tgoop.com/Islam_and_Science/6013
Last Update:
ከመፅሀፍ ገፅ ➊
#የነብዩ ሰዐወ መቃብር ቁፈራ የተጋለጠበት!!
አዘጋጅ ☞አሚር ሰይድ
የታሪክ መጻሕፍት በ557 ዓ.ሂ የተከሰተን አንድ አስገራሚ ጉዳይ ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ ያ ዘመን የዐብባሳውያን ሥርወ-መንግሥት በመንኮታኮት ላይ የነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በአጐራባች አገራት ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን መንግሥታት አንድ ከባድ ሴራ ጠነሰሱ። ሴራቸው የሙስሊሞችን መዳከም ተገን አድርገው የነቢዩን አስከሬን ከነበረበት በመስረቅ ወደ ራሳቸው ግዛት መውሰድ ነበር፡፡ ይህን በማድረግም በሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ ሞራላዊ ጉዳት ለማድረስ
አሰቡ::
ስለዚህ ይህን ረቂቅ ተንኮል ለማስፈፀም ሁለት የተመረጡ ሰላዮችን የሞሮኮ ኢስላማዊ አለባበስ በማልበስ ወደ መዲና ከተማ ሰደዱ ሰዎቹም ለነዋሪዎቿ ለፀሎት ወደ ቅድስቲቷ ከተማ የመጡ ሐጃጆች መሆናቸውን እንዲናገሩ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጣቸው፡፡ ሁለቱ ሰዎች ተልዕኮኣቸውን ለመወጣት እንዲችሉ መስጂደል ነበዊ (የነቢዩ መስጂድ) አጠገብ ባለ ቤት ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡ በጐረቤቶቻቸውም ዘንድ ለመታመን ሲሉ መስጂድ ማዘውተርና የዒባዳ ተግባራትን በጥልቀት ማከናወን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡ ዋናው ጉዳያቸው ግን የተላኩበትን ዓላማ ማስፈፀም እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህን ተልዕኮ ለማከናወን የመጀመሪያ ሥራቸውንም ከነበሩበት ቤት አንስተው ወደ ነቢዩ መቃብር ለመድረስ ውስጥ ለውስጥ በመቆፈር መሿለኪያ ለማበጀት ቁፋሮ ጀመሩ፡፡ እንዳይነቃባቸውም በየቀኑ ትንሽ ትንሽ ብቻ እየቆፈሩ የሚያወጡትን አፈር በትናንሽ መያዣዎች አድርገው ጀለቢያቸው ሥር በማንጠልጠል አል-በቂፅ ወደሚባለው የመዲና
የቀብር ስፍራ እየወሰዱ ይደፉ ነበር። ሌሎቹ ነዋሪዎች ሰዎቹ በየዕለቱ ወደ ቀብር ሥፍራ የሚሄዱት የሞቱትን በመዘየር ሞትና አኼራን ለማሰብ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ሰዎቹ አንዳንዴ ሲደክማቸው መሿለኪያ ለማበጀት የሚቆፍሩትን አፈር ከሚኖሩበት ቤት አጠገብ ወዳለ ጉድጓድም ይደፉ ነበር። እንዲህ እያደረጉ በመጨረሻ መሿለኪያውን ከነቢዩ ሰዐወ ቀብር ጋር ሊያገናኙ ደረሱ፡፡ እዚህ ደረጃ ሲደርሱ ተልዕኮኣቸው ለመሳካቱ እርግጠኛ ስለነበሩ የትኩረት አቅጣጫቸው የነቢዩን አስከሬን ካወጡ በኋላ በምን መንገድ ወደ መጡበት ግዛት እንደሚያጓጉዙ ማቀድ ነበር፡ የተለያዩ ዘዴዎችን አውጥተው አወረዱ፡፡ በዚያው ወቅት አላህ የራሱን ሴራ እያሴረባቸው እንደሆነ ግን አላወቁም፡፡
