tgoop.com/Ketbeb_mender/3489
Last Update:
♥️♡:。.。 እዮሪካ 。.。:♡♥️
ክፍል ፲፯
✍ደራሲ - አብላካት
ውስጤ በጥቂጡም ቢሆን ፍርሀት ነበረ ነገር ግን ማይለፍ ሊጎዳኝ እሚችል አይነት ሰው ነው ብሎ ልቤ ስላላመና እያመነታሁም ቢሆን መኪናው ውስጥ ገባሁኝ። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ አብሮኝ ቦታው ላይ ስንደርስ ከመኪናው እንድወርድ ነገረኝና ወረድኩኝ። ቦታውን ከዚህ በፊት አይቼው አላውቅም ትልቅ ሆቴል ነው አካባቢውን ለማወቅ ዙሪያዬን ብቃኝም ላውቀው አልቻልኩም ግን ትልቅ ሆቴል ነው። ወደ ውስጥ ስገባ ቤቱ በሰዎች የተሞላ ነው ከዳር እስከዳር ጢም ብሏል አለባበሳቸው ፣ አቀማመጣቸው ሁሉም ነገር ከቤቱ ደረጃ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው ነው። በአይን የማውቃቸው ባለሀብቶችም አለፍ አለፍ ብሎ አሉ። ሆቴሉ ከላይም ፎቅ ላይ ቦታ አለው። ሁሉም ነበር ስገባ ዞረው የተመለከቱኝ ትንሽ ያስፈራል በአይኖቼ ዙሪያዬን እየቃኘሁ ማይለፍን መፈለግ ጀመርኩኝ። እኔ ከቆምኩበት በስተቀኝ በኩል ስዞር ማይለፍን ከደረጃ ላይ ሲወርድ ተመለከትኩት የሆነ የሆሊዉድ አክተር ነው እሚመስለው ልቤ በሀይል እየመታ ነው በጣም አምሮበታል አለባበሱ ከሌላው ጊዜ በተለየ ይስባል። አጠገቤ ሲደርስ የልብ ምቴ ይባሱኑ ጨመረ። ጠጋ ብሎ አቀፈኝ ምናለ ባይለቀኝ ብዬ ተመኘሁኝ ...እንዳቀፈኝ
"በጣም አምሮብሻል" አለኝ
"አመሰግናለሁ ግን ካንተ አልበልጥም" መለስኩለት። እየሳቀ እጄን በእጁ ይዞ ወደ ፎቁ ወጣን.... አንበሩን ስቦ እንድቀመጥ ጋበዘኝ ከዛም....
"ቅድም አስጨነኩሽ አይደል እዚህ አካባቢ የስራ ስብሰባ ስለነበረኝ ከምመለስ ብዬ ነው ሰው የላኩት ይቅርታ ይደረግልኝ"
"ትንሽ አስፈርቶኝ ነበር ግን አሁን እረስቼዋለው"
"ዋናው መርሳትሽ ነው። ቤቱን ግን ወደድሽው ?"
"ውይ አዎ በጣም ነው እሚያምረው ለየት ያለ ቤት ነው"....... የቤቱን ውበት ባልክድም እንደ እውነታው ግን እኔ ይህን መሰል ቦታዎች ላይ ብዙም ነፃነት አይሰማኝም ምክንያቱም እራሴን የሆንኩኝ ስለማይመስለኝ አንዳንዴ ሳንፈልግ እምንላበሳቸው ባህሪዎች አሉ አደል ከትላልቅ ሰዎች ጋር አልያም ልባችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች ፊት ስንሆን ያ ሰው ለኛ ያለው ስሜት እንዳይቀንስ አልያም እኛን በጥሩ መልኩ እንዲያስበን ከመፈለጋችን የተነሳ እንዲሁም ትላልቅ ቦታዎች ላይ ስንገኝ ደግሞ ለቦታው መመጠናችንን ለማሳየት ስንል ፈልገነውም ይሁን ሳንፈልገው ውስጣችን እሚፈጠር አዲስ ባህሪ ከነበርነው ማንነታችን ወጣ ያለ ሰው እንሆናለን ባለማስተዋልም ይሁን በማስተዋል እንዲህ አይነት ባህሪ ውስጣችን አለ። ለዚህም ነው እንዲህ አይነት አካባቢዎች ላይ መገኘትን እማልፈልገው። ግን ደግሞ ይህንን አይነቱን ባህሪ ሰዎች በመጥፎም በጥሩም መልኩ ሲጠቀሙጥ አስተውያለው...... ሁለት ፍቅረኛሞች አበረው ከመሆናቸው በፊት በትውውቃቸው ጊዜ ሴቷ ወንዱን የምታውቀው ወጣ ባለ ባህሪው ነው እሱ ግን እየቆየ ሲሄድ ከሷ ፍቅር ይይዘዋል በዛን ጊዜ ለሱ ያላትን አመለካከት ስለሚያውቅ በሰው ዘንድ እሚጠላ ባህሪውን ይቀይርና ጥሩ ሰው የሆነ መስሎ ለትንሽ ጊዜ በጓደኝነት ይቀርባታል እሷም ያንን የተሻሻለ ባህሪውን ስትመለከት ለሱ ያላት ስሜት ወደ ፍቅር ተቀይሮ አብራው ለመሆን ፍቃደኛ ትሆናለች። አብረው ሲሆኑም እሷን የሱ ለማድረግ ሲል የተጠቀመውን የውሸት ባህሪውን ይቀጥልበታል ፤ በሆነ አጋጣሚ ግን ከጓደኞቹ ጋር እሷን ለመቅረብ ሲል ያልተቀየረውን ተቀይሬአለው ብሏት እንደነበርና በርግጥም ግን አሁን ላይ የበፊት ባህሪውን እንደማይፈልገው እና