tgoop.com/Islam_and_Science/6101
Last Update:
#መይት_ዛዴ(የሙት ልጅ)
✍አሚር ሰይድ
መይት ዛዴ ስለሚባል ቱርካዊ ሰምታችሁ ታቃላችሁ??ይህ ሰዉ በሱልጣን ሙሀመድ ቀዳማዊ ዘመን የኖረና በመልካም ምግባሮቹ የሚታወቅ የሀይማኖት ምሁር ነበር። መይት ዛዴ (የሙት ልጅ) የተባለበት ምክንያት በሚከተለው ክስተት አማካይነት የደረሰ ነው፡፡
የመይት ዛዴ አባት የኦቶማን ቱርክ መንግሥት ወታደር ነበር። ልክ እንደ ሌሎቹ የሀገሩ ጀግኖች ሁሉ በ1596 በተደረገውና ሱልጣን ሙሐመድ ሳልሳዊው በመራው የኢግሪ ዘመቻ እንዲሳተፍ ጥሪ ተደረገለት፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ጊዜ ሚስቱ ልትወልድ ተቃርባ የነበረ ሲሆን ጤንነቷም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ያ ጀግና ወታደር በአላህ መንገድ ላይ መዋጋትን ከሁሉም ነገር በላይ ያፈቅር ስለነበር ሚስቱ ይቅርታ እንድታደርግለት ከጠየቃት በኋላ ለዘመቻው ዝግጅት ማድረጉን ተያያዘው፡፡ ከዚያም እጆቹን የአርሹ ባለቤት አላህ ወዳለበት ሰማያዊ ችሎት ዘርግቶ የሚከተለውን ፀሎት አደረሰ
♦ጌታዬ ሆይ! እኔ ባንተ መንገድ ልዋጋ መጓዜ ነው፡፡ ካንተ በቀር ሌላ ረዳት የለኝም። ጌታዬ ሆይ! ይህን ልጄን ለዚህች ታማኝና ብዙ ድካም የሚታይባት ባለቤቴ ስጥቸዋለሁ፡፡ እባክህን አንተ ጠብቅልኝ።"
ጀግናው ሰው ይህን ካለ በኋላ ከፈረሱ ላይ ወጥቶ በመጋለብ ከዓይን ተሰወረ። በአላህ እርዳታና ፀጋ የኦቶማን ጦር በውጊያው ድል አደረገ፡፡
ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ጀግናው ወታደር፣ አዛዦቹ ወደ ቤቱ እንዲሄድ ይፈቅዱለት ዘንድ ጥያቄ አቀረበ፡፡ በቀጥታ ወደ ቤት ጋልቦ እዚያ ሲደርስ ግን በቤቱ ውስጥ ማንም አልነበረም😔፡፡ ባለቤቱ የድሉን ወሬ ስምታ ከሆነ ቤቱን ሞቅ አድርጋ በደስታ ልትቀበለው በተገባት ነበር፡፡ ሆኖም እንኳን አቀባበል ልታደርግለት ይቅርና በቤት ውስጥ አልተገኘችም። በታላቅ ጭንቀትና ጥንቃቄ ወደ ጎረቤቶች ሄዶ ምን እንደተፈጠረ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም ሰውዬውን ሲያዩት በሀዘን እንደተዋጡ እንዲህ አሉት- “አንተ ጀግና ሆይ! አላህ ድልህን ይባርክልህ፤ እንዲሁም ሕይወትህን ፀጋ የተሞላበት ያድርግልህ፡፡" ከዚህ አባባል ጀርባ ያለውን ትርጓሜ እያሰላሰለ ልቡ መቃጠል ስለጀመረ ሳይፈልገው እምባ😢😢የታከለበት ሲቃ ፈንቅሎት እንዲህ አለ፡-
"ሊሆን አይችልም:: የታለች ሚስቴ? ተወዳጁ ልጄስ የታለ? የልጄን ነገር ለዓለማት ጌታ በአደራ ሰጥቼዋለሁ፡፡ እርሱ ከሁሉም ጠባቂዎችና ተንከባካቢዎች በላጭ ነው::” ይህን ካለ በኋላ በሀዘን ተኮማትሮ እምባዉን እያነበ ለረዥም ጊዜ ፀጥ በማለት ቆየ። ከዚያም ዙሪያውን የከበቡትን ሰዎች እንዲህ አላቸዉ፡-