የዘመኑ የሙስሊሞች መሪ የነበሩትና ከመዲና ብዙ ርቀው የሚኖሩት ኑረዲን ሙሐመድ ኢብኑ ዘንጂ በዚያው ሰሞን አንድ ለየት ያለ ሕልም እዩ፡፡ በሕልማቸው ውስጥ ነቢዩ ሰዐወ ነበር የታዩዋቸው፡ ነቢዩ ወደ ሁለት ቀያይ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች እያመለከቱ ከእነርሱ እንዲያድኗቸው ኑረዲንን ይማፀናሉ ይህን ከባድ ሕልም ሲመለከቱ ኑረዲን በድንጋጤ እየተንቀጠቀጡ ከእንቅልፋቸው ነቁ። ራሳቸውንም ለማረጋጋት ሶላት ከሰገዱ በኋላ ተመልሰው ወደ መኝታቸው ቢሄዳም አሁንም ያው ሕልም ተመልሶ መጣባቸው:: ሕልሙ ለሦስተኛ ጊዜ ሊመጣባቸው ከእንቅልፋቸው በመነሣት ከሚንስትሮቻቸው መካከል ሷሊሕና ብልህ የነበረውን ጀማሉዲን አል ሙሲሊ የተባለውን አስጠሩ፡፡ ያዩትን ሕልም ለጀማሉዲን ሲነግሩት ሕልማቸው በመዲና ውስጥ የሆነ እንግዳ ነገር እየተከናወነ መሆኑን እንደሚጠቁም አስረዳቸው፡፡ በአስቸኳይም ወደ ነቢዩ ከተማ በመሄድ ስለ ሕልሙ ለማንም ሳይናገሩ ሁኔታዎችን እንዲከታተሉ አሳሰባቸው፡፡ ኑረዲን ከለሊቱ የቀረውን ክፍል ለጉዞው ዝግጅት ሲያደርጉ አደሩ፡፡ ጀማሉዲንን ጨምሮ ሃያ ጭነት ከሃያ ሰዎች ጋር እንዲዘጋጅ አዘዙ፡ ከሻም(ሶሪያ) ተነስተው መዲና ለመድረስ የፈጀባቸው ዐሥራ ስድስት ቀናት ብቻ ነበር። መዲና ሲደርሱ በፍጥነት የሄዱት በመስጂደል ነበዊ ውስጥ ወደሚገኘው አልረውዳ ልዩ የሶላት ስፍራ ነበር፡፡ እዚያ በመሄድም ዱዓ አደረጉ:: ይሁን እንጂ ሕልሙን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሊያውቁ አልቻሉም፡፡ አማካሪያቸው ጃማሉዲን በሕልማቸው ውስጥ ያዩዋቸው ሁለት ሰዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ እንዲነግሩት ሲጠይቃቸው ኑረዲን የሰዎቹን መልክና አለባበስ እንደሚያስታውሱና ቢያገኙዋቸው መለየት እንደሚችሉ ነገሩት፡፡ ጀማሉዲን ሰዎቹን ለመያዝና ሴራቸውን ለማክሸፍ ቆርጠው በመነሳታቸው ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድ ጀመሩ፡፡ የመዲና ነዋሪዎች በመስጂዱ ውስጥ ሲሰበሰቡም እንዲህ የሚል ማስታወቂያ አስነገሩ፡፡ 'መሪያችን በሶደቃ ለመስጠት ነይተው ያመጡት ብዙ ሃብት አለ፡፡ ሶደቃውን ለማከፋፈል እንዲመቸን በችግር ውስጥ ያላችሁ ሰዎች ሁሉ እየመጣችሁ ስሞቻችሁን እንድታስመዘግቡ እንጠይቃለን የሚል፡፡ ይህን ማሳሰቢያ እንዳስነገሩ ሰዎች ሶደቃውን ፍለጋ ተንጋግተው መምጣት ሲጀምሩ ኑረዲን በሕልማቸው ውስጥ ያዩዋቸውን ሰዎች ለመለየት ዳር ቆመው እያንዳንዱን ሰው ይቃኙ ነበር። ብዙ ሰዎች መጥተው የድርሻቸውን እያነሱ ቢሄዱም ኑረዲን ተፈላጊዎቹን ሁለት ሰዎች ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