በዚሁ መቀጠል እንደሚፈልግ ሲያወራ ትሰማለች እሷም ሰምታ እንዳልሰማች ትሆናለች ምክንያቱም እንደሰማችው ነግራ ብትጣላው ወደዛ ባህሪው በድጋሚ ይመለሳል ብላ ስለፈራች አውቃ እንዳላወቀ ሆነች አሁን ላይ በጣም ደስተኞች ነው። ይህንን አይነቱን ለጥሩ ነገር ሲባል የውሸት ማስመሰልን እደግፋለው ግን ደግሞ አለው ወይም አላት ለመባል በሰው ዘንድ ለመክበርና ትልቅ መስሎ ለመታየት ሲባል እሚፈጠርን ማስመሰል በጣም ነው እምጠላው ማስመሰል ጥሩ ጎን ባይኖረውም ሊጎዳ እማይችል መንገድም ሊኖረው ይችላል ልክ እንደ ፍቅረኛሞቹ ታሪክ። ለዚህም ነው እራሴን ከእንደዚህ አይነት ነገሮች ለማራቅ ስል ትላልቅ ቦታዎች እና ትላልቅ ሰዎችን ማግኘት እማልፈልገው። የሌላቸውን አለኝ ያጡትን አገኘው እያሉ በማስመሰል ህይወት ውስጥ እሚኖሩ ስንቶች አሉ ባለሀብቶችን ሲያዩ እንደነሱ ለመሆን እሚያስመስሉ ፤ የተቸገረ ሲያዩ ከነሱ ያልተናነሰ ኑሮ እየኖሩ ግን ያጣው ፊት እሚመፃደቁ ስንት የቀጨጨ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች አሉ። ማስመሰልን እንደለውጥ እሚቆጥሩ ሲያስመስሉ እውነትም እሚያስመስሉትን ህይወት እየኖሩት ያሉ እሚመስላቸው ስንት ሞኞች የሞሉባት አለም። ከዚህ ሁሉ ደረጃንና አቅምን ያማከለ ቦታ ላይ መገኘትን ያመሰለ ምን ነገር አለ። ሳይታወቀኝ በራሴ ሀሳብ ውስጥ ሰጥሜ ልጁን እረሳሁት.....
"ችግር አለ እንዴ ቃል ?" ሲለኝ ከሰጠምኩበት የሀሳብ ባህር ውስጥ ወጣሁኝ
"እእ አይ ምንም ችግር የለም ምነው ?"
"ከቅድም ጀምሬ ምን እንዘዝ እያልኩሽ ነው ግን አትመልሺም"
"ይቅርታ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው። ባንተ ምርጫ ይሁን ደስ ያለህን እዘዝ" አልኩት
"ካልሽ እሺ" ብሎ በሱ ምርጫ አዘዘ። ምግቡ እስኪመጣ ማውራት ጀመርን ከዚህ ቀደም የገጠመሽ ገጠመኝ ካለ አጫውቺኝ ሲለኝ ከነ ሳቢ ጋር ስሆን እሚያጋጥሙንን ነገሮች እየነገርኩት በጣም ሳቀ ፈገግታው በጣም ያምራል ሳላስበው ሲስቅ ሳየው ልቤ ላይ የሆነ ነገር ተሰማኝ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም ብቻ ግን የሆነ ደስ የሚል ስሜት። ሲስቅ በግራ ጉንጩ ላይ ዲምፕል ይወጣል ከጥርሶቹ ጥራት ጋር ተደምሮ ይበልጥ አሳምሮታል አላውቅም ብቻ ግን የሆነ ሄደሽ ተጠምጠሚበት እሚል ስሜት ይሰማኛል። በተቻለኝ አቅም እራሴን ለመቆጠብ እየሞከርኩኝ ነው። ለምንድነው እንደዚህ እምሆነው ? ለምንስ የዚህን ያህል ለሱ ተሰማኝ ? አሁንም ቀልብ እሚሰርቅ ፈገግታው አልቆመም.....ያዘዝነው ምግብ እና መጠጥ ተከታትሎ መጣ ፤ እሱን እየተመገብን ጨዋታችንንም ቀጠልን በመሀል አተኩሮ ሲያየኝ እምገባበት ጠፋኝ አንገቴን ሰበር አደረኩኝ።
"ምነው ማየት የተከለከለ ነው እንዴ ?" ጠየቀኝ
"ኧረ በጭራሽ እንደዛ አላልኩም" መለስኩለት
"ስቀልድ ነው። እራቱን ስንጨርስ ሌላ እምንሄድበት ቦታ አለ"
"ከዚህ ሰዓት በኋላ ወዴት ?"
"ገና እኮ ነው ብዙም አልመሸም እኔው እራሴ ወደ ቤት እሸኝሻለው" እምቢ ልለው አልፈለኩም እቤት ሄጄም እድሜ ለእህትና ወንድሜ ደህና ነገር አይጠብቀኝም ከእነሱ ሽሽት ይሆን ከሱ ጋር ለመሆን ፈልጌ ባላውቅም ግን በሀሳቡ ተስማምቻለው.....
"እሺ እንሄዳለን" አልኩት።
ይቀጥላል.......
ቀጣዩ ክፍል እንዲለቀቅ እያነበባችሁ አስተያየታችሁን አድርሱኝ
ለአስተያየት- @Yetomah_Bot
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
@Ketbeb_Mender
@Ketbeb_Mender
✯┄┅┅✿❀♥️❀✿┅┅┄✯
BY የብዕር ጠብታ✍📒📖

Share with your friend now:
tgoop.com/Ketbeb_mender/3489