tgoop.com/Islam_and_Science/5745
Last Update:
📖 #የመራም_ማስታወሻ
ክፍል ~ ➐
✍ ፀሀፊ ☞አሚር ሰይድ
ቤቱንም ጊቢውንም አፅድቸ እንደጨረስኩ ለመሄድ የጊቢውን በር ስከፍት አቶ አለማየሁ ጋር ተገጣጠምን.......
አቶ አለማየሁ እድሜያቸው ከሀምሳወቹ መጨረሻ እስከ ስልሳወቹ መጀመሪያ በሚገመት እድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ፊት ለፊት ሲያዩኝ " እንዴት አደርሽ የኔልጅ" አሉኝ
" አልሀምዱሊላህ ሰላም አደሩ ጋሸ" ብየ መልስ ሰጠሁ
" ምነው ዛሬ አንች መጣሽ እናትሽ ደህና አይደለችም እንዴ!?"
"አረ ደህና ናት ዛሬ ረፍት ስለሆንኩ ላግዛት ብየ ነው"
"ጎሽ የኔ ልጅ ጥሩ አረግሽ እንዲህ ነው ልጅ ማለት" ብለው እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ከተው ተጣጥፎ የተጠቀለለ የብር ኖቶችን አወጡና " ይሄ ለአንዳንድ ነገር ይሆንሻል"ብለው ሰጡኝ፡፡ እኔም በጣም ደስ ብሎኝ አመስግኘ ተቀበልኩ፡፡ " አይዞሽ ወደፊት ብዙ እጠቅምሻለሁ አንች ብቻ እኔ የምልሽን እሽ ማለት ብቻ ነው" ብለው እጃቸውን ትከሻየ ላይ ሲያሳርፉ ሰውነቴን ቅፍፍ አለኝ በቅፅበት በንዴት ፊቴ ተቀያየረ ...ግን ንዴቴን ሊያቀልልኝ የሚችል ቃል ፈልጌ አጣሁ ድንገት አፌ ላይ የመጣልኝን " አንተ የትልቅ ትንሽ የተዋረድክ ሽማግሌ በጣም አሳፋሪ ነህ" ብየ የሰጠኝን ብር በትኘለት ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
ብቻየን ሁኘ አለቀስኩ ሂወትን ታዘብካት ድሆች ሺህ ለማገኘት ያለ እረፍት ወር ሁሉ ይለፋሉ ሀብታሞች ለብልግና በቀናት ከሺህ በላይ ያወጣሉ አይ ዱንያ ለአንዱ ድሎት ለአንዱ ፈተና ምናለ ሚዛናዊ ሆነሽ ለሁሉ እኩል ብታካፍይ!? ብየ ደግሞ መለስ ብየ የንዴት ሳቅ መሳቅ ጀመርኩ፡፡ "ይገርማል የሰው ልጅ ግን ትንሽ ሰብአዊነት አይሰማውም!? ልጄ ብሎ አብረሽኝ ተኝ ማለት ምን ማለት ነው!? ንዴቴ ጣሪያ ቢነካም ኡሚ እንዳታውቅ ሚስጥር አድርጌ አፎኘ አስቀረሁት፡፡
ኡሚ ይሄን ከሰማች ዳግም ወደዛቤት እንኳን የኔ የሷም እግር አይረግጥም! ግን ወ/ሮ ጥሩወርቅ ጥሩ ሴት ናቸው ይሄን ነገር ሰምተው ከባላቸው ጋር እንዳይጣሉ ይሁን ወይም ደግሞ የሚሰጡን ጥቅማጥቅም እንዳይቋረጥ ይሁን አላውቅም ብቻ ዝም ብያለሁ ዳግም ወደዛ ቤት ግን አልሄድም ብየ ሀሳብ ሳውጠነጥን " መሪ መተሻል እንዴ ?? አዩብን ይዠ ወጣ ብየ ስትገቢ አላየሁሽም" ብላ ሪም ከሀሳቤ አባነነችኝ "
....እ አወ ተመልሻለሁ ማንም አልነበረም ስገባ" ብየ አዩብን አቅፌ ማጫወት ጀመርኩ፡፡
አዩብ ከኔ በተሻለ ከሪም ጋር ጊዜ ያሳልፋል ለዛም ይመስላል ሪምን በጣም ይወዳል ኡሚ ቤት ብትኖርም ምርጫው ሪም ናት! አዩብን ሳይ ውስጤ በሀዘን ይላወሳል! አንድ ቀን ድሎትን ሳያይ በችግር ተወልዶ በችግር ይኖራል ሚስኪን አዩ! ኡሚም ባየችው ቁጥር "አዩ ለኔ ስህተቴም መፅናኛየም ነው፡፡ ያረገዝኩት በስህተት ቢሆንም ግን ያጣኅቸውን መልሶ አዩ ያፅናናኛል ትላለች፡፡ ባለችን አቅም ሰርተን በምናገኛት ገንዘብ ለአዩብ ፍላጎት ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ቤተሰቦቼ ሆኑ ጓደኞቸ " መሪ" ብለው ቢጠሩኝም አዩ ግን በተኮላተፈ አንደበቱ "መሊ" ብሎ ሲጠራኝ በፍቅር ልቤን ያሞቃታል፡፡ ጣፍጭ አንደበቱን ሁሌም አልጠግበውም! አይ ልጅነት! ገና ልጆች እያለን ነበር ሪም ስሜን አቆላምጣ "መሪ" ብላ የጠራችኝ የሷን ተከትለው የሰፈር ልጆች በስሜ ብዙ ቀን አስለቅሰውኛል፡፡ "መሪ" ማለት የመኪና መሪ ነው አባቷ ሹፌር ስለሆነ ለዛ ነው መሪ የሆነችው" ሲሉኝ አለቅስ ነበር፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም ሂጀ ሰደቡኝ ብየ አለቅስ ነበር፡፡ ያኔ ሪም ብቻ ነበር "መሪ" ብላ ስጠራኝ የምደሰተው አሁን ግን መጠሪያየ ሆኗል፡፡
ጊዜ ጊዜን እየተካ መክነፉን ተያይዞታል፡፡ ይሄው እኔም ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ይች አመት ብቻ ቀረችኝ ሪምም ወደ መሰናዶ ለመሽጋገር ሁለታችንም የሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ነን፡፡ አዩም ሶስት አመት ሞላው፡፡ ኡሚ ኑሮ ቢያበሳቁላት ብትጎዳም ቁንጅናዋ እንዳለ ነው፡፡ የማይጠወልግ ውበት! ዩኒቨርስቲ ገብቸ በከፍተኛ ማእረግ ተመርቄ እዛው ዩኒቨርስቲ መቅረት እና ኡሚን ከዚህ ህይወት መገላገል የምጓጓለት ህልሜ ነው! እኔ በዚህ መልኩ ራሴን ከቻልኩ ሂወት አትከብደንም፤ እኔና ሪም ተጋግዘን የእማን ሂወት ማቃናት አያቅተንም፡፡ ስለዚህ ማትሪክን ከፍተኛ ውጤት አምጥቸ እማን ተስፋ ልሰጣት አይዞሽ ደርሸልሻለሁ ትንሽ ታገሽ ልላት ጥናቴን ተያያዝኩት፡፡
በጣም ግራ የገባኝ ነገር ኡሚ አልፎ አልፎ ሲያነስራት አያለሁ፡፡ " አሞሻል" ስላት "አይ ፀሀም ላይ ስለምውል ለዛነው እንጅ ደህና ነኝ አሁንማ ደርሰሽልኛል የኔ ልጅ ከባዱን ጊዜ እንኩዋን ብቻየን አልተውሽኝም ብቻ ተስፍየ በትምህርትሽ ነውና ትምህርትሽ ላይ ጠንክሪ" ትለኛለች፡፡ ሪም እና እኔ ፈተና ጨርሰን ክረምቱን ምን እንስራ እያልን እየተወያየን በመሀል ኡሚ ወደ ቤት ገባች፡፡ የማይጠገበውን ፍቅሯን ሳትሰስት መስጠት የማይሰለቻት ኡሚ ዛሬ ግን ደህነኛ አልመሰለችኝም ፡፡ ሳቅ እና ፈገግታዋ የውሸት የማስመሰል ሆነብኝ አንድ የረበሻት ነገር እንዳለ ገባኝ፡፡
....ቀስ ብየ ተጠግቸ ምን እንደሆነች ጠየኩዋት እቅፏ ውስጥ አስገብታ ሳመችኝና አይን አይኔን አየችን፡፡ የልቤ ምት ፈጠነ የሆነችውን ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ አይኖቿን ከኔ አንስታ ወደ ሪም አየች፡፡ ሪም ከአዩብ ጋር እየተጫወተች ወደኛ ትኩረት የላትም፡፡ እማ ወደ ሪም ማየቷ ሪም መስማት የለለባት ከበድ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ገመትኩ ጭንቀቴ በረታ.........ጉዳዩ ምን ይሆን???
የመራም ማስታወሻ #ክፍል ➑
https://www.tgoop.com/IslamisUniverstiy_public_group
BY ISLAMIC SCHOOL
Share with your friend now:
tgoop.com/Islam_and_Science/5745