በመጨረሻም ከሶደቃው ድርሻውን ያልወሰደ ሰው እንዳለ ሲጠይቁ የሆነ ሰው ·ከሞሮኮ የመጡ ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎቹ በጣም ሷሊሕ ሰዎች ስለሆኑ ሶደቃውን ለመቀበል አልፈለጉም አላቸው፡፡ ኑረዲን ይህን እንደሰሙ ሁለቱን ሰዎች በአስቸኳይ እንዲያመጧቸው አዘዙ፡፡ ኑረዲን ሁለቱ ሰዎች እፊታቸው እንደቀረቡ ሰዎቹ ነቢዩ ሰዐወ በሕልማቸው ያመለከቷቸው ሰዎች መሆናቸውን በቀላሉ አወቁ። ሰዎቹንም “ለመሆኑ ከየት ነው የመጣችሁት? በማለት ጠየቁ፡፡ እነርሱም የመጣነው ከመግሪብ ነው፣ አመጣጣችን ለሐጅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ዓመት እዚሁ ለማሳለፍ ወስነናል' አሏቸው:: ኑረዲን ሰዎቹ የሆነ ያቀዱት ሴራ መኖሩን ቢጠረጥሩም ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ለመለየት ስላልቻሉ ድብቅ ሴራቸውን ይፋ እንዲያወጡ በማሰብ የተለያዩ ጥያቄዎችን አከታትለው ቢጠይቁም ምንም ፍንጭ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በዚህም የተነሣ ምንም እርምጃ ሊወስዱባቸው አልተቻላቸውም:: ኑረዲን ቀጥለው ያዘዙት ቤታቸው ይፈተሽ የሚል ነበር፡፡ ቤታቸው ሲፈተሽም በቤቱ ውስጥ ካስቀመጡት በርካታ ገንዘብ ውጭ ሊያስጠረጥራቸውና ሊያስወነጅላቸው የሚችል ምንም ነገር ሳይገኝ ቀረ፡፡ ለፍተሻ ወደ ቤታቸው የገባ ሰው አንድ በአንድ መውጣት ሲጀምር ኑረዲንም ምንም ምልክት በማጣታቸው ቤቱን ለቀው ሊወጡ ሆነ: በዚያች ቅፅበት ነበር አላህ የሙስሊሞቹ መሪ አንዳች ነገር አትኩረው እንዲመለከቱ ያደረገው ኑረዲን ወለሉን ሲቃኙ በወለሉ ላይ ከተነጠፉት ጣውላዎች ው አጥብቆ እንዳልያዘ አስተዋሉ፡፡ ይህን እንዳዩ ጐንበስ በማለት ጣውላውን ሲያነሱ የመዲናን ነዋሪዎች ጉድ ያሰኘ ክስተት ተስተዋለ። በወለሉ መሿለኪያ መቆፈሩን ነዋሪዎቹ ግን ይበልጥ የተደናገጡት መሿለኪያው ወዴት እንደሚያመራ ሲረዱ ነበር፨ መሿለኪያውን የቆፈሩት በከተማይቷ ውስጥ በሷሊሕነታቸው ይታወቁ የነበሩት ሁለቱ የሩቅ አገር እንግዶች መሆናቸው ሌላው ግርምታ የፈጠረ ጉዳይ ሆነ፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሁለቱ ሞሮኮኣውያን የሚታወቁት በጥልቅ ዒባዳቸውና በላቀ ኢስላማዊ ሥነ-ምግባራቸው ነበር፡፡ እጅግ የተናደዱት መሪ ኑረዲን ሁለቱን ሰዎች መግረፍ ሲጀምሩ ሰዎቹ በርግጥ ከመግሪብ (ሞሮኮ) አንዳልመጡና በመሪያቸው ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው የተላኩ ክርስቲያኖች መሆናቸውን የመጡትም የነቢዩን አጽም ቆፍረው በማውጣት በድብቅ ወደ አገራቸው ለመውሰድ መሆኑን አመኑ፡፡ ኑረዲን ሁለቱ ሰዎች በሞት እንዲቀጡ አዝዘው የተቆፈረው መተላለፈያም በአስተማማኝ መልኩ በአለት እንዲደፈን አደረጉ፡፡ ሴራውንም እንዳከሸፉ ወደ ሻም (ሶሪያ) ተመለሱ፡፡
BY ISLAMIC SCHOOL
Share with your friend now:
tgoop.com/Islam_and_Science/6013