“እርግጥ ነው አላህ ከሁሉም በላይ አዛኝ የሆነ ጌታ ሲሆን አደራ በመጠበቅ በኩል ደግሞ እጅግ ታማኙ ነው፡፡ የባለቤቴን መቃብር አሳዩኝ አላቸዉ::"
....ከሰዎች ጋር ወደ መቃብር ሥፍራ አብሮ ከሄደ በኋላ የባለቤቱን መቃብር ሲያይ በመቃብሩ አፈር ላይ ጆሮውን ጣል አድርጎ ያዳምጥ ጀመር። ከዚያም፡- “አዎን! የልጄን የለቅሶ ድምፅ ሰማሁ!" በማለት እንደ እብድ ጮኸ፡፡
ይህን ካለ በኋላ ዶማና አካፋ እንዲመጣለት ጠይቆ መቃብሩን ይቆፍር ጀመር፡፡ ከእርሱ ጋር የመጡት ሰዎችም እያገዙት አፈሩ ሲወገድ የሕፃኑ ለቅሶ በግልፅ ይሰማ ጀመር፡፡ መቃብሩ ጨርሶ ከተከፈተ በኋላ በለህዱ (በጓዳው) ውስጥ አስደናቂ ተዓምር ተከሰተ፡፡
በሞተችው እናቱ ደረት ላይ ልጥፍ ያለ ወንድ ልጅ ታየ፤ የጦር ጀግና የሆነው ያ ወታደር ልጁን ወዲያውኑ ከእናቱ ደረት ላይ አንስቶ ወደ ደረቱ በማስጠጋት አቀፈው፡፡ ከዚያም የሚያምሩና ሮዝ መልክ ያላቸው ጉንጮቹን ደጋግሞ ይስመው ጀመር፡፡ ህፃኑን በጨርቅ ጠቅልሎ ለስዎች ከሰጣቸው በኋላ በውድ ባለቤቱ ላይ ሶላተል ጀናዛ ሰግዶ መቃብሩን እንደነበር በጥንቃቄ ዘጋው፡፡
ይህን ሁሉ ትዕይንት ዙሪያውን ከበው ሲመለከቱት የነበሩ ሰዎች በድንጋጤ ደርቀው ቀርተዋል። እየደጋገሙ የአላህን ተዓምራት በማስታወስ ስሙን ያወሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ምህረት ይጠይቃሉ፡፡
አባትዬው ግን ዓይኖቹ በእንባ እንደተሞሉ ልቡ በሚስቱ ሀዘንና በልጁ በሕይወት መትረፍ በተፈጠረበት የሀዘንና የደስታ ድብልቅ ስሜት ተውጦ ግራ እንደተጋባ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ይህ ልጅ ከዚያ ጊዜ በኋላ በታላቅ የእምነትና አላህን የመፍራት ድባብ ውስጥ እንዲያድግ ተደረገ፡፡ በመላው የኦቶማን ቱርክ ግዛትም የታወቀ አላህን ፈሪ ሰው ለመሆን በቃ:: 'መይት ዛዴ' በሚለው መጠሪያ ስሙ በሁሉም ሰው ዘንድ የታወቀ ነበር፡፡ ይህ ሰው በእርግጥም የእውነተኛ በአላህ የመመካት ውጤትና የኃያሉ አላህ ማለቂያ የሌለው ተዓምራት መገለጫ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ኖሯል፡፡
እኛ አላህ ጋር ያለን መመካት ምን ያህል ይሆን??
ለሌሎች ያካፍሉ
join👇👇👇
www.tgoop.com/IslamisUniverstiy_public_group
www.tgoop.com/IslamisUniverstiy_public_group
BY ISLAMIC SCHOOL
Share with your friend now:
tgoop.com/Islam_and_Science/6101