ነበር። ዛሬ እኔ እየኖርኩ ላለሁት ህይወት ተጠያቂው ማን ነው ? እናቴ ? አባቴ ? የእንጀራ እህት ወንድሞቼ ? የእንጀራ አባቴ ? እኔ ? ወይስ ፈጣሪ ? ማነው ተወቃሹ! ሌላ ሰው ላይ እያስታከኩ እራሴን ከጥፋተኝነት ማዳን ባልፈልግም ግን ደግሞ ይሄን ህይወት ለመኖር ከጅምሩም ፍላጎቱ እንዳልነበረኝ አውቃለው። እንደ ሁሉም ሰው ወጣትነቴን በአግባቡ ተደስቼ ማድረግ እምፈልገውን አድርጌ መደሰት በምፈልገው ልክ ተደስቼ ማለፍ ነበር ምኞቴ። ምን ያደርጋል ካሰብኩት አንዱን እንኳን ሳልኖረው ሊያልፈኝ ነው። መመኘት እንጂ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ የገባኝ የራሴን ኑሮ አይቼ ነው። አላማርርም እኮ ከኔም የባሰ እንዳለ አውቃለው እሱንም ብዬ ተመስገን ማለትን መርጬ ነበር ፤ ምን ዋጋ አለው ይቺ ክፉ አለም የተሳካ ነገር እንዳገኘ እድሉን አለመስጠጧ ሳያንስ ለበጎ ነው ማለቴንም ልትነጥቀኝ እየዳዳች ነው።
እድል እሚያገኝ ሰው ግን ምነኛ የታደለ ነው። ገንዘብ ካለው ነገሮችን ለማስተካከል እድል የተሰጠው ሰው ነው ለኔ ሀብታም ፤ ያጣነውን ለመመለስ ፣ የጎደለንን ለመሙላት ፣ ያለቀስነውን በሳቅ ለመለወጥ ፣ ነጋችንን የተሻለ ለማድረግ እድል ማግኘትን የመሰለ ነገር ምን አለ ? ይኽው አንድ እድል አይቼ አደል ያለእድሜዬ ላረጅ የደረስኩት። እኔ እኮ የተሟላ ነገር አልተመኘሁም አንድ ምኞቴ ሰላም ማግኘት ብቻ ነው ለምን ችግር ገጠመኝም ብዬ አልጠየኩም መደራረቡ እንጂ ያደከመኝ ከዚህ የተሻለ ህይወት ቢኖረኝም እኮ ችግር መኖሩ አይቀሬ ነው። ሰላምን የመሰለ ምን ነገር አለ ?
ስልኬ ጠራ... ማይለፍ ነው ከማታ ጀምሬ ስላላወራሁት እንዳይጨነቅ ብዬ አነሳሁት.
"ቃልዬ ?" ....መናገር አቃተኝ...
"ሄሎ!"
"ማይለፍ እባክህን ናልኝ" አልኩትና ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩኝ....እንዴት እንዲ እንዳልኩት ለኔም ማመን ከብዶኛል...
"ምን ሆንሽብኝ እእእ እሺ የት ነሽ ?"
"እኔንጃ"
"ተረጋጊና ያለሽበትን ንገሪኝ እባክሽን"
"ከኛ ሰፈር ስትወጣ የሚገኘው ኮንደሚኒየም ጀርባ ያለው አስፓልት ጋር ነኝ"....እራሴን ለማረጋጋት እየሞከርኩ ያለሁበትን ነገርኩት።
" እሺ መጣሁ በቃ ወዴትም እንዳትሄጂ" .......ብሎኝ ስልኩ ተዘጋ። ከግማሽ ሰዓት በኋላ የማይለፍን መኪና ወደኔ ሲመጣ አየሁት... እምባዬን መጠራረግ ጀመርኩኝ.....ከመኪናው ወርዶ እግሬ ስር ቁጭ አለና......
"ምን ተፈጥሮ ነው ?" አለኝ። ምን ብዬ ልመልስለት የተፈጠረው እኔንም ግራ አጋብቶኛል....
"ከፋኝ" አልኩት....ቶሎ ብሎ ወደ ደረቱ አስጠጋኝና አቀፈኝ....ለረጅም ደቂቃ እቅፉ ውስጥ ቆየሁኝ ሰላም ተሰማኝ የሆነ ሸክም ከላዬ ላይ የወረደልኝ መሰለኝ። ከቆይታ በኋላ...
"ምግብ ግን በልተሻል ?" አለኝ
"እ አይ አልበላሁም ጠዋት የወጣሁ ነኝ" አልኩት
"ምሳ ልጋብዝሽ ?"
"ደስ ይለኛል" አልኩትና ተነስተን መኪና ውስጥ ገባን። ማንንም ላለማዋራት ብዬ ስልኬን ዘጋሁት .....በዚህ ሰዓት ሁሉንም ነገር እረስቼ መረጋጋት ብቻ ነው እምፈልገው። አንድ ሆቴል ስንደርስ የመኪናውን በር ከፈተልኝና ወረድኩ ሊያቅፈኝ ሲሞክር እንደመሸሽ አልኩኝ... ደነገጠ....
"ይቅርታ በጣም እሚረብሽሽ አልመሰለኝም ነበር" ሲለኝ የፍቅር ጥያቄውን መቀበሌ ትዝ አለኝ። መልሼ በራሴ አፈርኩ....
"አይ እኔ ነኝ ይቅርታ ማለት ያለብኝ አንተ እኮ ልክ ነህ" አልኩት.....እና እንዲያቅፈኝ ተጠጋሁለት። ፈገግ አለ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ፈገግታው ፈገግ አስባለኝ። ፈገግታው ሳቁ ከልቡ ስለሆነ ነው መሰል ያምርበታል። ወደ ውስጥ ገብተን ምግብ አዘን መመገባችንን ጀመርን ...
"ምን አንደተፈጠረ ልትነግሪኝ ፍቃደኛ ነሽ ?" አለኝ...ምኑን ልንገረው እናቴ ለሚጠሏት ወግና መታችኝ ብዬ ?... ጓደኞቼ የክፉ ቀኖቼ እምላቸው ውሸት አምነው ጠሉኝ ብዬ ?...የቱን ነው እምነግረው ህይወቴ ውስጥ ችግሮች ከመፈራረቃቸው ይተነሳ እኔም ለመረዳት ከብዶኛል እንኳን ለሱ ላስረዳው።
"ሌላ ጊዜ ብሰፊው እነግርሀለው"
"ካልሽ እሺ እጠብቃለው። ድግሞ ትምህርት ነገ ነው መሰለኝ እምትጀምሩት አደል ?"
"እ አዎ ነገ ነው።"
"ታዲያ ስራሽን እንዴት ልታደርጊ ነው ?"
"ያው አስፈላጊ ቢሆንም ከትምህርቱ ጋር አብሮ ስለማይሄድ አቆማለው"
"ነገ ከክላስ ስትወጪ ወደ እኔ መምጣት ትችያለሽ ?"
"እሺ እሞክራለሁ" አልኩትና ሂሳብ ከፍሎ ወጣን። እምትሰሪው ከሌለ ጋሼ ጋር ደርሰን እንምጣ" አለኝ.......
"በጣም ደስ ይለኛል እንሂድ" አልኩትና ወደ እሳቸው ጋር ሄድን።
ዛሬም ከቤታቸው ደጃፍ ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚውን ይመለከታሉ። ጠጋ ብለን...
"ደህና ዋሉ ጋሼ ?" አላቸው ማይለፍ...
"ውይ ልጆቼ እንዴት ዋላችሁ ?" ብለው ከመቀመጫቸው እንደመነሳት አሉ...
"ደህና ነን ጋሽዬ እርሶ እንዴ ኖት ?" ጠየቃቸው
"ፈጣሪ ይመስገን ደህና ነኝ ልጆቼ። ግባና መቀመጫ ይዘህ ና" አሉት ማይለፍን..
... ወደ ውስጥ ሲገባ...
"ልጄ ደህና ነሽ ?" ጠየቁኝ
"አዎ ጋሼ ደህና ነኝ"
"ግን ንግግርሽ እና ሁኔታሽ አንድ አደሉምሳ" አሉኝ...
"እንዴት ጋሼ ?"
"ውስጥሽ እምባ እንጂ እንዲህ ፊትሽ ላይ እንደሚታየው አይነት ፈገግታ የለማ የኔ ልጅ" አሉኝ
"ሁሌም እኮ ደስታ የለም ጋሼ"
"እሱስ ልክ ብለሻል ሁሌም ደሞ ሀዘን የለም። ባለፈው ስትመጪ ሁኔታሽ ቢገባኝም ሳያውቁኝ እንዴት ያወራሉ እንዳትይኝ ብዬ ነበር ዝም ማለቴ። አሁን ግን ልጄ ሁነሻል ታዲያ መጠየቅ አልችልም እንዴ የኔ ልጅ ?"
"ኧረ ይችላሉ አባቴ"
"ዛድያ ንገሪኛ ምን ሁነሽ ነው እንዲህ መከፋትሽ ?"
"አባቴ...." ብዬ ገና ንግግሬን ከመጀመሬ ማይለፍ ወንበር ይዞ መጣ.... ንግግሬን ገታ አደረኩኝ። እሳቸውም...
"ጌታ መሳይ ዛሬ ስራ የለም እንዴ ?" አሉት
"ነበረኝ ግን ከቃልዬ ጋር ላሳልፍ ብዬ ነው። ምነው ጋሼ ?"
"ከእሷ ጋር እምናወራው ነበረን...ስራ ቢጤ ካለህ ወደዚያ ሄደህ ስንጨርስ ደውላለህ መተህ ብትወስዳት ብዬ ነበር ጌታ መሳዬ ቅር ካልተሰኘህ"
"ኧረ ችግር የለውም እንደውም ከፍቷት ነበር ጋሼ ለኔ አልነግርም ስላለችኝ በዛውም እሱን ጠይቃት"
"እሺ እጠይቃለሁ የኔ ልጅ" አሉት
"ቢሮ የጀመርኩት ስራ ስለነበር እንደውም እሱን እሰራለሁ። ስትጨርሱ ደውይልኝ እና እመጣለሁ"
"እሺ እደውልልሀለው"
"በሉ በቃ ሰላም ዋሉ" ብሎን ሄደ...
ይቀጥላል....
ቀጣዩ ክፍል እንዲለቀቅ እያነበባችሁ አስተያየታችሁን አድርሱኝ...
ለአስተያየት - @Yetomah_Bot
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
@Ketbeb_Mender
@Ketbeb_Mender
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
BY የብዕር ጠብታ✍📒📖

Share with your friend now:
tgoop.com/Ketbeb_mender/3513